በአማራ ክልሉ የሚከሰቱ የኀብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ማሳለጫ ማዕከላት አስፈላጊው ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው በተጠናከረ ቅንጅት እየሠሩ እንደሚገኙ በክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክተር ፍቅርተ እስጢፋኖስ የ2017 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት አፈጻጸም በተገመገመበት ወቅት ተናግረዋል::
ዳይሬክተሯ እንደሚሉት ማሳለጫ ማዕከላቱ በክልሉ ውስጥ የሚከሰቱ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በትኩረት ለመከታተል፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመወያየት እና የተጠናከረ ድጋፍ ለማድረግ ኅብረተሰቡን ከከፋ አደጋ ለመጠበቅ እየሠራ ነው::
የጤና ልማት ምርምርን ከማሻሻል አንፃር የማረጋገጫ ጥናት ከተሠራላቸው ወረርሽኞች መካከል ኮሌራ፣ ኩፍኝ ፣ ወባ እና የልጅነት ልምሻ ተጠቃሽ ናቸው:: እነዚህን ወረርሽኞች ሙሉ በሙሉ በላብራቶሪ ማረጋገጥ እንደተቻለም ዳይሬክተሯ አረጋግጠዋል:: ከተከሰቱ እና ተቀባይነት ያለው የሞት ምጣኔ ከተቀመጠላቸው ሦስት ወረርሽኞች መካከል ኮሌራ፣ ኩፍኝ፣ እና አባሰንጋ/ከእንስሳ ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ/ ሲሆኑ እነዚህ በሽታዎች ከተከሰቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መካከል የሚቻልበት ሥራ በተለይም በኮሌራ መሰራት መቻሉ ዋና ዋናዎቹ ሥራዎች ናቸው::
በማዕከሉ የተለየ ምላሽ አሰጣጥ በሚያስፈልጋቸው በኮሌራ፣ በጦርነት ምክንያት በጊዜጣዊ ማቆያዎች በሚኖሩ ተፈናቃዮች፣ በሥርዓተ-ምግብ እና የምርምር ልማትን ለማሻሻል ምርምር እና ጥናት አድርጓል:: ይህን ተከትሎም በእናቶች፣ በሕፃናት እና በአፍላ ወጣቶች ጤና ተላላፊ እና የማይተላለፉ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር፣ የአመጋገብ እና የምግብ ደህንነት እንዲሁም የጤና ደህንነት እና የአእምሮ ጤና ትኩረት ያደረጉ አምስት የተጨመቁ የምርምር ውጤቶች፣ ሦስት የዳሰሳ ጥናት ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል::
በተያዘው ዓመት የግማሽ ዓመቱ የወባ በሽታ ስርጭት መረጃ እንደሚያመላክተው ደግሞ ከባለፈው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር 65 በመቶ መጨመሩን ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል:: የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስም በየደረጃው የሚገኙ የፌዴራል መንግሥት እና የአማራ ክልል መሪዎች በቁርጠኝነት እየሠሩ ይገኛሉ። ማኅበረሰቡም በሽታውን ለመቆጣጠር የበኩሉን አስተዋጾ ሲያደርግ መቆየቱን አንስተው ምስጋናም አቅርበዋል።
“የአርብ ጠንካራ እጆች የወባ ወረርሽኝን ይታገላሉ” በሚል መሪ መልዕክት በየሳምንቱ አርብ ከፍተኛ የመከላከል እና የፅዳት ሥራ እየተከናወነ እንደሆነም ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል:: በክልሉ ባሉ ሁሉም አካባቢዎችም የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝት ሲደረግ ቆይቷል፤ በተለይም 241 ቀበሌዎች በግማሽ በጀት ዓመቱ የተጠናከረ እና እንደ መልካም ተሞክሮ የሚጠቀስ ሥራ ሲከናወን መቆየቱን አስታውሰዋል:: ዳይሬክተሯ ኢንስቲትዩቱ በድርቅ እና መሰል አደጋዎች ለተጎዱ ሕጻናት እና ለሚያጠቡ እናቶች ለመድረስ አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱንም ተናግረዋል።
ስትራቴጂክ አጋርነትና ትብብርን ማጠናከር የናሙና ቅብብሎሽ ሥርዓትን ከማጠናከር አኳያ በኢንስቲትዩቱ ከተያዙ አዳዲስ የጤና ተቋማት ናሙና በመላክና ውጤት በመቀበል አገልግሎቱን እንዲጠቀሙ ተደርገዋል። ከተለያዩ የሪፈራል የላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎቶች መካከል የኤች አይቪ የቫይረሱ መጠን /ቫይራል ሎድ/ ምርመራ 89 በመቶ ተከናውኗል።
የውጭ የጥራት ቁጥጥር ትስስር ከተሠራላቸው አንድ ሺህ 84 የጤና ተቋማት ውስጥ በወባ 330 (30 ከመቶ) እና በቲቢ 221 (20 ከመቶ) ጤና ተቋማት እንዲሳተፉ ተደርጎል።
የጤና ግብዓት አቅርቦት እና የላቦራቶሪ መሣሪያዎች አሥተዳደር ሥርዓትን በማሻሻል ከ15 ከመቶ በታች፣ የላብራቶሪ አገልግሎት የተቋረጠባቸው የጤና ተቋማት መጠን ወደ 32 ከመቶ ዝቅ ማድረግ፣ ጥገና የተደረገላቸው የላብራቶሪ ማሽን በማሻሻል ፣ ለተመረጡ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች የመጠባበቂያ ግብዓት አቅርቦት መጠን እንዲኖራቸው ማድረግ ተችሏል::
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በበኩላቸው ለክልሉ በገጠሙ እና በተለያ ግጭቶች ምክንያት በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ላሉ ተፈናቃዮች ወረርሽኝ እንዳይከሰት የማድረግ ጠንካራ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል። ለዚህም በየጣቢያው ተንቀሳቃሽ የጤና ባለሙያዎች ቡድንን በመመደብ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን አረጋግጠዋል።
በወባ በሽታ ላይ በተለየ በዚህ ዓመት ከፍተኛ ችግር እንደ ነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለተግባራዊነቱም ከክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ጀምሮ እስከ ታች ባሉት መዋቅሮች በተደረገው ርብርብ እንደወረርሽኙ ስፋት ጉዳቱን መቀነስ መቻሉን ጠቁመዋል::
በቀጣይም የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል በጋራ መሥራት እንደሚገባም ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል። በተያዘው በጀት ዓመት አጋማሽ ከሦስት ሚሊዮን ለሚበልጡ የወባ ተጠርጣሪዎች በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ አንድ ሚሊዮን 315ሺህ 970 ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸው መረጋገጡን ዋና ዳይሬክተሩ አሳውቀዋል። ከነዚህ መካከልም 11 ነጥብ አራት በመቶ ሕጻናት እና ነፍሰ ጡሮች መሆናቸው ተመላክቷል።
የኅብረተሰብ ጤና ስጋቶች እና አደጋዎች የመከላከል እና የመቋቋም አቅም ከማሳደግ አኳያም የተሠራውን አገልግሎት አሰጣጥ በተመለከተ በኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥ ማሳለጫ ማዕከል በክስተት አስተዳደር ሥርዓት በአግባቡ መምራት መቻሉን ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል::
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ዘንድሮ ከሌላው በተለየ የወባ በሽታ በክልሉ ከፍተኛ የኅብረሰተብ ጤና ችግር ሆኖ ቆይቷል:: ለዚህም በየደረጃው ባሉ ጤና ተቋማት የላቦራቶሪ ምርመራ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ሥራን በአግባቡ መሥራት ተችሏል:: በጥር ወር መግቢያ ሳምንት ብቻ እስከ 29 ሺህ የወባ ሕሙማን በጤና ተቋማት ታክመዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ካሁን ቀደም የወባ በሽታን ሪፖርት አድርገው የማያውቁ ቀበሌዎች አሁን ላይ ሪፖርት ማድረግ መጀመራቸው የስርጭቱን ስፋት እንደሚያሳይ አመላካች ነው::
ከያዝነው ወር አጋማሽ ጀምሮም ከ500 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የወባ በሽታ ምርመራ እና የሕክምና ንቅናቄ ዘመቻ በጤና ባለሙያዎች ቤት ለቤት ይካሄዳል:: በዘመቻውም ባለሙያዎች የወባ በሽታ ምልክት ያለባቸውን ሰዎች በፈጣን መሣሪያ በመመርመር ያክማሉ ብለዋል።
ወባ የኅብረተሰቡ ችግር እንዳይሆንም በዘመቻው ሁሉም በትብብር መሥራት ይጠበቅበታል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የመድኃኒት እና የገንዘብ አቅርቦት ወደ ወረዳዎች መድረሱን ጠቁመዋል።
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም