የወንጀል ቅጣት

0
340

በፍትሕ አምድ በዚህ ሳምንት የምናስነብባችሁ ስለ ወንጀል ምንነት እና እሱን ተከትሎ ስለሚመጣው ቅጣት ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ መረጃ የሚሰጡን ደግሞ በፍትሕ ሚኒስቴር አማራ ክልል ቅርንጫፍ ምክትል ረዳት ጠቅላይ አቃቢ ሕግ አቶ ስመኘው መንበሩ ናቸው፡፡፡

ምክትል ረዳት ጠቅላይ አቃቢሕግ አቶ ስመኘው እንደሚገልፁት የወንጀል ቅጣት ማለት አንድ ሰው በወንጀል ተጠርጥሮ ክስ ከተመሰረተበት በኋላ ድርጊቱን መፈፀሙ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ የሚወሰን የእስራት፣ የግዴታ ሥራ ፣ የገንዘብ መቀጮ ወይም የሞት ቅጣት  ነው፡፡

አንድ ሰው የፈጸመው ተግባር ወንጀል ነው የሚባለው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23 ንኡስ አንቀፅ ሁለት በግልጽ እንደተደነገገው ድርጊቱ የተፈጸመው ታስቦ ወይም በቸልተኝነት ሲሆን እና ይህ ድርጊትም በወንጀል ሕጉ ልዩ ክፍል ወይም በአዋጅ ወንጀል ነው ተብሎ የተደነገገ ከሆነ  ነው፡፡ ይህም ማለት አንድን ድርጊት ወንጀል ነው ለማለት ሞራላዊ ፣  ድርጊት እና  ሕጋዊ ፍሬ ነገሮች በአንድ ላይ ተሟልተው ሲገኙ ብቻ ነው፡፡

በሕጉ እንደተጠቀሰው ሞራላዊ ማለት ድርጊት ፈጻሚው ወንጀሉን ሲፈጽም የነበረውን ሃሳብ  ለማለት ነው፡፡ ይህም ሰውየው ድርጊቱን አስቦ አልያም በቸልተኝነት  መፈጸሙን ለማረጋገጥ የሚረዳ ሁኔታ ነው፡፡ ድርጊት ማለት ደግሞ የተከናወነውን ሂደት ለማመላከት ነው፡፡

ሕጋዊ ፍሬ ነገር ማለት አንድን ወንጀል ለማቋቋም አስፈላጊው ነው፡፡ ይህም ማለት አንድ ድርጊት ወንጀል ነው ለማለት ወንጀል  ፈጻሚው ሃሳቡን እና ድርጊቱን ማከናወን ብቻ ሳይሆን ድርጊቱ በሕግ በግልጽ ወንጀል ነው ተብሎ ተደንግጎ መገኘት ያለበት መሆኑን ለማመላከት ነው፡፡ እነዚህ ሦስት ነገሮች በተሟሉ ጊዜ አንድን ድርጊት ወንጀል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህን ተከትሎ አንድ የተፈጸመ ድርጊት ወንጀል መሆኑ እና ወንጀሉን የፈጸመው ሰው ከተረጋገጠ ቀጥሎ የሚመጣው ወንጀል የፈጸመው አካል ምን ሊቀጣ ይገባዋል? የሚለው ነው፡፡

አቶ ስመኘው እንዳሉት ወንጀል ፈጻሚው ሕጋዊ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት በሆነ ጊዜ የሚቀጣው ምንጊዜም ገንዘብ  ነው፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 90 ንኡስ ቁጥር ሦስት  ወንጀሉን የፈጸመው ሰው  እንደ ወንጀሉ ክብደት እና ቅለት እንዲሁም እንደ ወንጀሉ አፈጻፀም አደገኛነት እና ከባህሪ አኳያ ታይቶ ከግዴታ ሥራ/የሥራ ቅጣት/ እስከ ሞት ባለው አንዱን ወይም የተደራረበ ቅጣት ሊቀጣ ይችላል ማለት ነው፡፡

የወንጀል ሕግ እና ቅጣት

የወንጀል ሕግ ዓላማ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ አንድ የመጀመሪያው አንቀጽ በግልጽ እንደተቀመጠው የሀገሪቱን መንግሥት የነዋሪዎቹን ሰላም፣ ደህንነት፣ ሥርዓት፣ መብት እና ጥቅም መጠበቅ እና ማረጋገጥ ነው፡፡  ግቡም በዚሁ አንቀጽ ሁለተኛው አንቀጽ በግልጽ እንደተመለከተው የወንጀል ሕግ ዓላማ ወንጀል እንዳይፈጸም መከላከል ነው፡፡

ይህንንም ለማረጋገጥ ስለወንጀሎች እና ቅጣታቸው በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት፤ ማስጠንቀቂያው በቂ ባልሆነበት ጊዜ ደግሞ ወንጀል ፈጻሚዎቹ ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈጸም እንዲቆጠቡ፣ ለሌሎች ማስጠንቀቂያ እንዲሆኑ እና  ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈጽሙ ርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው ማድረግ ነው፡፡

        የወንጀል ቅጣቶች

ምክትል ረዳት ጠቅላይ አቃቢሕግ አቶ ስመኘው የወንጀል ቅጣቶች በዋነኝነት አራት ዓይነት ናቸው፡፡ እነዚህም የገንዘብ፣ የግዴታ ሥራ፣ ነጻነትን የሚያሳጡ  እና የሞት  ናቸው፡፡

በወንጀል ሕግ አንቀጽ 90 ንኡስ አንቀፅ አንድ የገንዘብ መቀጮ መነሻው  10 ብር ሲሆን ጣሪያው ደግሞ  10 ሺህ ብር ነው፡፡ ነገር ግን ጥፋተኛው የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት በሚሆንበት ጊዜ  ዝቅተኛው ቅጣት 100 ብር ሲሆን ጣሪያው 500 ሺህ ነው፡፡

ሌላው የቅጣት ዓይነት የግዴታ ሥራ ነው፡፡ ይህ ቅጣትም ዝቅተኛው የአንድ ቀን የግዴታ ሥራ ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ የስድስት ወር የግዴታ ሥራ መሆኑ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 103 ንኡስ አንቀፅ አንድ ላይ ሰፍሯል፡፡

የወንጀል ሕግ አንቀጽ 106 ንኡስ አንቀፅ አንድ ቀላል እስራት የሚቀጣው በድርጊቱ ክብደት ሳይሆን መካከለኛውን ወንጀል ባደረገ እና ጥፋተኛውም በህብረተሰቡ እጅግ አደገኛ መስሎ ባልታየ ጊዜ የሚወሰን ቅጣት ነው፡፡ ቅጣቱም ዝቅተኛው የአስር ቀን ከፍተኛው ደግሞ የሦስት ዓመት እስራት ነው፡፡ ነገር ግን በልዩ ሕጉ በግልጽ በተደነገገ ጊዜ ወይም ተደራራቢ ቀላል እስራት የሚያስቀጡ ወንጀሎች በተፈጸሙ ጊዜ የቀላል እስራት ጣሪያው አምስት ዓመት ሊደርስ ይችላል፡፡

በወንጀል ሕግ አንቀጽ 108 አንቀጽ 106 ንኡስ አንቀፅ አንድ ሌላው ነጻነትን የሚያሳጣ ድርጊት የፈፀመ የሚወሰንበት ቅጣት ጽኑ እስራት እንደሆነ አስቀምቷል፡፡  የጽኑ እስራት ቅጣት የሚወሰነውም ከባድ ወንጀል በፈፀሙ በተለይም ለህብረተሰቡ አደገኛ በሆኑ ወንጀለኞች ላይ ነው፡፡ ይህ ቅጣት ዝቅተኛው አንድ ዓመት ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 25 ዓመት ብሎም በልዩ ሕጉ ተደንግጎ ሲገኝ የእድሜ ልክ እስራትንም የሚያካትት ነው፡፡

የመጨረሻው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 117 ንኡስ አንቀፅ አንድ የተቀመጠው ትልቁ ቅጣት ሞት ነው፡፡  የሞት ቅጣት የሚወሰነው ወንጀሉ ፍጻሜ ያገኘ ሆኖ እጅግ በጣም ከባድ እና ወንጀለኛውም በተለይ አደገኛ ሲሆን እንዲሁም ለወንጀለኛው ቅጣትን የሚያቀልለት ምክንያት በታጣ ጊዜ እና ወንጀለኛው ወንጀሉን በፈጸመበት ጊዜ እድሜው ቢያንስ አስራ አምስት ዓመት የሞላ ሲሆን ብቻ ነው፡፡  የሞት ቅጣት በሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር ፍርዱ ካልጸና በቀር ተፈጻሚ ሊሆን አይችልም፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 117 ንኡስ አንቀፅ  ሁለት እንዲሁም በይቅርታ ወይም በምሕረት ያልተሻረ ወይም ያልተለወጠ መሆኑ አስቀድሞ ከመመርመሩ እና ከመታወቁ በፊት ተፈጻሚነት የለውም፡፡

አንድ ሰው ላጠፋው የወንጀል ድርጊት እንደድርጊቱ ክብደት እና ቅለት እንዲሁም የአጥፊው አደገኝነት መሰረት ተደርጎ ከላይ ከተዘረዘሩት ቅጣቶች አንዱ ወይም ተደራርበው በአንድ ላይ ሊቀጣባቸው ይችላል ማለት ነው፡፡

ገደብ

ገደብ ማለት አንድ የተሰጠ የጥፋተኝነት ፍርድ ወይም የተሰጠ ቅጣት ለጊዜው ከመፈጸም ታግዶ እንዲቆይ በፍርድ ቤት የሚሰጥ ውሳኔ ነው፡፡ በመሰረቱ ቅጣት የሚወሰነው በዋነኝነት አጥፊውን ለማረም እና ሌላውንም ለማስተማር ነው፡፡ ነገር ግን  ጥፋተኛው ቅጣቱን በእስር ሆኖ ከሚፈጽም ይልቅ አንድ ብርቱ ፈተና ቢሰጠው የጸባይ መሻሻል ያደርጋል፤ መልካም ውጤትም ያመጣል ብሎ ፍርድ ቤት በሚያምንበት ጊዜ  የተወሰነው ቅጣት እንዲገደብ ሊወስን ይችላል፡፡

ተከሳሹ ጥፋተኛ ከተባለ በኋላ ቅጣት ሳይወሰን የሚሰጥ የገደብ አይነት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 191 እንደተገለጸው ወንጀለኛው በፊት ያልተቀጣ ከሆነ፣ ጠባዩም አደገኛነት ከሌለው፣ የሚታመንበት  እና ጥፋቱ በመቀጮ፣ በግዴታ ሥራ ወይም ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ከሆነ ብቻ ነው፡፡

ሌላው ዓይነት ገደብ የሚሰጠው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 192 በግልጽ እንደተደነገገው ጥፋተኛው አስቀድሞ የተፈረደበት ቢሆንም ባይሆንም ቅጣቱ ከመፈጸሙ በፊት ለተወሰነ ጊዜ ታግዶለት ሁለተኛ ጥፋት ከመፈፀም እና ስለጸባዩም መሻሻል አንድ ጽኑ ማስጠንቀቂ ብቻ የሚበቃ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ካመነበት  አፈጻጸም ታግዶ እንዲቆይ ሊወስን ይችላል ማለት ነው፡፡

ገደብ የሚሻረው ደግሞ የመጀመሪያው ወንጀለኛው ቅጣቱ ታግዶለት ለፈተና በተለቀቀበት ጊዜ ውስጥ አስቦ አንድን ወንጀል ያደረገ እንደሆነ ነው፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ የቅጣት አፈጻጸሙ በታገደለት ጉዳይ የተሰጠው የፈተና ጊዜ መልካም ፍሬ የሚያስገኝ አለመሆኑን ፍርድ ቤቱ ሲረዳ የተሰጠው እግድ ሊሻር እንደሚችል የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 194 ንኡስ አንቀፅ ሁለት በግልጽ ይደነግጋል፡፡

የገደብ የፈተና ጊዜ የሚሰጠው ከሁለት ዓመት የሚያንስ አይሆንም፡፡  ከአምስት ዓመት የሚበልጥ መሆን እንደሌለበት የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 196 ንኡስ አንቀፅ ሁለት በግልጽ ይደነግጋል፡፡ ይኸው አንቀጽ የገደብ ጊዜ የሚሰላው (የሚታሰበው) የመጨረሻው ፍርድ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ እንደሆነ በግልጽ ይደነግጋል፡፡

አመክሮ

አንድን በወንጀል የተቀጣን ሰው በአመክሮ መፍታት ማለት የተቀጣው ሰው የተወሰነበት የእስራት የጊዜ ገደብ ሳይደርስ የእስራት ጊዜው ከማለቁ አስቀድሞ ከእስር መፍታት ማለት ነው፡፡ በአመክሮ በተወሰነ ገደብ መፍታት የተቀጭውን ጠባይ ማሳያ እና ወደ ደንበኛው ማህበራዊ ኑሮ መመለሻ ሆኖ ይቆጠራል፡፡ ተቀጭው ለዚሁ ተገቢ ካልሆነ እና በተወሰነ ገደብ መፈታቱ ተፈላጊውን ውጤት የሚያስገኝ መሆኑ ካልታመነበት በቀር ሊፈቀድለት አይችልም፡፡ አንድን ተቀጪ በአመክሮ ለመለቀቅ ማሟለት ያለባቸው ሁኔታወች አሉ፡፡

የመጀመሪያው አንድን ተቀጭ በአመክሮ ለመለቀቅ ከተወሰነበት የእስራት ቅጣት  ጊዜ ከሦስት እጅ ሁለቱን እጅ ወይም ፍርዱ የእድሜ ልክ እስራት ሲሆን ሃያ ዓመት በፈጸመ ጊዜ ነው፡፡ ሌላው እና ሁለተኛው ሁኔታ አስፈላጊ የሆነውን ነጻነት የሚያሳጣ ቅጣት በመፈጸም ላይ ሳለ በሥራው እና ጠባዩ የተረጋገጠ መሻሻል አሳይቶ እንደሆነ ነው፡፡ ሦስተኛው ሁኔታ ለደረሰው ጉዳት በተቻለ መጠን ሊከፍል የሚጠበቅበትን በፍርድ ቤት በተወሰነው መሰረት ወይም ከተበዳዩ ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረት ካሳ ለመክፈል ማረጋገጫ ሲያቀርብ ነው፡፡

የመጨረሻው ሁኔታ ጠባዩ በመልካም አኗኗር ለመኖር የሚያስችለው እና በአመክሮ መፈታቱ መልካም ውጤት ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ የታመነ እንደሆነ ነው፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 202   ወጀለኛው በተደጋጋሚ ወንጀል የፈፀመ ከሆነ በአመክሮ የመፈታት ውሳኔ ተፈጻሚ አይሆንም ሲል በግልጽ ደንግጎ ይገኛል፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here