የወተት ማዕዳችን ከቀንድ ብዛት እንዲወጣ …

0
275

በቀንድ ከብት ብዛት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ዐሥረኛ ደረጃ ተቀምጣለች፤ ይሁን እንጂ ከዘርፉ የምታገኘው ውጤት ዝቅተኛ ነው:: የእንስሳት ተዋጽኦ ፍላጎት በፍጥነት እየጨመረ ቢሆንም ከሀገር ውስጥ የምርት እድገቱ ጋር የማይመጣጠን እንደሆነ ተመላክቷል::  ለአብነትም የወተት ምርቷ ዝቅተኛ እንደሆነ ይነገራል::

ከአማራ ክልል እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ የእንስሳት እርባታ ግብርና ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ካለው አስተዋፅኦ 47 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል::      ይሁን እንጂ የሀገራችን የእንስሳት ሀብት የምርታማነት ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ ለምግብ ዋስትናና ለምጣኔ ሀብት ዕድገት የሚጠበቀውን ያህል አስተዋፅኦ ማበርከት አልቻለም::

ከጽ/ቤቱ የተገኘው መረጃ አክሎም በኢትዮጵያ የወተት ምርት ከተጠቃሚዎች ፍላጎት አንፃር በየዓመቱ 22 ቢሊዮን ሊትር መመረት ይኖርበታል (ያስፈልግ ነበር) ይላል፤ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የሚመረተው ከ7 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ሊትር አይበልጥም::

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከ10 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ (6 መቶ ሚሊዮን ብር ገደማ) የወተት ተዋጽኦዎችን በየዓመቱ ከውጭ እንደምታስገባ መረጃው ይጠቁማል:: በቀንድ ከብት ብዛት በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ ለሆነች ሀገር ደግሞ ያላትን ሀብት አለመጠቀሟን ያሳያል::

የዓለም ጤና ድርጅት አንድ ሰው በአማካኝ በዓመት 200 ሊትር ወተት መጠጣት እንዳለበት ይመክራል:: በኢትዮጵያ ግን በአማካኝ አንድ ሰው 19 ሊትር ወተት ብቻ እንደሚጠጣ መረጃዎች ይጠቁማሉ::

አንድ ህፃን ተወልዶ ከአየር ቀጥሎ የሕይወቱ ቀጣይነት የሚረጋገጠው ከእናቱ ወይም በሌላ መንገድ በሚያገኘው ወተት ነው:: ወተት ሁሉንም የምግብ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ ስለያዘ ለሰው ልጅ የተሟላ ጤንነትን በማጎናፀፍ የሥርዓተ ምግብ ችግርን ለመፍታት የላቀ አስተዋፅኦ ያበረክታል:: ከዚህ በተጨማሪም ለአምራቹ የገቢ ምንጭ ነው፤ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የወተት ተዋፅኦዎችን በመተካትም የውጭ ምንዛሪ ወጪን ያስቀራል::

ስታትስታ (statista) የተባለ የመረጃ ምንጭ እንዳስነበበው ፊንላንድ 430 ሊትር ወተት በዓመት በነፍስ ወከፍ በመጠቀም በዓለም በአንደኛነት ደረጃ ተቀምጣለች:: ሕዝቧንም ወተት አፍቃሪ ሲል ነው የገለጻት:: የጎረቤት ሀገር ኬንያ ነፍስ ወከፍ የወተት ፍጆታዋ 120 ሊትር ነው::

አቶ ደመላሽ አይችሌ በአማራ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ጽ/ቤት  የእንስሳት ምርት እና ተዋጽኦ ባለሙያ ናቸው፤ ባለሙያው እንደተናገሩት የመኖ ጥራት እና አቅርቦት ችግር እንዲሁም የጤና እንክብካቤ ጉድለት ለወተት ምርታማነት ዝቅተኛ መሆን በምክንያትነት አንስተዋል::

ከአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት ዓመታዊ መጽሔት ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው፣ መኖን በመጠንና በጥራት አለማቅረብ፣ ኋላቀር አመጋገብና የእንስሳት አያያዝ (አረባብ)፣ በቂ ሕክምና አለመኖር፣ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች እጥረት እንዲሁም የገበያ መሠረተ ልማት አለመዳበር የእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው::

የገበያ እሴት ሰንሰለቱም አለማደጉን በማንሳት፣ ዘርፉን ለማዘመን ብዙ ርቀት መሄድ እንደሚጠይቅ አቶ ደመላሽ ይናገራሉ::  እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የወተት ምርትን በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ የእንስሳት ጤና፣ የተሻሻለ ዝርያና መኖ ላይ መሥራት ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው:: ወተት ከማለብ ጀምሮ ለተጠቃሚው እስከሚደርስበት ድረስ ልዩ ጥንቃቄ የሚፈልግም ነው:: ጥራትና ደህንነቱ የተጠበቀ ወተት ለሕብረተሰቡ ለማቅረብ ደግሞ የአምራቹን ግንዛቤ ማሳደግ ወሳኝ ነው::

በሌላ በኩል የወተት ላሞች እንደ ብዛታቸው ወተት የሚሰጡ አይደሉም፤ ለዚህ መሠረታዊ ምክንያቶች ደግሞ ከላይ የተዘረዘሩት (መኖ፣ ዝርያ፣ ጤና ክብካቤ፣ …) ጉዳዮች ናቸው:: በመሆኑም የወተት ኢንዱስትሪው በሚጠበቀው ደረጃ ዕድገት አለማሳየቱንና ግብይቱ ጤናማ አለመሆኑን ተናግረዋል፤ እነዚህም በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸዉን ጠቁመዋል::

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የእንስሳት ተዋፅኦ ባለሙያ አቶ ሲሳይ ተረፈ  በከተማ አስተዳደሩ አራት የወተት ልማት ማሕበራት እንዳሉ ነግረውናል:: ባለሙያው እንዳሉት በከተማ አስተዳደሩ 15 ሺህ የሚታለቡ ላሞች አሉ፤ ከነዚህም ሦስት ሺህ ያህሉ የፈረንጅ (የተሻሻሉ) እና 12 ሺህ ደግሞ የሀበሻ ላሞች ናቸው::

የወተት ጥራትና መጠን እንዲጨምር፣ ዝርያ እንዲሻሻል፣ የጤና እንክብካቤ፣ የአያያዝ እና ሌሎች ጉዳዮችን እንዲሻሻሉ ከሚመለከታቸው ጋር እየተሠራ እንደሚገኝ አቶ ሲሳይ አመላክተዋል:: የወተት ምርቶች  በቢሮዎች፣ በክፍለ ከተማዎችና በቀበሌዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል:: ይህ ሲሆን ደግሞ የገበያ ትስስር ችግርን ለመፍታት በትኩረት መሠራት እዳለበት ጠቁመዋል::

አቶ ሲሳይ እንዳሉት ሮዳስ የተባለ የሳር ዝርያ በዓመት ሦስት ጊዜ ታጭዶ ለመኖ አገልግሎት ይውላል:: አራተኛው ደግሞ ለምርት  የሚያገለግል በመሆኑ የተሻሻሉ የመኖ ሳር ዝርያዎችን መጠቀም ይገባል፤ ይህን እና መሰል ተግባራትን በማከናወንም የወተት ልማትን ማሳደግ ይገባል ብለዋል:: ለዚህም የሚመለከተው ሁሉ በትኩረት እንዲሠራና የድርሻው እንዲወጣ ጠይቀዋል::

ባለሙያዉ እንዳሉት በዘርፉ 70 በመቶ የሚሆነው ወጭ ለምግብ (ለመኖ) የሚውል ነው፤ በመሆኑም ለመኖ ልማት (ሌሎችም እንደተጠበቁ ሆነው) ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል::

ተገቢ የመመገቢያ ገንዳ አለማዘጋጀት መኖ እንዲባክን ያደርጋል፣ ላልተገባ ወጭ ይዳርጋል፣ ጉልበት ያላቸው እንስሳት (ላሞች) ብቻ ተጋፍትው እንዲገቡ ያደርጋል:: ይህ እንዳይሆን ደግሞ  መመገቢያ ገንዳው በአግባቡ ተዘጋጅቶ መመገብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል::

የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እንደ ከተማም ሆነ እንደ ክልል ተቋቁሞ የሚፈጠሩ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸውም አቶ ሲሳይ ተናግረዋል:: በመንገድ መዘጋት ምክንያት ወደ አዲስ አበባ የሚላክ ወተት ብልሽት እየገጠመው ነው፤ ከፍተኛ ኪሳራም (ብክነት) እያስከተለ ነው:: ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄው ደግሞ ፋብሪካዎችን ማቋቋምና አማራጮችን መጠቀም ነው::

የወተት ምርትን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ጽ/ቤት የእንስሳት ሃብት ልማት ባለሙያው ደመላሽ አይችሌ ተናግረዋል:: ባለፈው በጀት ዓመት (2015 ዓ.ም) በሀገር  ደረጃ ሰባት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ሊትር ወተት ተመርቷል:: በአማራ ክልል ደግሞ አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ሊትር ወተት መመረቱን አመላክተዋል:: ይህም ሀገሪቱ ከምታመርተው 23 በመቶ ክልሉ ሸፍኗል ማለት ነው::

የወተት ላሞችን የማዳቀል፣ የተሻሻሉና የተመጣጠነ የመኖ ዝርያዎችን ማሻሻልና ቅድመ መከላከል እንዲሁም የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እየተረደገ ነው  ብለዋል:: ባለሙያው አክለውም ወጣቶች በወተት ሀብት ልማት እንዲሰማሩ፣ የገበያ ትስስርም እንዲፈጠር አበረታች ጅምሮች መኖራቸውን  ጠቁመዋል::

በአማራ ክልል ካሁን በፊት በቀን ከ230 ሺህ እስከ 250 ሺህ  ሊትር ወተት ወደ አዲስ አበባ ይላክ ነበር፤ አሁን ላይ ግን በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት የመንገድ መዘጋት በመኖሩ በሚፈለገው ደረጃ መላክ አለመቻሉን ከጽ/ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል:: ጥሬ ወተቱን ወደ ወተት ተዋፅኦ እንዲቀይሩ እና በአቅራቢያችው ለሚገኙ ተቋማት እንዲያቀርቡ በማድረግ ጊዜያዊ መፍትሔ መወሰዱን አክለዋል:: ዘላቂው መፍትሔ ግን በክልሉ ፋብሪካዎችን መገንባትና ሥራ ማስጀመር እንደሆነ አስገንዝበዋል::

በዚህ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች በቂ የቦታ አቅርቦት በመስጠት፣ በበጀት በመደገፍና አስተማማኝ ሰላም በማስፈን ዘርፉን ማጠናከር ይገባል ብለዋል::

በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ሕክምና ለመስጠት፣ ዝርያዎችን ለማሻሻል እንዲሁም የተመጣጠነ መኖ ከፋብሪካዎች ወደ አርቢዎች ለማድረስ በባለሙያዎች ላይ እንቅፋት ፈጥሯል:: የሚመረተው ወተትም ለማዕከላዊ  ገበያ እንዳይቀርብ በማድረግ በዘርፉ ላይ የከፋ ተፅኖ አሳድሯል። የወተት ብክነትን እያስከተለም ነው።

በክልሉ የተወሰኑ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅም በወተት ምርት ላይ ጫና አሳድሯል፤ የበርካታ ሺህ እንስሳትን ሕይወትም ቀጥፏል:: የእንስሳት መኖ ዋጋ መናር በዘርፉ ለተሰማሩ ዜጎች ፈተና መሆኑም ተገልጿል::

በቀጣይ የመኖ፣ የዝርያ ማሻሻል፣ የጤና አገልግሎት ማስፋፋት፣ የገበያ ትስስርን ማጠናከር፣ ማሕበራትን ማደራጀትና መከታተል፣ ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ማድረግ፣ የግንዛቤ ፈጠራ እንዲሁም ዘመናዊ የእንስሳት አያያዝ እንዲኖር በትኩረት የሚሠራባቸው ተግባራት መሆናቸውን አብራርተዋል::

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here