የወንጀል ቅጣት ማቅለያ እና ማክበጃ

0
343

በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ወንጀልን ከመከላከል እና የሕዝብን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሰዎች በዕውቀት ማነስ ምክንያት ጥፋት እንዳይፈጽሙ እና በወንጀል እንዳይጠየቁ ለማድረግ ሲባል ሀገሪቱ ወንጀል ያለቻቸውን የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አስፍሯቸዋል::

ሕገወጥ ተግባራት በውል እንዲታወቁ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ ሰዎች ካላቸው ያላግባብ የመጠቀም እና ሌላውን የመጉዳት ሀሳብ ወይም ቸልተኛነት በሚመነጭ ተግባር ክልከላውን ተላልፈው ወይም በሕግ የተጣሉባቸውን ግዴታዎች ባለመወጣት የወንጀል ሕጉን ጥሰው ሲገኙ እርምት መውሰድ ዋነኛው አማራጭ ይሆናል::

በወንጀል ሕጉ ላይ በወንጀል የሚያስቀጡ ሕገወጥ ተግባራት ተዘርዝረዋል። ለእነዚህ የወንጀል ድርጊቶች እንደየወንጀሉ ባህርይ እና ክብደት በተበዳይ፣ በሕዝብ እና በመንግሥት ላይ ሊያስከትል ከሚችለው የጉዳት መጠን አንጻር ቅጣቶችን አስቀምጧል::

ቅጣት የራሱ የሕግ ፍልስፍና እና የንድፈ ሀሳቦች ያሉት ሲሆን ወንጀል አድራጊዎችን በማስተማር መልካም ዜጋ እንዲሆኑ እና ካለፈው ጥፋታቸው ትምህርት ወስደው ወደ ማሕበረሰቡ ሲቀላቀሉ ወንጀልን የሚጠየፉ እና ለሌሎችም ተምሳሌት የሚሆኑ ዜጎች እንዲሆኑ ጉልህ ሚና ይጫወታል። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ሰዎች በሕግ የበላይነት ከመገዛት ይልቅ አሸናፊነታቸውን በመጠቀም በሌሎች ላይ ተጽዕኖዎችን ማድረሳቸው እና ጉልበት የሌላቸውን ሰዎች መብቶች በመጣስ በሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እንዳያብብ እና ከስጋት ነፃ የሆነ ኑሮን እንዳይኖሩ መንገድ ይከፍታል::

ቅጣትን ወጥ፣ ተመጠጣኝ ወይም ተቀራራቢ ለማድረግ ፍርድ ቤቶች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው:: ይህ ሚናቸው ውጤታማ ይሆን ዘንድ ከወንጀል ሕጉ በተጨማሪ የቅጣት አወሳሰን መመርያው በጠቅላይ ፍርድ ቤት ወጥቶ በመተግበር ላይ ይገኛል::

በዚህ  ፍትህ ሚኒስቴር እና ኢትዮ ሕግ ያገኘነው ጽሁፍ ለማዳሰስ ትኩረት የሚደረገው ዐቃቤ ሕግም ሆነ ተከሳሽ ቅጣትን ለማክበድ እና ለማቅለል ሊያቀርቧቸው ስለሚገቡ በሕግ የተደገፉ ምክንያቶች ነው::

በክርክር ወቅት በውል ማስተዋል እንደሚቻለው ብዙዎች የቅጣት ማቅለያዎች እያሏቸው በዕውቀት ማጣት ወይም ማነስ ምክንያት ችሎት ላይ ሳያነሱ እየቀሩ ቅጣት ሊቀልላቸው እየተገባ ማክበጃዎች ብቻ ተወስደው ቅጣቶቹ ከብደው የሚወሰኑበት አጋጣሚዎች ቀላል የሚባሉ አይደሉም::

ፍርድ ቤቶችም በክርክር ወቅት የሚታዘቧቸውን የተከሳሽን በችሎት ማመን እና ተደጋጋሚ ጥፋት ካልቀረበበት ከዚህ ቀደም የነበረውን መልካም ባህርይ በመውሰድ በራሳቸው የቅጣት ማቅለያዎችን በመያዝ ቅጣትን አቅልለው ለመወሰን ይገደዳሉ::

ልዩ የቅጣት ማቅለያ ምክንያት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 83 ስር የተቀመጠውን የሕግ ድንጋጌ ስንመለከት ወንጀል መፈጸሙን እያወቀ ይህንኑ ለሚመለከተው አካል ወይም ባለስልጣን ሳያሳውቅ የቀረው ወይም ግዴታውን ያልፈጸመው ወይም ተገቢውን እርዳታ መስጠት ያልቻለው ወይም ሀሰተኛ ምስክርነት፣ መግለጫ እና መረጃ የሠጠው በራሱም ላይ ሆነ በቅርብ ዘመዱ (የሥጋ እና የጋብቻ) እንዲሁም ከእሱ ጋር ጥብቅ በሆነ ወዳጅነት የተሳሰረው ሰው ላይ ቅጣት እንዳይጣልበት ወይም ውርደት እንዳይደርስበት ለመከላከል ሲል ያደረገው መሆኑ ሲረጋገጥ ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን በመሰለው ሊያቀል እንደሚችል ሕጉ በግልጽ ይደነግጋል:: ይሁንና ፍርድ ቤቱ በዚህ ምክንያት ቅጣትን ከማቅለሉ በፊት ተከሳሽ ያነሳው የዝምድና እና የወዳጅነት ግንኙነት በትክክልም ስለመኖሩ ማረጋገጥ አለበት::

ወንጀል ፈፃሚው ከላይ በተጠቀሰው መሠረት ግዴታውን ሳይወጣ የቀረው ቀላል በሆነ ወንጀል ላይ ከሆነ ፍርድ ቤቱ በማስጠንቀቂያ ወይም በወቀሳ ብቻ ሊያሰናብተው ይችላል::

ፍርድ ቤቱ ቅጣትን በመሰለው ያቀላል ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ከወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ክፍል ቅጣትን በመሰለው ስለ ማቅለል በሚል ርዕስ ስር የተቀመጠውን መመልከት ተገቢ ነው:: በዚህም መሠረት የቀረበውን ልዩ የቅጣት ማቅለያ ምክንያት ፍርድ ቤቱ ሲቀበለው በልዩ ሕጉ ለወንጀሉ ከተቀመጠው የቅጣት ወለል ዝቅ በማለት በጠቅላላ ሕጉ እስከተቀመጠው (ለቀላል እስራት 10 ቀን ለጽኑ እስራት አንድ አመት) የቅጣት ዝቅተኛ መጠን ድረስ በማቅለል መቅጣት እንደሚችል ተቀምጧል::

ተከሳሽ በልዩ የቅጣት ማቅለያ ምክንያትነት ሊያነሳቸው ከሚችላቸው ምክንያቶች የተወሰኑትን እንመልከት።  የወንጀል ሪከርድ የለኝም፣ የቀድሞ ባህሪዬ መልካም ነበር፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ ነኝ፣ የድርጊቴ አፈጻጸም ቀላል ነው፣ አደገኛነትን አያሳይም፣ ባለሁበት የጤንነት ሁኔታ ማረሚያ ብገባ ሞቴ ሊፋጠን ይችላል፣ ከግንዛቤ ማነስ የፈጸምኩት በመሆኑ፣ ትምህርት የሌለኝ እና በቅንነት የፈጸምኩት በመሆኑ፣ ጥቅምን ለማግኘት ሳይሆን በግል ስሜት ተነሳስቼ ነው የፈጸምኩት፣ ፍትሐዊ ሥራ የሠራሁ መስሎኝ ነው የፈጸምኩት፣ የአስም በሽተኛ በመሆኔ ማረሚያ ቤት ብገባ አየር አጥቼ ልሞት እችላለው የሚል እና የመሳሰሉት ከላይ የተመለከትናቸው የቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ ምክንያቶች ቅጣትን በምን መልኩ እንደሚያቀሉት እና እንደሚያከብዱት ከአንቀጽ 179 እስከ 183 ድረስ ባሉት የወንጀል ሕጉ ድንጋጌዎች በግልጽ ሰፍረው እናገኛቸዋለን::

በመሆኑም ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ ጥፋተኛ ከተባለ በኋላ በሚያቀርበው የቅጣት ማክበጃም ሆነ ማቅለያ ምክንያት በቅጣት አወሳሰኑ መመሪያው የተቀመጠውን አሠራር መሠረት በማድረግ ይሠራል:: ተከሳሹም በተመሳሳይ ጥፋተኛ ከተባለ በኋላ የሚያቀርባቸው ማቅለያ ምክንያቶች በማስረጃ መደገፍ አለባቸው:: በመሆኑም ከላይ የጠቀስናቸው ማቅለያ ምክንያቶች የሚቀርቡ ከሆነ ምክንያቶቹ የእውነት ስለመሆናቸው የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል::

 

የቅጣት ማክበጃ ምክንያት

የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች በሁለት ይከፈላሉ። እነዚህም ጠቅላላ የቅጣት ማክበጃ ምክንያት እና ልዩ የቅጣት ማክበጃ ምክንያት ናቸው::

ጠቅላላ የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች የምንላቸው በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 84 ስር የተዘረዘሩት ናቸው:: ወንጀለኛው ወንጀሉን ያደረገው በከሀዲነት ወይም በወስላታነት ወይም በወራዳነት ወይም መጥፎ አመልን በሚያሳይ ምቀኝነት፣ ጥላቻ፣ ስግብግብነት፣ መጥፎ ነገርን ለመሥራት ወይም ሰውን ለመጉዳት ፍጹም ፍቃደኛ በመሆን ወይም በተለየ ክፋት ወይም ጨካኝነት እንደሆነ፣ ወንጀል ታስቦ ወይም በቸልተኛነት ሊፈጸም ከተቻለ፣ ወንጀለኛው ወንጀሉን ያደረገው ስልጣኑን፣ ተግባሩን ወይም የተጣለበትን እምነት ወይም ኃላፊነት ያለ አግባብ በመገልገል እንደሆነ ማለትም ባለስልጣናት ወይም የመንግሥትን ሥራ ለመሥራት ወይም ለመምራት ስልጣን ወይም እምነት የተጣለበት ሰው ከሆነ፣ ወንጀለኛው በቀድሞ ጥፋተኛነቱ ወይም ወንጀልን ማድረግ ሙያ ወይም ልማድ አድርጎ መያዙ፣ ወይም የወንጀሉ አፈጻጸም ዘዴ፣ ጊዜ፣ ቦታ እና የአፈጻጸም አኳኋን፣ በተለይም በሌሊት ወይም በሽብር ወይም በሁከት ለአደጋ ሽፋን ወይም በጦር መሳርያ ወይም በሌላ አደገኛ መሳርያ ወንጀሉን በማድረግ የተለየ አደገኛነቱን አሳይቶ እንደሆነ፣ … የሚሉት በወንጀል ቅጣት ማክበጃ ምክንያትነት ተዘርዝረዋል።

በመሆኑም ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ ጥፋተኛ ከተባለ በኋላ በሚያቀርበው የቅጣት ማክበጃም ሆነ ማቅለያ ምክንያት በቅጣት አወሳሰኑ መመሪያ መሠረት መሆን እንዳለበት በግልጽ የተቀመጠ በመሆኑ ይህንኑ ሊከተል ይገባዋል::

በአጠቃላይ ቅጣት ወንጀል አድራጊዎችን የሚበቀል ሳይሆን የሚያስተምር ነው። በመሆኑም ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት ውሳኔ ግልጸኝነት የተሞላበት እና በሚሰጡት ውሳኔ ውስጥ ለውሳኔ ያደረሳቸውን ምክንያት ምን እንደሆነ በግልጽ እና በዝርዝር መግለጽ፣ ተከሳሽን ነጻ ለማውጣትም ሆነ ጥፋተኛ ለማለት፣ የዋስትና መብት ለመጠበቅ ወይም ለመከልከል፣ ተለዋጭ ቀጠሮ ለመስጠት ወይም መዝገብን ለማቋረጥ እና ለመሳሰሉት ውሳኔዎች መነሻ የሆኑ ምክንያቶች በግልጽ መጠቀስ አለባቸው።

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ጥቅምት 4  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here