‘‘የኳሱ ንጉሥ’’

0
88

ከአቶ አሰፋ ገብረ ስላሴ ከወ/ሮ ጥሩ መሸሻ በ1936 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቡልቡላ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ተወለዱ:: በቤተሰቦቻቸው የሥራ ዝውውር ምክንያትም ፍቅር ከሆነዉ ቤተሰባቸዉ ፍቅርን እና መተሳሰብን ባህል ባደረጉት ታሪካዊ ከተሞች በሆኑት ናዝሬት፣ ሐረር እና ድሬዳዋ ኖረዋል::

በታዳጊነት ዕድሜያቸው ለብሄራዊ ቡድን ለመጫወት ከበቁት እና ስመ ጥር ከሆኑት ኢታሎ ቫሳሎ፣ ሉቺያኖ ቫሳሎ እንዲሁም ከአስራት ጎራዴዉ ጋር በድሬዳዋ ኮተኒ እና ምድር ባቡር የእግር ኳስ ቡድኖችን በመመልከት፣ ብሎም በመጫወት የኳስ ሕይወትን እንደጀመሩ ይናገራሉ። ከድሬዳዋ ክለብ በተጨማሪ ቀይ ኮከብ ከሚባል አንድ የጣሊያን ቡድን ጋር እግር ኳስ ተጫውተዋል፡፡

ትምህርታቸውን ድሬዳዋ የተከታተሉ ሲሆን በ1971 ዓ.ም ወደ ጎጃም ክፍለ ሀገር ብር ሸለቆ እርሻ ልማት በማምራት ሥራ ጀምረዋል፤ አሰልጣኝ ዘነበ አሰፋ::

አሰልጣኝ ዘነበ አሰፋ በስራ ምክንያት ወደ ጎጃም ብር ሸለቆ ከተዛወሩ በኋላ በሚፈልጉት ልክ ምኞታቸውን ማሳካት ባይችሉም ከልጅነታቸው ጀምሮ ለእግር ኳስ ያላቸው ፍቅር ከፍ ያለ በመሆኑ በ1971 ዓ.ም ወደ ጎጃም እንደመጡ በብር ሸለቆ እርሻ ልማት ውስጥ ለነበረው አረንጓዴው ብር ለሚባል የእግር ኳስ ቡድን በተጫዋችነት እና ለመጀመሪያ ጊዜ በአሰልጣኝነት የወቅቱ የጎጃም ክፍለ ሃገር ሻምፒዮን እስከመሆን ደርሰዋል::

ከዚያም ለአስር ዓመታት ያክል ያገለገሉበትን የብር ሸለቆ እርሻ ልማትን በመልቀቅ ወደ ፍኖተ ሰላም ከተማ አመሩ፡፡ በዚያም በ1969 ዓ.ም የተቋቋመውን የቀድሞውን ገራይ የአሁኑን ዳሞት ከነማ የእግር ኳስ ቡድንን ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት አስርት ዓመታት በታላቅ ፍቅር እና ወኔ በማሰልጠን ቡድኑንም ሆነ ተጨዋቾችን ታላቅ ደረጃ ላይ ማድረስ ችለዋል::

በአሰልጣኝነት ጊዜአቸው በርካታ ተጨዋቾችን እና አሰልጣኞችን ማፍራት ችለዋል። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተለያዩ ክለቦች ውስጥ ከተጫዋቾች አድማሱ አንተነህ፣ አብርሃም ብርሃኔ፣ ገበያው ሽፈራው፣ ሰለሞን ተስፋዬ እና የመሳሰሉትን አፍርተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኝ ገብረ መድህን ኀይሌ እና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለም በዘነበ አሰፋ ሰልጥነዋል።

ለዳሞት ከነማ እግር ኳስ እድገት ዕውቀታቸዉን፣ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ሁሉንም ነገራቸውን የሰጡ ጀግና ተብለው የሚመሰከርላቸዉ ታላቅ ሰው ለመባልም በቅተዋል፡፡

አሰልጣኝ ዘነበ አሰፋ ከበኲር ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ እግር ኳስ ሲናገሩ፣ “ሙያዬ ብቻ አይደለም፤ ብዙ መስዋእትነት የከፈልኩበት ህይወቴም ጭምር ነው” ይላሉ፤ ከተጨዋችነት እስከ አሰልጣኝነት ብዙ ዓመታትን በእግር ኳስ ጨዋታ ማሳለፋቸውን በመግለጽ። “ለዚህ ደግሞ ከእኔ ይልቅ ዛሬ የተሰጠኝ እውቅና ምስክር ነው” ሲሉም ያነሳሉ።

አሰልጠኝ ዘነበ አሰፋ ከስፖርቱ ዘርፍ በተጨማሪ በንግድ እና በሆቴል ስራ፣ በቤት እንዲሁም በቢሮ ዕቃዎች አምራችነት፣ በዳቦ ቤት እና በከብት እርባታ ላይ በመሰማራት ለበርካታ ዓመታት በዉጤታማነት የዘለቁ ሰዉም ናቸዉ፡፡

በዚህም በስፖርቱም ሆነ በንግድ ስራዎቻቸው በታማኝነት እና በሃቀኝነት እንዲሁም ዘመን ተሸጋሪ የሆኑ ስራዎችን በማበርከት በፍኖተ ሰላም ማህበረሰብ ዘንድ የተከበሩ ሰው ናቸው፡፡

አሰልጣኝ ዘነበ አሰፋ በልጆቻቸዉ እና በሚያሳድጓቸዉ የልጅ ልጆቻቸዉ የሞቀ እና የደመቀ የትዳር ሕይወት የሚመሩ፤ ከራሳቸዉ አልፈዉ ለሌሎች የተረፈ የሀብት ባለቤት ነበሩ፡፡ በርካታ አድናቂዎቻቸው፣ ወዳጆቻቸው እና አለፍ ሲሉም የስፖርት ወዳዱ ማህበረሰብ ለዳሞት ከነማ ላደረጉት ነገር ሁሉ ምስጋናን ችሯቸዋል።

ዳሞት ከነማ የእግር ኳስ ክለብ ከምስረታው ጀምሮ ከፍተኛ ሊግ እስኪደርስ ድረስ ሚናቸው ግንባር ቀደም ነበር። በክለቡ ባበረከቱት አስተዋጽኦ እና ባሳዩት ብቃትም በአካባቢው ስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ “የእግር ኳሱ ንጉሥ” እስከመባልም ደርሰዋል።

ዳሞት ከነማ የእግር ኳስ ክለብን ከምስረታው ጀምረው ጠንክረው በማሰልጠናቸው በአንድ ዓመት ብቻ ከወረዳ እስከ ክልል በተደረጉ ውድድሮች  ሶስት ዋንጫዎችን በማንሳት ክለቡን ሻምፒዮን በማድረግ አንቱታን አትርፈዋል።

በአጠቃላይ አሰልጣኝ ዘነበ አሰፋ ከ1971 ዓ.ም እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ በብር ሸለቆ የእርሻ ልማት ውስጥ የአረንጓዴው ክለብን እና ዳሞት ከነማን በአሰልጣኝነት ጊዜ ቆይተዋል። የዳሞት ከነማ የእግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ለነበሩት ዘነበ አሰፋ በክለቡ ለነበራቸው አበርክቶ በክለቡ ተጨዋቾች እና የአካባቢው ስፖርት አፍቃሪያን እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ወጣት ሙሉጌታ ተረፈ በዳሞት ከነማ የእግር ኳስ ክለብ ውስጥ ለአንደኛ እና ከፍተኛ ሊግ በተጫዋችነት አገልግሏል። ስለ አሰልጣኝ ዘነበ አሰፋ ሲናገር፣ “ጋሼ አሰልጣኛችን ብቻ ሳይኾን አባታችንም ጭምር ነው፤ ከስልጠና ስንመለስ ቤቱ ወስዶ ምግብ አብልቶ፣ መክሮ፣ አበራትቶ ይሸኘን ነበር ‘’ ይላል። በማያያዝም “ትጋት፣ ቁርጠኝነት እና ለዓላማ መፅናት የጋሼ መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ እኔ አሁን የጅም ቤት አሰልጣኝነት ሙያ እንድይዝ ደግሞ ጋሼ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው” በማለት ይገልፃል።

ሌላኛው የቀድሞው ተጫዋች አቶ መላኩ ጥላሁን በክለቡ ለበርካታ ዓመታት የቆየ ሲኾን አሁን ደግሞ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽ (ካፍ) የ ‘C’ ፍቃድ የአሰልጣኝነት ሙያ አለው፡፡ ስለ አሰልጣኝ ዘነበ ሲናገር ‘’ጋሼስ መጫወትን በተመለከተ ብቻ አደለም ስልጠና የሚሰጠን፤ በስነ ምግባር ተኮትኩተንም እንድንወጣ ጭምር ነው፤ አሁን ላለሁበት የአሰልጣኝነት ሙያ ምሳሌዬ ነው” በማለት ይላል። “አሰልጣኝ ዘነበ ለሙያው ያለውን ፍቅር በመግለፅ ሁላችንም በተሰማራንበት ሙያ በፍቅር ብንሰራ ብዙ ተዓምር መስራት እንችላለን” በማለትም ቁጭት የወለደው አስተያየት ሰጥቷል።

የቀድሞ ተጫዋቾች ደግሞ ለስፖርቱ  አስተዋጽኦ ላደረጉ እውቅና መስጠት ተተኪ ስርተኞችን ለማፍራት ሚናው የጎላ መኾኑን ገልፀዋል ።

የፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደርም ለአሰልጣኙ የተለያዪ ድጋፎችን ያደረገ ሲኾን በተጨማሪም የፍኖተ ሰላም ከተማ ስቴዲየም መግቢያ እና መውጫ ዘነበ አሰፋ በሚል እንዲጠራ አድርጓል።

(ንጉስ ስንታየሁ)

በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here