የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት ምን እየተሠራ ነው?

0
237

የወባ በሽታ ስርጭት በከፍተኛ መጠን መጨመሩን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ እና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተደጋጋሚ አስታውቀዋል። የበሸታው ተጠቂዎች ቁጥርም በከፍተኛ መጠን መጨመሩን ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት። ስርጭቱ በከፍተኛ መጠን ከጨመረባቸው አካባቢዎች አንዷ ባሕር ዳር ከተማ ናት።የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው የወባ በሽታ ስርጭት ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው በ71 በመቶ ብልጫ አለው።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው አቶ ሙላቴ አስራደ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ በከፍተኛ ደረጃ የወባ በሽታ ተጠቂ እንደሆኑ ይናገራሉ። በአካባቢያቸው ያለው ውጋጅ ማጠራቀሚያ (ሴፍቲ ታንከር) ቶሎ እየሞላ በመፍሰሱ ምክንያት ውኃ ያቁራል። ይህም ለወባ በሽታ ስርጭት መስፋፋት ምክንያት እንደሆነ አንስተዋል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ዓለሙ አለባቸው በበኩላቸው በባሕር ዳር ሁሉም አካባቢ ውኃ ያቋሩ ተፋሰሶች መኖራቸውን ተናግረዋል። የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ታዲያ ወቅታዊ የማፅዳት (የዘመቻ) ሥራ ብቻ ሳይሆን የተቀናጀ ተከታታይ ሥራ መሠራት እንዳለበት አንስተዋል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዳስታወቀው የዘንድሮው የወባ በሽታ ስርጭት በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንዳሉት በክልሉ ከእሁድ እስከ እሁድ ባለው በአንድ ሳምንት ብቻ ከ70 ሺህ በላይ የወባ ሕሙማን መመዝገባቸውን አስታውቀዋል።
ክልሉ ካሉበት ውስብስብ ችግሮች የጤና ችግር አንዱ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ቀድሞ መከላከል ካልተቻለ ወደከፋ ውስብስብ የጤና ችግር ሊሸጋገር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። በመሆኑም የመከላከል ሥራው ላይ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል::
“በመከላከል ማስወገድ የሚቻልን በሽታ፣ ሰዎች ተጠቅተው በመድኃኒት ለመከላከል ሲገደድ እና ታማሚዎች ሲበዙ የመድኃኒት እጥረት እና ሞት ይከሰታል” ብለዋል::
አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ለከፍተኛ የወባ በሽታ ተዳርገው እንደነበር እና ለዚህም ግብጽን በአብነት ያነሱት አቶ በላይ የዓባይ ወንዝ ከደቡብ እስከ ሰሜን አቋርጦ የሚያልፍባት ግብጽ ያጋጠማትን ከፍተኛ የወባ በሽታ ስርጭት የተቆጣጠረችው የተቀናጀ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ በማከናዎን እንደሆነም ተናግረዋል።
“እንደኛ ሀገር ግን ወባን በተቀናጀ የቁጥጥር ሥራ በመከላከሉ ረገድ ገና ያልተሠራ ሥራ ነው፤ ሊቆጨንም ይገባል” ብለዋል። ስለዚህ የወባን በሽታ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የተቀናጀ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ማከናዎን እንደሚገባ በመጠቆም ለዚህ ማሳያም (ሌሎች አካባቢዎችም አርዓያነቱን እንዲከተሉ) በየሳምንቱ የሚደረግ የፅዳት ሥራ በባሕር ዳር ከተማ ስለመጀመሩ ተናግረዋል::
ባሕር ዳር ከኬፕታውን (ደቡብ አፍሪካ) እና ኪጋሊ (ሩዋንዳ) ቀጥሎ ለመኖሪያ ተስማሚ ከተማ መሆኗን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በሽታ ከተስፋፋ ግን ይህንን እውነታ የሚቀይር በመሆኑ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የወባ በሽታ አስተላላፊዋ የወባ ትንኝ የምትራባው ከአምስት እስከ ሰባት ቀን ስለሆነ “በሳምንት አንድ ጊዜ እንኳን አካባቢን የማፅዳጽት ሥራ ከተሠራ መከላከል ይቻላል” ብለዋል::
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንክር በ2022 እ.አ.አ 249 ሚሊዮን የወባ ሕሙማን እንደነበሩ አስታውሰዋል። 60 ሺህ 800 የሚሆኑት ደግሞ ከ85 ሀገራት በዚሁ በሽታ ሞተዋል:: ከዚህ ውስጥ ደግሞ የዕኛ ሀገር 23 በመቶ ድርሻ ይይዛል::
የወባ በሽታ ከጤና ችግርነት እና ህይወት ከመቅጠፍ ባለፈ በተጠቂ ሀገራት ምጣኔ ሀብታቸውን በአንድ ነጥብ ሦስት በመቶ ያሽቆለቁለዋል::
መከላከል ሳይቻል በበሽታ በመጠቃት ደግሞ በተለይ አፍሪካ ሀገራት የጤና ወጭአቸው 40 ከመቶ ያወጣሉ፤ አፍሪካ በየዓመቱ 12 ቢሊዮን ዶላር በበሽታው ምክንያት ታጣለች:: በሽታው ሁሉንም የሚያጠቃ ቢሆንም በዋናነት ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህፃናት፣ ነፍሰ ጡር እናቶች … በብዛት ይጠቃሉ::
በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ 75 በመቶ ለወባ አመቺ የሆነ ቦታ ነው ያለው:: በሽታውን በቅድመ መከላከል ተግባራት ማስቀረት እየተቻለ ይህንን ባለማድረግ ሕመሙ ሲከሰት ለሕክምና እናወጣለን::
ከሕክምና አልፎ ሞት ሲከሰት ከሚታጠው ህይወት ባሻገር ሌላ ወጭን አስከትሎ ስለሚመጣ ቅድመ መከላከል ሲሰራ ችግሩን በግማሽ ከመቀነስ አልፎ ከላይ ያነሳናቸውን ከፍተኛ ወጭዎች ሌላ የጤና ችግርን መፍቻነት ማዋል ይቻላል::
ህብረተሰቡ በየቦታው ያሉ የትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ለመቀነስ ግንዛቤውን ማሳደግ እና ከጠዋቱ አንድ እስከ ሦስት ሰዓት የማፅዳት ሥራን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ነው የገለፁት::
የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው በባሕር ዳር ከተማ እየታየ ያለው የወባ በሽታ መስፋፋት በእጅጉ አሳሳቢ ነው ብለዋል።
እንደ ሀገርም ወባ በከፍተኛ ኹኔታ ከሚከሰትባቸው 14 ከተሞች ባሕር ዳር አንዷ ናት ያሉት አቶ ጎሹ ችግሩን ለማስወገድ ልዩ ትኩረት በመስጠት በንቅናቄ እስከ ቀበሌ ድረስ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ይሠራል ብለዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በያሉበት ቀጣና ዘወትር ዓርብ ወጥተው የቁጥጥር ሥራ የሚያከናውኑ ይሆናል ነው ያሉት። በዚህም ባሕር ዳርን ለነዋሪዎች ምቹ እና ለጎብኚዎች ተመራጭ ለማድረግ እንደሚሠራ ነው አቶ ጎሹ የተናገሩት።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ እንደተናገሩት እንደ ሀገርም እንደ አማራ ክልልም የወባ በሽታ ሥርጭት እየጨመረ ነው:: በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያትም የበሽታው ስርጭት እየሰፋ ነው::
በሽታው አምራቹን ኃይል እያጠቃ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው ይም ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖው እንዳለው አክለዋል፤ ከዚህ ባለፈም ለህልፈተ ሕይወት የሚዳርግ በመሆኑ ሁሉም በትኩረት መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል::
ክልላዊ ጤና ጣቢያ መር ማሕበረሰብ አቀፍ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ተጀምሯል፤ ይህም የገንዘብ ወጪ የማይጠየቅበት ነው:: ይህም የመከላከል ሥራውን ውጤታማ ለማድግ ከፍተኛ አስታዋጽዖ እንዳለው አብራርተዋል::
በአጠቃላይ የቁጥጥር እና የመከላከል ሥራውን በሚፈለገው መንገድ ውጤታማ ለማድረግ ማሕበረሰብ አቀፍ ሥራን መሥራት ይገባል ተብሏል፤ እስከ ታህሳስ 30 ድረስ ያለው ወቅት ከፍተኛ የወባ ስርጭት የሚኖርበት መሆኑን በማንሳት ስርጭቱን ለመግታ ታዲያ የማሕበረሰብ አቀፍ የቁጥጥር ሥራን መሥራት እንደሚገባ ኃላፊው አሳስበዋል::
የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ መሥራት፣ የቅድመ መከላከል ተግባራትን በማከናወን ጤናን ማሻሻል፣ የመከላከል እና የማከም ሥራን ማከናወን እንደሚገባ አቶ አብዱልከሪም አሳስበዋል:: እነዚህን ተግባራትም በሥራ ቦታ፣ በኢንዱስትሪ፣ በመኖሪያ ቦታ፣ በትምህርት ቤቶች እና በሁሉም አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የወባ መራቢያ ቦታዎች የማከም፣ የማፋሰስ ሥራ በቋሚነት መሥራት እንደሚገባ በመተቖም ለዚህም ማሕበረሰቡ ሊያግዝ እንደሚገባ ተናግረዋል::
የጤና ተቋማት ሕክምና ከመስጠት ባለፈ በቂ መድኃኒት እንዲቀርብ ይደረጋል ያሉት ኃላፊው ማንኛውም አካል በቁጭት ሥራው የኔ ሥራ ነው ብሎ ሊሠራው እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here