“የወርቅ ከተማ”

0
157

ዱባይ ከየተባበሩት የአረብ ኢምሬት ግዛቶች አንዷ ከተማ ናት። የሕዝብ ቁጥሯ ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን አካባቢ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 17 ከመቶ ብቻ የሀገሪቷ ዜጎች ናቸው። የተረፉት 83 ከመቶ ነዋሪዎች የውጭ ሀገር ጊዜያዊ ሠራተኞች ናቸው። አብዛኞቹም (ከግማሽ በላይ) ከሕንድ ሀገር የመጡ ሠራተኞች ናቸው።

በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ዱባይ ለቱሪዝም እና ለቅንጦት ትኩረት በመስጠት ትልቅ የአካባቢና ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል ሆነች። ኢኮኖሚዋ ከንግድ፣ ቱሪዝም፣ ከኤርላየንስ (አቪየሽን)፣ ከማይንቀሳቀስ ንብረት እና ከገንዘብ አገልግሎቶች በተገኘ ገቢ ላይ ጥገኛ ነው። የነዳጅ ዘይት ገቢ የከተማዋን ልማት ለማፋጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል። ይሁን እንጂ የነዳጅ ምርት በ2018 ለዱባይም ሆነ ለአጠቃላይ ለተባበሩት አረብ ኢምሬት አንድ በመቶ ያላነሰ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ዱባይ ዋና ዋና የንግድ፣ የፋይናንስ እና የሎጅስቲክስ የዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል ናት።  በመካከለኛው ምስራቅ እና በአፍሪካ ዋነኛ የፋይናንስ ማዕከል የሆነው ዱባይ ኢንተርናሽናል ፋይናንስ ሴንተር (DIFC) ከ2,500 በላይ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መኖሪያ ነው። ከተማዋ ከፍተኛ የሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ገበያ አላት። በ2024 ዓ.ም ብቻ 761 ቢሊዮን ብር የንግድ ልውውጥ ተደርጓል።

ዱባይ ውስጥ ከለንደን ቀጥሎ በአለም ላይ  ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ያሉ ሲሆን በአለም ላይ ረጅሙ (828 ሜትር) ከፍታ ያለው ቡርጅ ካሊፋ በከተማዋ ይገኛል። በፋይናንሺያል ሚስጥራዊነት፣ በዝቅተኛ ታክስ እና ውድ ሪል እስቴት ምክንያት ዱባይ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች፣ ወንጀለኞች፣ ሙሰኞች፣ የፖለቲካ ሰዎች እና የንግድ ሰዎች ገንዘብ ለማጭበርበር ወይም ለመደበቅ የሚጠቀሙባት መዳረሻ ናት።

ቱሪዝም የዱባይ ኢኮኖሚ ዋና ዘርፍ ሲሆን በ2023 እ.አ.አ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ 11 ነጥብ አምስት በመቶውን ይይዛል። ከተማዋ በቅንጦት ግብይት፣ በዘመናዊ ስነ ሕንጻ እና በመዝናኛ ትታወቃለች። በጠቅላላው በዓለም ላይ ትልቁ የገበያ ማዕከል የሆነው ዱባይ ሞል ከ100 ሚሊዮን በላይ ጎብኝዎችን በየዓመቱ ይቀበላል። እ.አ.አ. በ2023 ዱባይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሦስተኛዋ በብዛት የተጎበኘች ከተማ ነበረች።

ቱሪዝም የዱባይ መንግሥት ወደ ኢሚሬትስ የሚደረገውን የውጪ ገንዘብ ፍሰት ለመጠበቅ የነደፈው ስትራቴጂ ወሳኝ አካል ነው። የዱባይ የጎብኚ መስህብ በዋናነት በመገበያየት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ነገር ግን ሌሎች ጥንታዊ እና ዘመናዊ መስህቦችንም ይዟል፡፡ ከተማዋ እ.አ.አ  በ2016፣ 14 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የአዳር ጎብኚዎችን ያስተናገደች ሲሆን በ2020 ወደ 20 ሚሊዮን ጎብኚዎች ደርሷል።

ዱባይ “የመካከለኛው ምስራቅ የንግድ መገበያያ ዋና ከተማ” ተብላለች። በከተማው ውስጥ ብዙ የቡቲኮች እና የጌጣጌጥ መሸጫ መደብሮችም ይገኛሉ። በዲራ የሚገኘው የወርቅ መገበያያ ወደ 250 የሚጠጉ የወርቅ መሸጫ ሱቆች ስላሉት ዱባይ “የወርቅ ከተማ” ተብላ ትጠራለች።

በዱባይ ክሪክ የሚገኘው የዱባይ ክሪክ ፓርክ በዱባይ ቱሪዝም ውስጥ በጣም ዝነኛ የሆኑ የጎብኚ መስህቦችን እንደ ዶልፊናሪየም፣ የኬብል መኪና፣ የግመል ግልቢያ፣ የፈረስ ጋሪ እና ልዩ የአእዋፍ ትርኢቶችን ያሳያል። ዱባይ እንደ ሳፋ ፓርክ፣ ሙሽሪፍ ፓርክ እና ሃምሪያ ፓርክ ያሉ ሰፊ ፓርኮች አሏት።

በዱባይ ከሚገኙት በጣም ታዋቂ የባህር ዳርቻዎች መካከል ኡም ሱቄም፣ አል ማምዛር፣ ጄቢአር፣ ኪት ቢች፣ ጥቁር ቤተ መንግሥት እና የሮያል አይላንድ ናቸው። ማስተርካርድ ግሎባል የተባለ ተቋም  እ.አ.አ በ2019 ጎብኝዎች በዱባይ ከማንኛውም ሀገር የበለጠ ወጪ እንዳወጡ አረጋግጧል። አማካይ የቀን ወጪውም 553 ዶላር ሆኖ ተገኝቷል።

እ.አ.አ በጥቅምት 2019 ዱባይ የአልኮል መጠጥ የሚከለክሉ ህጎቿን ለመጀመሪያ ጊዜ ሰርዛለች። በዚህ ስር ጎብኚዎች በመንግሥት ቁጥጥር ስር ካሉ መደብሮች አልኮል እንዲገዙ ፈቅዳለች። ከዚህ ቀደም አልኮል የሚደርሰው ልዩ ፈቃድ ላላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ ነበር። ወሳኙ የፖሊሲ ለውጥ የመጣው የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ባጋጠማት ጊዜ ነው፡፡

ዱባይ የተለያዩ የሕንፃ ስታይል እና አወቃቀሮች ስብስብ አላት። በከተማ የአረቡን ዓለም ጥንታዊ እስላማዊ ኪነ ሕንጻ የሚያሳዩ ውብ ሕንጻዎች በብዛት ይገኛሉ፡፡ ሰማይ ጠቀስ እና ዘመናዊ እንዲሁም ዘመኑ በኪነ ሕንጻ ጥበብ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚያሳዩ ውድ እና ውብ ሕንጻዎች አሉ፡፡ የቡርጅ ካሊፋ ንድፍ የተገኘው በኢስላሚክ ኪነ-ህንፃ ውስጥ ከተካተቱት የስርዓተ-ጥለት አወጣጥ ስርዓቶችን በመጠቀም ሲሆን የሕንፃው ባለ ሦስት ጎንዮሽ አሻራ በዱባይ ክልል የሚበቅለው ሂሜኖካሊስ የተሰኘው የበረሃ አበባ አምሳልን መሠረት በማድረግ ነው።

የዱባይ ሚራክል ጋርደን በዓለም ላይ ትልቁ የአበባ (የአትክልት) ስፍራ ነው፡፡ የአትክልት ስፍራው ከ50 ሚሊዮን በላይ አበቦች ከ70 በላይ የአበባ እፅዋት ዝርያዎችን ያሳያል። የአትክልት ቦታው ከከተማው ማዘጋጃ ቤት የወጣ ቆሻሻ ውኃ ይጠቀማል፤ እፅዋትን ለማጠጣት የጠብታ መስኖ ዘዴን ይጠቀማል። በበጋው ወቅት ከግንቦት መጨረሻ እስከ መስከረም ባለው ጊዜ የአየር ሁኔታው በጣም ሞቃታማ ሲሆን በአማካኝ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ (104 ዲግሪ ፋራናይት) አካባቢ ሲደርስ የአትክልት ስፍራው ተዘግቶ ይቆያል።

ዱባይ ማሪና በፋርስ ባሕረ ሰላጤ የባህር ዳርቻ ሦስት ኪሎ ሜትር (2 ማይል) ዝርጋታ ላይ የተገነባ ሰው ሰራሽ የቦይ ከተማ ነው። ከተማው ባሕርን በመደልደል እና የብስ በማድረግ የተሠራ ነው፡፡ እ.አ.አ ከ2018 ጀምሮ 55,052 ሕዝብ ይኖርበታል። አጠቃላይ ልማቱ ሲጠናቀቅ ከ120,000 በላይ ሰዎችን በመኖሪያ ማማዎች እና ቪላዎች ያስተናግዳል።

የዱባይ ማሪና 50 ሚሊዮን ስኩዌር ጫማ ስፋት ሦስት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የውኃ ቦይ የልማቱ እምብርት የሆነ እና ዱባይ ማሪናን ቀዳሚ የመርከብ መዳረሻ የሚያደርገውን የባህር ዳርቻን ያካተተ ማዕከል አለው።

ጌት ዮር ጋይድ የተሰኘ ድረ ገጽ በዱባይ መታየት እና መደረግ አለባቸው ብሎ አሥር ቦታዎችን እና መዝናኛዎችን አስፍሯል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በበረሃ አሸዋ ላይ የሚደረግ የሞተር፣ መኪና እና የግመል ግልቢያን አንዱ አድርጎ አስቀምጧል፡፡ ይህ አስደሳች ክዋኔ ከአራት እስከ ሰባት ሰዓታት ሊፈጅ ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ በቅንጡ የሞተር ጀልባዎች የባሕር ላይ ጉዞ ነው፡፡ ከአንድ እስከ ሦስት ሰዓታትን የሚፈጀው የጀልባ ሽርሽር ምግብ እና መጠጥም የተሟላበት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ትላልቅ ቤተ መዘክሮች፣ የውኃ ፓርኮች፣ ቅንጡ ሪዞርቶች እና ሌሎች የጎብኚ መስህቦች አሉ፡፡  ሽርሽራችንን በዚሁ ቋጨን፤ ሰላም!

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here