የኢትዮጵያ ታሪክ ከተጻፈው ይልቅ በእንቆቅልሽ፣ ተረት፣ ስነ ቃል፣ በቃል ግጥሞች፣ አፈታሪክ እና ሌሎች መሰል ዘዴዎች የሚተላለፍበት አጋጣሚ ይበልጣል፡፡ ለዘመናት ሕዝቦች እነዚህን ዘዴዎች በመጠቀም ጥበብ እና እውቀት በማግኘት ኖረዋል፡፡ ያልተጻፈው እውቀት ብዙ ያነጋግራል፡፡ የጥናት እና ምርምር መነሻ ይሆናል፡፡
ከእነዚህ የዕውቀት ዘርፎች መካከል አንዱ ቃል ግጥሞች ናቸው፡፡ ማህበረሰብ ብሶቱን፣ ስሜቱን፣ ደስታ እና ኀዘኑን ለመግለጽ የሚጠቀምበት መሳሪያ ነው፡፡ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ በቃል ይተላለፋል፡፡ የሚከወንበት አውድም ተለዋዋጭነት ሊገጥመው ይችላል፡፡ ቃል ግጥሞች የአንድን ማህበረሰብ አመለካከት እና ሕይወት ለማሳየት ዓይነተኛ መሳሪያ ናቸው፡፡
በእብናት ወረዳ በወፍጮ አውድ ላይ የሚከወኑ ቃል ግጥሞችን ዛሬ በአጭሩ እንመለከታለን፡፡ ጋሻው አሻግሬ በእብናት ወረዳ የባህላዊ ወፍጮ አውድ ላይ የተገጠሙ ቃል ግጥሞችን ሰብስቦ ተንትኗል፡፡ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት የሂዩማኒቲስ፣ ቋንቋዎች ጥናት ጆርናሊዝምና ኮምዩኒኬሽን ኮሌጅ የአማርኛ ቋንቋ፣ ስነ ጽሑፍና ፎክሎር ትምህርት ክፍል ድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር “በእብናት ወረዳ ከባህላዊ ወፍጮ አውድ ላይ የተሰበሰቡ ቃል ግጥሞች ትንተና” በሚል ርእስ ጥናቱ ቀርቧል፡፡
ቃል ግጥሞቹ ክፋት፣ ደግነት፣ ውዳሴ፣ ኀዘን፣ ማግኘት፣ ማጣት፣ ንቀት፣ ሽሙጥ እና ሌሎች የሕይወት አውዶችን ያሳያሉ።
አጊሳ፣ ደብር ተክለሃይማኖት፣ ግብጻዊት፣ ቁርቋራ፣ አዲያ፣ መናዲቅ፣ መና መድኀኒዓለም፣ አጃ ፋሲለደስ እና ዘቀልሞቃ የተባሉ ቀበሌዎች ጥናቱ የተደረገባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡
“ልጅነቴ መልካም ልጅ መውለዴ ክፉ
የማን ናት እመጫት እያሉኝ አለፉ”
ይህን ቃል ግጥም የምታቀነቅነው ፍቅሬ ዓለሙ የተባለች ሴት ናት። በሕጻንነቷ ለማደጎ ተድራለች። በ15 ዓመቷም ባል አግብታ ወልዳለች። ባሏ ልጅ ካስወለዳት በኋላ መሬት የለሽም በሚል ፈትቷታል። ልጅነት ላይ ልጅ ተደርቦባታል። በዚያ ላይ ደግሞ የከፋ ሕይወት እንድትመራ አድርጓታል።
ልጅ በመታቀፏ ልትታጭ አልቻለችም። የማን ሚስት ናት መባል ሲገባት የማን ናት እመጫት መባሏ ስሜቷን ጎድቶታል። በለጋ እድሜዋ በመውለዷ ወንዶች ሊያገቧት አይፈቅዱም። መጅ ይዛ እየፈጨች በግጥም ማህበረሰቡ በለጋ እድሜ ልጅን በመዳር የሚያደርሰውን ጉዳት ትቃወማለች፤ ትተቸዋለች።
“እንዝርት ያለ ወልቆ አይሽከረከርም
አህያ ተጭና አትንከባለልም
የሰጎን እንቁላል ወድቆ አይሰበርም
ሴትነት ነው እንጂ መልክ አያሳድርም”
ወይዘሮ ደብሬ ዓለሜ እየፈጨች ያንጎራጎረችው ቃላዊ ግጥም ነው። ሴትነት በእብናት ወረዳ ደብር ቀበሌ ምን ትርጉም ይሰጠዋል የሚለውን ትናገራለች። በዚህም መጋገር፣ መፍተል፣ መጥመቅ፣ መስፋት እና ሌሎች መሰል ተግባራት ሴትነት የሚገለጽባቸው እንደሆኑ ትናገራለች።
ማህበረሰቡ የጀግንነት መገለጫ ብሎ ከሚጠራቸው እንደ ማረስ፣ መማር፣ በንግድ፣ በጦር ሜዳ ውሎ ባሉ ተግባራት አትታማም። “ሞራ የመሰለ እንጀራ ስትጋግር፣ የዶሮ ዓይን የመሰለ ጠላ ስትጠምቅ፣ ሽታው የሚያውድ ወጥ ስትሰራ፣ በጥቅሉ በሙያዋ አንቱ ስትባል ትዳር እንደሚሞቅ ቃል ግጥሙ ያስገነዝባል” በሚል ጥናቱ አስፍሯል። ሴት ልጅ መተዳደሪያዋ ጥሩ ሙያተኛ መሆኗ ነው ይላል። ሴት ልጅ በዚህ ምክንያት በቤት ውስጥ እና ከቤት ውጪ ስራ ጫና ውስጥ መግቧታን ማህበረሰቡ አምኖ እንደተቀበለ ግጥም ደርዳሪዋ ገልጻለች።
ውዳሴ እና ሙገሳ ሴቶች እህል ሲፈጩ ከሚያዜሙባቸው አውዶች ሌላኛው ነው።
“እየው ከዚያ ማዶ የወጭት ስባሪ
ንጋቱ መኮንን ንጉሥ አሳዳሪ
ማሳደሩንማ ሁሉም ያሳድራል
ንጋቱ መኮንን ጠጅ ያዘነብላል”
አቶ ንጋቱ መኮንን በቁርቋራ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። በሀብት እና ንብረታቸው፣ በማርና ወተታቸው፣ በእህል ምርታቸው ስመ ጥር ናቸው። ስንኝ እየቋጠረች የምታሞግሳቸው ደግሞ ልጃቸው እናት ንጋቱ ናት። እንግዳ አቀባበላቸውን ታደንቃለች። አባቷ በአካባቢው ባለ ብዙ ጎተራ፣ ከብት እና ፍየል ይታወቃሉ። የመንግሥት አካላት ወደ አካባቢው ሲመጡም የሚያርፉት አቶ ንጋቱ ቤት ነው።
በቤት ለእንግዳ ከሚቀርበው መጠን፣ ከሚታረደው ሙክት፣ ከሚጠጣው ጠላ በተጨማሪ ልዩነታቸው ጠጅ ማዘንበላቸው ነው።
“ለቀይ ልጅ ቢሉኝ በርበሬ በላሁኝ
ለጥቁር ልጅ ቢሉኝ ከሰል ቆረጠምኩኝ
ኧረ ለጠይሙስ መድኀኒት አጣሁኝ”
ይህን ግጥም የምትደረድረው ሴት በተለያዩ ጊዜያት የተለያዬ ቀለም ያላቸው ወንዶችን አፍቅራ ነበር። በወንዶች ፍቅር የደረሰባትን ጉዳት ለመሻር ስትል የራሷን ዘዴ ተጠቅማለች። ከዚህ ቀደም ለቀዩ ስትል በርበሬ በልታለች፣ ለጥቁሩም ከሰል ቆርጥማለች። አሁን ግን ለጠይሙ ልጅ መላ ቸግሯታል። በጠይም ሰው ፍቅር የወደቀ መድኀኒት እንደማይገኝለት ከራሷ ተሞክሮ ትናገራለች።
“ከእንግዲህ ለባዳ ከእንግዲህ ለሰው
አፌም አይናገር ሆዴም አይረሳው”
ማሚት እሸቱ የተባለች ሴት ናት ይህን ቃል ግጥም የምታንጎራጉር። ከበደሉ ሁሉ ሰው ያደረሰባት በደል ምርር ያላት ትመስላለች። አንደበቷን ለመከርቸም መወሰኗን ትናገራለች። በደል ሆዷ ውስጥ በቅሎባታል። እዚህ ውሳኔ ላይ ድንገት አልደረሰችም። ሰው አምና የልቧን በመናገሯ ከመረዳት፣ ችግሯን ከመጋራት ይልቅ ምስጢሯ አደባባይ ተዘርቷል። ለዚህም ነው ከዚህ በኋላ ሰው ለሚባል ፍጡር አንደበቴ አይከፈትም፤ ሆዴም የደረሰበትን አይረሳም ስትል የምትናገረው።
“የሰው ልብሱ ሰው ነው” ከሚለው አባባል በተቃርኖ የሰው ጠላቱ ሰው መሆኑን ግጥሙ ያሳያል። እገሌ አለኝ ብሎ መመካት እና መኩራት የማይቻል ነው። “ከእንግዲህ ነገሬን ከከንፈሬ አልለቅም፤ አለ የሰው ዶሮ ከአፍ ከአፍ የሚለቅም” እንደሚባለው ሁሉ ይህችም ሴት በደረሰባት በደል ምክንያት ዝምታን መርጣለች።
ይህ ቃል ግጥም ዝምታን እንደ ብልሀት ይወስዳል። ምስጢርን በሆድ መያዝ መከበሪያ መሆኑን ይጠቁማል። “ዝም አይነቅዝም” የሚለውን አቻ አባባል ያስገነዝባል። ነገርን ሁሉ መናገር የሚያስከትለውን ችግር በመጠቆም መጠንቀቅን ያስታውሳል። ሆድ ከአገር ሰፊ ነው ብሎ የግል ጉዳይን በሆድ መቻልን ይሰብካል።
በዚህ ጥናት ላይ በእብናት ወረዳ አንዱ ወንድ ሚስቱን ትቶ ሌላ ሴት ጋር መሄዱ የተለመደ ሀቅ ነው። ለዚህም ደግሞ ወንዱ ከቤት የጎደለው ነገር ቢኖር ነው ተብሎ ይታሰባል። ሚስቱ የሆነችው ሴት ማድረግ የሚገባትን ሳታደርግለት ስትቀር ሌላ ሴት በድብቅ ወይም በይፋ ይይዛል። ባሌን ነጠቅሽኝ በሚል በሁለት ሴቶች መካከል ግጭት እና ጸብ ይፈጠራል። ባልየው ለምን እኔን ትተህ ሌላ ሴት ዘንድ ሄድህ ተብሎ አይጠየቅም። አዲስ የሄደባት ሴት ናት ቤት ባለችው ሚስት የምትወቀሰው።
አሁን ውዝግቡ በሁለቱ ሴቶች መካከል ነው። ጎባን ወይም ጣውንት ይባላሉ እነዚህ ሴቶች። ይህንም ጉዳይ በግጥም ይገልጹታል።
“እውነቱን መሰለሽ እኔን ትቶ ካንቺ
ያላየውን አይቶ ሊመጣ ነው እንጂ”
ማህበሩሰቡ አንድ ወንድ ሁለተኛ ሴት ሲይዝ ከቤት የጎደለበት ነገር ቢኖር ነው ብሎ ያምናል። ማህበረሰቡም ብቻ ሳይሆን ባላቸው ሌላ ሴት የደረበባቸው ሴቶች ራሳቸው በሙያ ወይም በሌላ ጉዳይ አንዳች ነገር እንደጎደላቸው አምነው ይቀበላሉ። ከዚህ የተነሳም ወንዝ ወርደው ውኃ መቅዳት፣ገበያ ሄደው ጉዳይ መፈጸም፣ ቤተክርስቲያን መሳምና ማህበር መጠጣት ይቸገራሉ። ማህበረሰቡም ይህች ባሏን ያስነጠቀች ብሎ በሽሙጥ ይጎነትላታል። በነጻነት መንቀሳቀስ እና መኖር አትችልም።
ከላይ ያለውን ግጥም የያቀረበችው ባሏን በሌላ ሴት የተነጠቀች ሴት ናት። ባሌ አንቺ ዘንድ የመጣው እኔ ጋ የጎደለበት ነገር ሳይኖር ነው፤ አንቺ ዘንድ ያላየው ነገር ብርቅ ሆኖበት ነው ትላለች። ደግሞም ሲሰለቸው ተመልሶ ይመጣል ነው የምትለው። በመልክ፣ በሙያ እና በሌላ ነገር ካንቺ የማንስ ሰው አይደለሁም በማለት ችግሩ የባሏ አመል መሆኑን ትናገራለች። ይህ አገላለጿ ግን የሚደርስባትን ውግዘት እና ትችት ለመሸሽ የምትፈጥረው እንጂ ውስጧ የጎደላት ነገር መኖሩን ያምናል፡፡
በዚህ ጥናት የእብናት ወረዳ ሴቶች ከፍተኛ የስራ ጫና ውስጥ ማለፋቸው እና በልጅነት መዳራቸው ተመላክቷል። ማፍቀር እንደ ወንጀል ይቆጠርባቸዋል። ወላጆች ከሚያመጡት ወንድ ሌላ ማግባት አይቻልም። ይህን ጣልቃ ገብነት በሕይወታቸው ካሰቡበት እንዳይደርሱ ማድረጉን ገልጸውታል።
በመጨረሻም ጥናቱ የዚህ ጥናት አካል ሴቶች ከደስታ ይልቅ የመረረ ሕይወት የሚገፉ መሆናቸውን አሳይቷል፡፡።
ማረፊያ
ህልምና አላሚ
ትናንት ህልም ነበር
ህልም ዛሬም አለ
ነገም ህልም አይጠፋ
አላሚው ብቻ ነው
በወረፋ መጥቶ ‘ሚሄድ በወረፋ
በወረፋው መሃል
ዘመን ሸፍጥ ሲያምረው
ጊዜ ተረብ ሲሻ ባ’ገር ላይ ያሾፋል
የሚታለም በዝቶ የሚያልም ይጠፋል።
ገጣሚ ደሱ ፍቅርኤል
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም