የወሬያችን ነገር!

0
145

የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

ዓለም አንድ ለውጥ ካመጣችበት ቴክኖሎጂ አንዱ ቋንቋ ነው፡፡ ቋንቋ ደግሞ በንግግር ይገለጻል፤ ንግግር አንድ ተናጋሪ ለአድማጩ በቃል የሚያቀርበው ሀሳብ፣ መልዕክት፣ አስተያየት ሲኾን በሰዎች መካከል የሚደረግ የቃል ጭውውት፣ የሃሳብ ልውውጥ መኾኑን “ዘርጋው ከፍተኛ የአማርኛ መዝገበ ቃላት” ይገልፃል፡፡ ስለዚህ ንግግር ሁለት እና ከዚያ በላይ በኾኑ ሰዎች መካከል በሚደረግ የቃላት ልውውጥ እንደኾነ መረዳት ይቻላል፡፡ መናገር ብቻ ሲኾን ደግሞ አንድ ሰው ብቻ ይናገራል ሌሎች ከማድመጥ ውጭ ሃሳባቸውን መግለፅ አይችሉም ማለት እንደኾን መረዳት ይቻላል፡፡ ንግግር ሲኾን ከአንደኛው ተናጋሪ ባሻገር ሁለተኛውና ሌሎች ሰዎች ከመስማት ባለፈ ሃሳባቸውን በመግለጽ ተሳታፊ ይኾናሉ ማለት ነው፤ ስለዚህ ሰብሰብ ብለን ስንጫወት ሁላችንም ሃሳባችንን በሚገባና አጭር በኾነ መንገድ መግለጽ መቻል ደግሞ ጨዋታውን የደመቀ፣ ጓደኝነታችን የጠበቀ፣ መገናኘታችን የሚናፈቅ፣ ውይይታችንም እውቀትን የሚያጎናጽፍ እንዲኾን ያደርጋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ የሚገጥሙን ሰዎች እራሳቸው አውርተው፣ እራሳቸው ጥያቄ ጠይቀው እና ራሳቸው መልሱን መልሰው ይጨርሱታል፤ መሰብሰብ ብለው ቆመውም ኾነ ተቀምጠው የሚነጋገሩበት ሳይኾን የአንድ ሰውን ወሬ ብቻ ሰምተው የሚመለሱበት ይኾናል፡፡ የዚህ አይነት ሰዎች ያሉበት ጨዋታ፤ ጨዋታ መኾኑ ይቀርና የአንድ ሰው ማባሪያ የሌለው ወሬ ጥረቃ ይኾናል፡፡ ከዚያም እርሱ ባለበት ምን ጨዋታ አለ ይባላል፤ ምክንያቱም ያ’ሰው ሁልጊዜ እራሱ አውርቶ እራሱ የሚጨርስበት ስለሚኾን፡፡ ከዚህ ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ይህ ሰው የሚያወራው ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ የሌለው፣ እራሱን እያገነነ ሌሎችን እያኮሰሰ እና ትክክለኛ  አለኾኑ ነው፡፡

እራሳቸው አውርተው ራሳቸው የሚጨርሱ ሰዎች መነሻቸው ራሳቸውን ሰው ዝቅ አድርጎ ይመለከተኛል ብለው ማሰባቸው ሲኾን መድረሻቸው ደግሞ ብዙ በማውራት ከሌሎች በመረጃ የላቁ፣ ያወቁ፣ የነቁና የበቁ መስሎ መታዬት ነው፡፡ ይኹን እንጅ የሚያወሩት ፋታ ሳይሰጡና አድማጮችን ሳያሳትፉ መኾኑ፣ ትክክለኛ መረጃ አለመኾን እንዲሁም በቅንጭብ እውቀት ላይ የተመሠረተ መኾኑ ከመወደድ ይልቅ ጥላቻን፤ ከመከበር ይልቅ መናቅን፤ ንግግር አዋቂ ከመባል ይልቅ ወሬኛ የሚል ስያሜን ያሰጣል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አንዱ ሁልጊዜ እኔ ነኝ የማውቅ፣ እንዲህ አድርጌው፤ እንዲህ አደርጋለሁ እያለ በየጊዜው ጓደኞቹን በወሬ ፋታ ያሳጣቸዋል፤ ታዲያ ጓደኞቹ ከሠራው ይልቅ ያወራው ሲበዛባቸው “አውግቸው” የሚል ቅጥል ስም ሰጡት፤ ወደ እነርሱ ሲመጣም “አውግቸው መጣ እንግዲህ ስማው” እያሉ ቀድመው ያሽሟጥጡታል፡፡ ይህ ሽሙጥ ለልጅ እና ለቤተሰብ ሲሰማ ለወረኛው ሰው ብቻ ሳይኾን ውርደቱ ለቤተሰብም ይኾናል ማለት ነው፡፡

ብዙ ጊዜ ወሬ የሚያበዙ ሰዎች በእውቀት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ እንደኾኑ ምሁራን ይገልፃሉ፤ በምሳሌ ሲነግሩንም ’’ጥልቀት የሌለው ጅረት ጩኸት ያበዛል፥ የረጋ ውሃ በጥልቀት ይጓዛል’’ ይሉናል፡፡ ወሬና ጩኸት የሚያበዛው ከእውቀት ነጻ የኾነ ወይንም በዝቅተኛ የእውቀት ደረጃ ላይ ያለ መኾኑን ሲያስረዱን፤ በዚሁ አጋጣሚ ለሁለተኛ ድግሪ/ማስተርስ/ ትምህርት በጀመርኩበት ጊዜ የነበርነው ተማሪዎች ሁላችንም በሥራ ልምድ የጠገብን ስለነበርን ከዚህ በፊት ከነበረን የትምህርት እውቀት፣ በንባብና በሥራ ልምዳችን ካገኘነው እውቀት ተነስተን ዶክተሩ በክፍል ውስጥ ሲያስተምሩን ለሚያነሱት ጥያቄ በፍጥነት በመመለስ ብቻ ሳይኾን በተቀነጨበ እውቀት ላይ ተመሥርተን በረጅሙ እያብራራን የማስተማሪያ ጊዜያቸውን እየበላን ስናስቸግራቸው፤ ዶክተሩ “ከዚህ በኋላ እንደ ማስተርስ ተማሪነታችሁ መልስ ስትሰጡ የመረጃ ምንጭ እየጠቀሳችሁ ነው” በማለታቸው እርሳቸው የሚሰጡንን ትምህርት ብቻ መቀበል ጀመርን፤ ለሚጠይቁትም ጥያቄ ስንመልስ “ማን ነው ያለው” ሲሉን ስለማናውቀው ከማፈር ለመውጣት በደንብ እያነበብን በመምጣት መመለስ ጀመርን፤ በመማሪያ ክፍላችን ጫጫታችን ቀነስ አድርገን አድማጭ መኾን ጀመርን፡፡ ሥለዚህ ያለ እውቀት ማውራት ደፋር ያደርጋል፤ ስለምናወራው ነገር ብቻ ሳይኾን ስለምናወራላቸው ሰዎች እንኳ ግድ አይኖረንም ማለት ነው፡፡

ከሰዎች ጋር ስንነጋገር ቅድሚያ አድማጭ መኾንን መምረጥ፤ ስንናገርም ሰዎች ይታዘቡናል ብለን መመዘን፤ በምናውቀው ጉዳይ ላይ ብቻ አተኩረን በመናገራችንም ነገ የማናፍርበት እውነት መኾኑን አረጋግጠን መኾን አለበት። ይህ ሳይሆን “ጅብ ከማያውቁት ሀገር ሔዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ” እንደሚባለው ሰዎች እኔን አያወቁኝም፤ ጉዳዩን አያውቁትም እና አዋቂ መስዬ እታያለሁ ብሎ አፍ እንዳመጣ ማውራት የራስን ክብር ዝቅ ያደርጋል። የቤተሰብንም ክብር የሚነካ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ ላይ አንድ የደርግ ዘመን ወታደር የነበረ ሰው ያጫወተኝን ነገር ላካፍላችሁ፤ ይህ ሰው በወታደራዊ ማእረግ ያለፈ፤ ብዙ የጦር ቀጣናዎች ላይ የተሳተፈ እና በወቅቱ ላይ በቂ መረጃ የነበረው ሰው ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሰው በአንድ የድራፍት ቤት በረንዳ ላይ ቁጭ ብሎ ድራፍት ሲጠጣ ከጎን ከተቀመጡት ሰዎች መካከል አንዱ “እኔ በደርግ ወታደር ቤት ብዙ ነገር ያሳለፍኩ ነኝ” እያለ ይቀደዳል። ታዲያ ይህ ወዳጄ ይገርመውና “በየትኛው ግንባር ተሳተፍክ ተጋድሎህስ ምንድን ነው” እያለ ጥያቄ ሲያቀርብለት ያለምንም ሀፍረት እግሩን አራጦ ቀደዳውን ቀጠለ፤ በአጋጣሚ አውቀዋለሁ እና ነበርኩበት የሚለው የደርግ ዘመን ክፍለጦር ውስጥ የእኔ ወዳጅ በአመራርነት ነበርና “ታዲያ እኔን ታውቀኛለህ ማለት ነው? እኔ እኮ በክፍለጦሩ ውስጥ መቶ አለቃ ሆኘ አገልግያለሁ” ብሎ ስሙን ይጠቅስለታል፡፡ እግሩን አራጦ አፉን አስፍቶ ወሬውን ሲቀድ የነበረው ሰው፤ እሳት የነካው ፌስታል መስሉ ሰውነቱ ሁሉ መሰብሰብ ጀመረ፤ ቅስሙ እንክት አለ፡፡ ይህንን ነገር ስሰማ አይደለም እሱ እኔም ስለ እርሱ የሰማሁት አነስኩ፤ ቅስሜ ስብር አለ፡፡

ራሳችንን ካላወቅን፣ ስሜታችንን መቆጣጠር ካልቻልን እና ለሰዎች ግድ የማይሰጠን ከኾነ በንግግር ውስጥ መሳተፍ የለብንም፤ ምክንያቱም ራሳችንን ካወቅን ደረጃችንን እንለያለን፤ ስሜታችንን የማንቆጣጠር ከኾነ የተሰማንን እና የመሰለንን ሁሉ እናወራለን፤ ለሰዎች ግድ ሲኖረን የምንናገረው መረጃ በእነርሱ ሕይወት ላይ ሊያስከትል ስለሚችለው ጉዳይ እና በሚሰሙት ነገር ሊመዝኑን እንደሚችሉ እንረዳለን፡፡ ስለዚህ ብዙ ከማውራት መርጦ መናገር፤ ከስሜታዊነት መቆጠብና ሰዎችን ማሳተፍ ወሳኝ ይመስለኛል፤ ብዙ የሚውቁ ሰዎች ከንግግር ይልቅ ተግባር ላይ ያተኩራሉ፤ መጀመሪያ ሌላው ሲናገር በጥሞና ይሰማሉ፣ የሚያደምጡት ለመመለስ ሳይኾን ነገሩን ለመረዳት ነው፤ መናገር እንኳ ቢኖርባቸው ንግግራቸው አጭርና ግልፅ እንዲሁም አይረሴ ነው፡፡

ለዚህ ዓለም በምሳሌነት የማነሳው እና ማሳያ የሚኾነው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፤ የዚህ ዓለም ፈጣሪና ሁሉን አዋቂ ኾኖ ሳለ ብዙ ሲያወራ አልተሰማም፡፡ እየሱስ ክርስቶስ ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጥም ኾነ መናገር ያለበትን ጉዳይ ሲናገር አጭር፣ ግልፅና በምሳሌ የተደገፈ በማድረግ ነበር። የዓለም ገዥ ኾኖ ሳለ በወቅቱ ዓለም የሾመቻቸው ሹመኞችን እንኳ ንቆ ወይንም የእነርሱን ንግግር አቋርጦ አድምጡኝ ያለበት ጊዜ የለም። ሁሉም ሰዎች ሹመኞችም ይሁኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች ተናግረው ከጨረሱ በኋላ እንጅ አቋርጦ ልናገር ያለበት ጊዜ የለም፡፡ ሰዎች ሃሳባቸውን ካልገለጡ ምን እንዳሰቡ እና እርሱ እየመለሰላቸው ያለው ነገር ምን እንደኾነ ሌላው ሰው ስለማይረዳው፡፡ ስለዚህ ለሁሉም ነገር አርአያችን ከኾነው ኢየሱስ ክርስቶስ መማር ወሳኝ ይመስለኛል፤ እርቀንም ሳንሔድ በሰፈራችን የተከበሩ የሚባሉት ሰዎች ብዙ የሚያወሩ ሳይኾን ሰዎች ሲናገሩ አድምጠው የሚያውቁትን ብቻ የሚመልሱ እና የሚናገሩ ናቸው። ከእንደነዚህ አይነት ምሳሌዎቻችን በመማር ራሳችንን ተደማጭና የተከበረ ሰው ማድረግ እንችላለን፡፡

እንቁራሪቶች በመንጋ ኾነው ቢጮሁ፤ ቁራ አሞራም በሚያምረው ድምፁ ሲጮህ ቢውል ማንም የሚያደምጣቸው የለም፤ የሚፈራቸውም  የሚያከብራቸውም  የለም፡፡ ብዙ ጊዜ ድምፁን የማንሰማው ከጮኸም የምንፈራውና የምናደንቀው አንበሳን ነው፤ ምክንያቱም ድምፁ ከስንት አንዴ የሚመጣ በመኾኑ ለመስማት እንጓጓለን ከመጣም እንደሚያጠፋን እናውቃለን፡፡ በመጮኽ የሚገኝ ክብር እና ዝና እንደሌለ ከተረዳን ሁሌም መጀመሪያ ማድመጥ ዋና ሥራችን መኾን ይገባዋል፤ አድምጠንም በይሉኝታ ሳይኾን የምናውቀውን ብቻ አጭር እና ግልጽ በኾነ መንገድ መናገርንና ሌሎችም ሃሳባቸውን እንዲገልጹ የማድረግ ልምዳችንን ማሳደግ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡

(አዲሱ ታደገኝ)

በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here