የወባ በሽታ ስርጭት አሳሳቢ ሆኗል

0
169

በአማራ ክልል የተከሰተውን ከፍተኛ የወባ በሽታ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የተቀናጀ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ማከናወን እንደሚገባ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ።
በአማራ ክልል ያለው ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ያሳወቀው ኢንስቲትዩቱ ከባሕር ዳር ከተማ በአንድ ሳምንት ብቻ በተሠበሠበ መረጃ ከሦስት ሺህ በላይ ሕሙማን መገኘታቸውን ነው ያመላከተው።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው ሙላቴ አስራደ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ያለው ውጋጅ ማጠራቀሚያ (ሴፍቲ ታንከር) ቶሎ ቶሎ እየሞላ በመፍሰሱ ምክንያት የሚከማቸው ውኃ የወባ በሽታ ስርጭት ለመስፋፋቱ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ዓለሙ አለባቸው ደግሞ በየሰፈሩ ያሉ ተፋሰሶችን የማፅዳት ሥራው የዘመቻ መሆን እንደሌለበት ጠቁመዋል። በመሆኑም በቅንጅት እና በዘላቂነት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ “እንደ ክልል በተቀናጀ መንገድ የወባ በሽታን በመከላከል እና በመቆጣጥር ረገድ ገና ነን፤ ሊቆጨንም ይገባል” ብለዋል። ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት የወባ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የተቀናጀ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ማከናወን ይገባል። ለዚህ አብነት ባሕር ዳር ከተማን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በከተማዋ በየሳምንቱ የሚደረግ የፅዳት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እንደ ሀገር የወባ በሽታ በከፍተኛ ደረጃ ከሚከሰትባቸው 14 ከተሞች ባሕር ዳር አንዷ መሆኗን ገልጸዋል። በመሆኑም ስርጭቱን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ልዩ ትኩረት በመስጠት በንቅናቄ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።አቶ ጎሹ አክለውም የከተማዋ ነዋሪዎች በያሉበት ቀጣና ዘወትር ዓርብ ወጥተው የቁጥጥር ሥራ እንደሚያከናውኑ አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ በግብርና የተሰማራውን አምራች ኃይል የሚያጠቃው በሽታው ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተጽዕኖው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህም ባለፈ ለህልፈተ ሕይወት የሚዳርግ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው ሁሉም በትኩረት በመሥራት መከላከል እና መቆጣጠር ካልተቻለ ጉዳቱ ከፍተኛ ይሆናል ብለዋል።
በቅርቡ የተጀመረው ጤና ጣቢያ መር የማኅበረሰብ አቀፍ የቁጥጥር ሥራ የገንዘብ ወጪ ሳይደረግበት ውጤታማ ተግባርን ማከናወን የሚያስችል እንደሆነ ነው የገለፁት። በመሆኑም መሰል ተግባራትን አጠናክሮ በመቀጠል ስርጭቱን መከላከል እና መቆጣጠር እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዓ.ም ዕትም)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here