የወሰደ መንገድ …

0
108

ጊዜ ሩጫው ለጉድ ነው፤ ተከተሉኝም አይል፤ ቆዩኝ ማለትም አልለመደበት። ብቻ ይከንፋል እንደ በራሪ፤ ይቀዝፋል እንደ አሳ አስጋሪ። ጊዜ በእሳት ሳይሆን በህይወትና በዕውነት የተፈተነ ወርቅ ነው።

አሁን ይች የትናንቷ አንድ ፍሬ ልጅ አይሻ ከመቸው አስራ አምስት ዓመት ሞላት!… አይ አይሻ! ገላዋን ለመታጠብ አስቸግራ የጎረቤቱን ደጅ በሙሉ በለቅሶ ስታካልል፣ ፀጉሯን አያቷ ታለም ያይኔ ሲጎነጉኗት ስትወራጭ፣ ትምህርት ቤት ለመሄድ ስሙኒ ስትጠይቅ እንደ ትናንት ትዝ ይለኛል።

እንደ ጠባቂ መልዓክ ከጎኗ ከማትለየው ጓደኛዋ ሰናይት ጋር ሆነው ቅጠል እየቆረጡ “ብር” ነው እያሉ ለጎረቤት፣ ምን ለጎረቤት ብቻ ለአላፊ አግዳሚው ሲያድሉ ትናንት የሆነ ያህል ትዝ ይለኛል። ቅጠል እንደ ብር በለጋስነት ሲያድሉ የነበሩ እነዚህ የትናንት ለጋ ልጆች ናቸው ዛሬ ኑሮ ከልጅነት ምናብ ውጭ ቢሆንባቸው፣ ሕይዎት የእቃቃ ጨዋታን ያህል ባይቀናላቸው፣ ጎደሏቸው እንደ አሮጌ ጣራ ሽንቁሩ በዝቶ ቢመራቸው ነው ልባቸው ከሐገር መውጣትን የተመኘው፤ እንዲያ ያለስስት የቦረቁበትን ቀዬ ጥለው  ዱር፣ ገደል በረሃውን አቋርጠው መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመፍለስ የቆረጡት።

“እንትፍ ይች ምራቅ ሳትደርቅ!…” ብለን ልከነው እናቶች በዳረጎት እኛ በፉትቦል ማስቲካና በደስታ ከረሜላ ያታለልነው ሳሚስ ቢሆን ከመቸው ጎረመሰና ነው ባህር አቋርጦ ለመሄድ የወጠነው። የዛሬን አያድርገውና ያኔ የምነዳትን አሮጌ ላዳ ታክሲ ጧት ከግቢ ሳስወጣ በኮልታፋ አንደበቱ “ወደ ኋላ…በቃ…በቃ ትንሽ ወደ ፊት” የሚለኝ ረዳቴ ነበር፤ ሳሚ። አይሻና ሰናይት ደግሞ ከበር ጠብቀው ካልሸኘኸን እያሉ እየተንጠላጠሉ ሲያስቸግሩኝ የሚያስፈራሩልኝ ጎረቤታችን የነበሩት መቶ አለቃ አስራደ ነበሩ።

ሰፈራችን ለአራዳ ቅርብ በመሆኑ ነብስ ያወቀ ልጅ ቤቱ አይውልም። ቢያገኝም ቢያጣም አራዳን ከቅዳሜ ገበያ ጀምሮ እስከ ፒያሳ በጣም ዙረት የተጠናወተው ከሆነም እስከ ብልኮ ያካልላል። እኔም በግሬ ሰፈር ሳካልል አደግኩ፤ በጉርምስናየም ላዳ ታክሲየን ይዤ ከአቦ እስከ አራዳ፣ ከአራዳ እስከ ፒያሳ፣ ከፒያሳ እስከ ማራኪ ከዛም እልፍ ሲል አዘዞን አካልላለሁ።

አራዳን እልፍ ብሎ ረጅሙን የፒስታ መንገድ አቋርጦ ወደ መንደራችን ጎራ ያለ ሰው ሁለት አነስተኛ ህንጻዎችን ይመለከታል። አንደኛው የነአይሻ ጎረቤት የነእማማ ገነት ሲሆን ሁለተኛው የነሳሚ ጎረቤት የታታ ዘይነብ ነው።

እንዴው ለተጨማሪ መረጃ ያክል “ማምሻም እድሜ ናት” እንዲሉ፣ የነጋሼ ቢተው በጎሰው የድሮ ህንጻና ምድር ቤትም የሰፈራችን አካል ነው። የነጋሼ ቢተው በጎሰው ህንጻ ‘ጠማማው ፎቅ’ የሚል ቅፅል ስምም አለው። ስሙን ያወጡለት ጥሩንባ ነፊው ጋሼ ምቾት ማንአዬ ናቸው ይባላል። ጋሼ ምቾት በጧቱ በጥሩምባ እየለፈፉ ይመጡ ይመጡና እኛ ሰፈር ሲደርሱ “እከሌ እከሌ ስላረፉ አቃብሩን ብለዋል ቤተሰቦች፣ ቀብሩ ——– ነው። ቤታቸው ከጠማማው ፎቅ ዝቅ ብሎ ነው” ይላሉ። ታዲያ የፎቁ ባለቤት ጋሼ ቢተውም የዋዛ ሰው አይደሉም። ለተሰነዘረባቸው ከባድ ሾርኔ ሲመልሱ፣ “ሰካራምና የቢራ ጠርሙስ አንድናቸው፤ ለምን ቢሉ ሁለቱም ሆድ እንጅ ጭንቅላት የለቸውማ! ምቀኛውን አፉን ለምለም ያድርግልኝ እንጅ እኔማ ሌላ ምን እላለሁ! ከአያት ቅድመ አያት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የጥሊያን ፎቅ ያለእድሜው ሊያስረጅ መከራ ያያል!” ይላሉ፤ በንዴት።

በነገራችን ላይ የኔም ታክሲ ስም አላት፤ ‘ከማን አንሼ’ ትባላለች። ታዲያ የመንደራችን ሁለቱ ፎቆች ጉምቱ የፍልሰት የማስታወቂያ ባለሙያዎች ናቸው ማለት ይቻላል። እነዚህን ሁለት ፎቆች አይቶ በሃሳብም፣ በሃላልም (በገሃድ) ወደ ጅዳ ያልከነፈ የለም።

ለኛ ሰፈር ሰው ስኬት ማለት ሁለቱ ፎቆች ናቸው። “ከሰሩ አይቀር እንደታታ ዘይነብ ልጅ ሶፊያ ነው እንጅ! ከወለዱ አይቀር እንደእነ እማማ ገነት ልጅ ማርዬ ነው እንጅ! ከፍ ዝቅ ብለው ሰርተው ይሄን ቤተ-መንግስት የመሰለ ፎቅ ለእናት አባት መስራት!” እየተባለ ሁለቱ ልጆች በሌሉበት ይሞካሻሉ። ይሄን የሰማ ወዳጅ ዘመድ ጎረቤት ያለውን ጥሪት እየሸጠ ጉዞ ወደ ጅዳ….  እኛ ሰፈር “…ጠንክረው ከሰሩ መርካቶም ጅዳ ነው” የሚለው የይሁኔ ሙዚቃ ለዘፋኙ ካለ ክብር ቢሰማም ከልብ አይደመጥም።

እንደለመድኩት ከማን አንሼ ላዳ ታክሲየን ይዠ ስንከራተት ፒያሳ አካባቢ አይሻን እና ሰናይትን አገኘኋቸውና ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ ያለ በረንዳ ላይ ተቀምጠን መጨዋወት ያዝን። በጨዋታ በጨዋታ መሃል የሳሚ ጉዳይ ተነሳና ያልጠበኩትን ነገር ሰማሁ።

“ሳሚሻ እኮ ደላላው አስቸኩሎት ከሄደ ሁለት ሳምንት ሞላው አልሰማህም እንዴ?” አለችኝ ሰናይት አተኩራ እያየችኝ። ለመሄድ እየተሰናዱ እንደሆነ ባውቅም ነገሩ “ምክርና ቡጢ ለሰጩ ቀላል ነው” ሆኖብኝ ዝምታን መርጬ ነበር፡፡ ነገር ግን እንዲህ በፍጥነት ይሆናል ብዬም አልጠበኩም ነበር። ሐዘኔታ ይሁን ትዝታ ብቻ ምን እንደሆነ ያልተረዳሁት ስሜት አንጀቴን አላወሰው።

“ያው እኛ ከፋም በጄ መንግስት ያየዘው ነገር ጥሩ ነው ብለን ፕሮሰስ እያደረግን ነው። ሳሚሻ ግን ደላላው ቶሎ ከሄደ ወደ አውሮፓ እንደሚያሻግረው ቃል ስለ ገባለት የቤታቸውን ካርታ አሲዞ ተበድሮ ከወጣ ይሄው ዛሬ ጁምአ ሁለት ሳምንት ሆነው። ያው እንግዲህ ኸይር ይግጠመው!” አለች አይሻ ዐይኖቿ እንባ እያቀረሩ። በሰማሁት ሁሉ አዝኘ በትካዜ ተውጬ ዝም አልኩ። ክፉ እንዳላወራ ሟርት እንዳይሆን ሰግቼ፣ ጥሩ እንዳልናገር ውሼት አስጠልቶኝ ፈራ ተባ እያልኩ ዝም አልኩ። ምንም እንኳ ፕሮሰሱ ቢዘገይም ውሻ በግ ነው ብሎ በሚሸጥ፣ ቅቤ ጠባሽ፣ አፈ ጮሌ ደላላ ተታለው በኢ-መደበኛ መንገድ እንዳይሄዱ የዕውቀቴን ያህል አስረድቸ የፀሐይዋን መዘቅዘቅ ተከትሎ እኛም ወደ አራዳ የቆብ አስጥልን መንገድ ይዘን ተንደረደርን።

ለመተኛት ብሞክርም አልተሳካልኝም፤ የሳሚ ነገር ሆዴ ገብቶ ያብሰለስለኛል። ከህገ-ወጥ ደላሎች መካከል አንዱም ታማኝ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ካየሁት ነገር አረጋግጫለሁ።

“መወለድ ቋንቋ ነው ይባል የለ? በገዛ ወገን ላይ እንዲህ መጨከን ለምን አስፈለገ?” አልኩ ለራሴ ድንገት ሳይታወቀኝ። ለመተኛት በሞከርኩ ቁጥር የሳሚ ምስል እየመጣ ይደቀንብኛል። “ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደር” እንዲሉ ሊነጋጋ ሲል ትንሽ የዕንቅልፍ ምህረት ወረደልኝ።

ከእንቅልፌ የነቃሁት እናቴ እና ታታ ዘይነብ ሲነጋገሩ ሰምቸ ነው። እናቴ ወደ ክፍሌ ገብታ ታታ ዘይነብ እንደሚፈልጉኝ ነገረችኝ። የቀኑን መርፈድ ያስተዋልኩት በመስኮት በኩል የፀሐዩን መቀተር አይቸ ነው። በፍጥነት ተነስቸ፣ ልብሴን ለባብሼ፣ ፊቴን ታጥቤ፣ እናቴ የሰራችልኝን ቂጣ ፍርፍር ቁርስም ምሳም አድርጌ ከማን አንሼ ላዳ ታክሲየ ጋር ከአነስተኛው ጊቢያችን ወጣን።

እንደው ይሄ ነው ብየ የምተርከው የስኬት ታሪክ ባይኖረኝም እዚህ የደረስኩት ሎተሪ ደርሶኝ እንዳይመስላችሁ ለግንዛቤያችሁ ተጠንቀቁ! አልጠነቀቅም የሚል ጉልቤ ካለ እንዳሻህ ብየ አልፈዋለሁ። “ስቆ መተውና አይቶ ማለፍ ሙዴ ነው!” የሚል ጥቅስ የማግኜቱን ያህል ስቆ መተውና አይቶ ማለፍ ሙዱ የሆነ ሰው ማ ቀላል እንዳይመስላችሁ። እጅና እግሬን ይዤ ከመዞር ወደ ሎተሪ ማዞር አደኩ፤ ናላየ በዙረት ስለዞረ ሊስትሮ ይዤ ተቀመጥኩ፤ ከዛ ጋሪ ገዝቼ የሰኞ ገበያን በርበሬ መጫን ማውረድ ጀመርኩ። ሰኞ ገበያ የሚያስነጥሰው ሰው ብዙ ነው። ስታስነጥስ ብትውል “ይማርህ” የሚል ሰው አታገኝም። እንዴውም በምትኩ “ለሃጫም ምን ትዝረበረባለህ? ቆፍጠን በል እንጅ!” ትባላለህ። አንድ ቀን እያስነጠስኩ ብቻየን ቁጭ ብየ የድምፃዊት የእጅጋየሁ ሽባባውን “እህህ እስከመቼ”  ሙዚቃ ስሰማ “አዎ እስከመቼ” ብየ ፎክሬ አሮጌ ላዳ ታክሲ ለመግዛት በቃሁ።

ከዚህ ሁሉ በፊት ግን ከሃገር ለመውጣት ያልሄድኩበት ደላላ አልነበረም ማለት ይቻላል። አንዱ ደላላ በአንድ ወር አውሮፖ እንደሚያሻግረኝ ሲምልልኝ አንዱ በሁለት ሳምንት ሌላው በሳምን እንዳይል ጨንቆት በአስር ቀን እንደሚያስገባኝ ሊያሳምነኝ ሲሞክር ብቻ ቃል ለመግባት የማይቸግራቸው ናቸው። በወቅቱ የምሰማቸው አንዳንድ መረጃወችና የናቴ ልመና ተጋግዘው አደብ ገዝቸ እንድቀመጥ ረዱኝ።

ለሰፈራችን ብርቅየ ወደሆነው የታታ ዘይነብ ፎቅ አመራሁ። ታታ ዘይነብ ልጃቸው ሶፊያ  ዘጠኝ ሰዓት ስለምትመጣ በሰዓቱ ደርሼ ከኤርፖርት ተቀብየ እንዳመጣት ነገሩኝ። እኔም ትዛዛቸውን ተቀብየ ወደ ፒያሳ ከነፍኩ። እንደወትሮው ሁሉ ከወዲያ ወዲህ ስባዝን ሳይታወቀኝ ዘጠኝ ሰዓት ደረሰ። በማራኪ አድርጌ ወደ አዘዞ ተምዘገዘኩ።

ሶፊያ በጣም ከመቅላቷ በቀር ይሄ ነው የሚባል የተጋነነ አካላዊ ለውጥ አይታይባትም። እሷን ቤት አድርሼ የተቀበልኩትን የሚጣፍጥ ዳቦ እየገመጥኩ ከማን አንሼ ታክሲየን ይዤ ወደ አቅሚቲ ግቢያችን አዘገምኩ።

አንዱ ሲሄድ ሌላው ሲመጣ…

ጊዜ መቼም መክነፍ አመሉ ነው። ሳሚ ከወጣ ወር አለፈው፤ ሶፊያም ከመጣች ሁለት ሳምንት ሆናት። አይሻና ሰናይትም ፕሮሰሳቸውን እንደ ስለት ልጅ አይን አይኑን ያዩታል። ጊዜ ሩጥ ቢሉት አይሮጥ፣ ቆይ ቢሉትም አይቆይ፣ ተመለስ ቢሉት አይመለስ! እንደልቡ፣ እንደፈቃዱ ነው።

በጧት የጋሼ ምቾት ጥሩምባ ሲያምባርቅ ምቾት ነስቶኝ ቶሎ ነቃሁ። የሚለው ነገር አልሰማህ ብሎኝ ጀሮየን ወደ መስኮቱ ቀሰርኩ። ዛሬ እንደተለመደው ‘ከጠማማው ፎቅ’ አላለም። ከታታ ዘይነብ ፎቅ ጎን ነው ያለው? ማመን አቃተኝ! ስካሩ ባይለቀው ነው ብዬ ሰበብ ላደርግ ፈለኩ:: ግን የሰማሁት እውነት ሆነ። የተሻለ ኑሮ ፍለጋ፣ ያልተሻለውን መንገድ ተከትለው የተንከራተቱ እግሮች ካሰቡት መድረስ አቃታቸው፤ ለካ! ክብር ያለው ሞት ለመሞትም ሃገር! ሃገር! ሃገር! ያስፈልጋል። ደራሲው እና ገጣሚው በዕውቀቱ ስዩም ወዶ አይደለም ለካ እንዲህ ያለው፤

“ከተመኙ ላይቀር ወንዝነት መመኘት

ሃገርን ሳይለቁ ሌላ ሃገር መገኘት፡፡”

(ደረጀ ደርበው)

በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here