የአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ሲገለጥ በወርቃማ ቀለም ጎልቶ የሚነበብ አንድ ስም አለ – ኢትዮጵያ። በተለይም በ1950ዎቹ ማብቂያ እና በ60ዎቹ መጀመሪያ የነበረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአህጉራችን የንግሥና ዘውድ የደፋበት ጊዜ ነበር። በ1954 ዓ.ም ግብፅን በማሸነፍ ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ያነሳው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከአንድ ዓመት በኋላ በ1955 ዓ.ም ወደ ምዕራብ አፍሪካዋ ሀገር ጋና ያቀናው የሻምፒዮንነት ክብሩን ለማስጠበቅ በታላቅ ተስፋና ኩራት ነበር። ነገር ግን በአክራ ከተማ የጠበቃቸው እግር ኳሳዊ ፉክክር ብቻ አልነበረም፤ የፖለቲካ ሴራ፣ የሰንደቅ ዓላማ ክብር እና አስገራሚ የጀግንነት ታሪክ ጭምር እንጂ።
1955 ዓ.ም ለአፍሪካ ፖለቲካ እና ስፖርት ልዩ ዓመት ነበር። የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እና የጋናው ፕሬዝዳንት ክዋሜ ንኩሩማህ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) መመስረት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ በነበረበት ወቅት የአፍሪካ ዋንጫ በጋና መካሄዱ ውድድሩን ከስፖርታዊ ሁነት ባሻገር የፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መገለጫ አድርጎት እንደነበር ትራንስፈር ማርኬት ዶት ኮም አስነብቧል።
ኢትዮጵያ ወደ ጋና ያቀናቸው ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በማሸነፍ ጭምር በመሆኑ በታላቅ ግርማ ሞገስ ነበር። በወቅቱ ቡድኑን የመሩት የአፍሪካ እግር ኳስ ባለውለታ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ናቸው። የተጫዋቾቹ ስብስብ ደግሞ ወርቃማው ትውልድ ተብሎ እስካሁን የሚጠራ ነው። የቡድኑ አምበል ሉቺያኖ ቫሳሎ፣ ተከላካዩ መንግስቱ ወርቁ፣ ግብ ጠባቂው ጊላ ሚካኤል ተክለማርያም እና የመሃል ሜዳ ኮከቡ ጌታቸው ወልዴ የቡድኑ የጀርባ አጥንቶች እንደነበሩ የኢትዮጵያ የስፖርት የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ።
ይሁን እንጂ ቡድኑ ወደ ጋና ሲያቀና አንድ ትልቅ ክፍተት ተፈጥሮበት ነበር። በ1954ቱ ድል ወሳኝ ሚና የነበረው እና በቴክኒክ ብቃቱ የሚደነቀው ኢታሎ ቫሳሎ በኦሎምፒክ ማጣሪያ ከኬንያ ጋር ናይሮቢ ላይ በነበረው ጨዋታ ባጋጠመው ጉዳት ከሜዳ ውጭ መሆኑ ቡድኑን ወሳኙን ተጫዋች አሳጥቶታል። ነገር ግን አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ኢታሎ ቫሳሎ ለቡድኑ ያለው የሞራል ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን በማመን በክራንች እየተንቀሳቀሰም ቢሆን ከቡድኑ ጋር ወደ አክራ እንዲጓዝ አደረጉ። ይህ ውሳኔ ዛሬ ለዘከርነው ክስተት መሪ ተዋናይ ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።
በአራተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ፣ የድግሱ አስተናጋጅ ጋና እና ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ቱኒዚያ በአንድ ምድብ ነበሩ። ጋና ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጣችበት ወቅት በመሆኑ እና ብሄራዊ ቡድኗን የገነባችበት ጊዜ በመሆኑ ዋንጫውን በሀገሯ ለማስቀረት ቆርጣ የተነሳችበት ወቅት እንደነበር የካፍ ኦንላይን መረጃ ያስነብባል።
በዚህ ምክንያት የሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ የኢትዮጵያ ቡድን አክራ እንደደረሰ ፈታኝ መስተንግዶ እንዲገጥመው አድርጓል። ጋናውያን ዋንጫውን ለመውሰድ ሲሉ የኢትዮጵያን ቡድን ሞራል መስበር እና ስነ ልቦናዊ ጦርነት መክፈት ጀመሩ። ቡድኑ ያረፈበት ሆቴል የጥራት ደረጃው የወረደ፣ ጥሩ ያልሆነ ምግብ መቅረቡ እና የመለማመጃ ሜዳ እና በቂ የትራንስፖርት አቅርቦቱ ያልነበረ መሆኑን የጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ “ፍትሐዊ የጠጅ ክፍፍል” መጽሐፍ ያስረዳል። ይህም በተጫዋቾቹ ላይ ከፍተኛ ብስጭት ፈጥሮ እንደነበር መጽሐፉ ያስረዳል። በተለይም ጉዳት ላይ የነበረው ኢታሎ ቫሳሎ ክስተቱን በንዴት ይታዘብ ነበር።
ህዳር 18 ቀን 1955 ዓ.ም የአክራ ስታዲየም በሺዎች በሚቆጠሩ ጋናውያን ተሞልቷል። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በስታዲየሙ አንድ ውዝግብ ተፈጠረ፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተዘቅዝቆ በመሰቀሉ ነበር። ይህንን የተመለከተው ኢታሎ ቫሳሎ በክራንቹ እየሮጠ ሰንደቅ ዓላማው እንዲስተካከል ተከራከረ፤ በመጨረሻም ተስተካከለ።
ጨዋታዉም ተጀመረ፤ የመጀመሪያው አጋማሽ ፉክክርም ያለ ግብ ተጠናቀቀ። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ነገሮች ተቀየሩ። የጋናው አጥቂ ኤድዋርድ አኩዋህ በኢትዮጵያ ተጫዋች ጥፋት ተሰራበት። ለጥቋቁር ከዋክብቱ የፍጹም ቅጣት ምት ተሰጠ፤የመጀመሪያው ግብም ተቆጠረ። ግቡ መቆጠሩን ተከትሎ በክብር ትሪቡን ተቀምጦ የነበረው የጋና የመከላከያ ሚኒስትር በደስታ ተውጦ ወደ ሜዳ በመሮጥ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ማውረድ ጀመረ።
ተቀያሪ ወንበር ላይ ተቀምጦ ክስተቱን ይመለከት የነበረው ኢታሎ ቫሳሎ አይኖቹን ማመን አቃተው። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በመከላከያ ሚኒስትሩ ሲወርድ ማየት ደሙን አፈላው። ብዙዎች የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ስለተገዙ የሰንደቅ ዓላማ ክብር እና ምንነትን በሚገባ አይገነዘቡትም፤ አያት ቅድመ አያቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው የጠበቁት በመሆኑ ስለ ስንደቅ ዓላማ የሚረዱት ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው ማለት ይቻላል። ለዚያም ነው ኢታሎ የተሰበረ እግሩን እና ክራንቹን ይዞ ወደ ጄኔራሉ የተንደረደረው። ተጫዋቹ መንግስቱ ወርቁ ሁኔታውን ሲያስታውስ እንዲህ ይላል “ጄኔራሉ ወደ ሰንደቅ ዓላማ መስቀያው በመሄድ የኛን ሰንደቅ ዓላማ ከተሰቀለበት ማውረድ ሲጀምር ኢታሎ በክራንቹ በመታገዝ እያነከሰ ሄዶ ጄኔራሉን በክራንቹ ከኋላ ሲመታው ከነማዕረጋቸው በአፍ ጢማቸው ተደፉ።”
ሜዳ ውስጥ ኳስ እያንከባለሉ የነበሩት ሉቺያኖ እና ጓደኞቹ በድንገት ከሜዳ ውጪ ግጭት ሲነሳ ተመለከቱ። ሉቺያኖ ኳስ ይዞ የሚቀበለው ሲያጣ ዞር ብሎ ሲያይ ጓደኞቹ በሙሉ ሜዳውን ጥለው ወደ ሰንደቅ ዓላማ መስቀያው ምሰሶ እየሮጡ ነው፤ ጉዳዩ የእግር ኳስ መሆኑ ቀርቶ የክብር ጉዳይ ሆነ። “ኢታሎ ሲደባደብ አየሁት፤ እየሮጥኩ ወጣሁና ቦታው ላይ ደርሼ ድብድብ ውስጥ ገባሁ፡፡ ኢታሎን ሲታገል የነበረውን አንዱን ፖሊስ በቴስታ ስለው ወደቀ። ስታዲየሙ በግርግር ታመሰ። የቻይና ፊልም የሚመስል ድብድብ ተካሄደ። የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ከፖሊስ እና ከወታደሮች ጋር ተጋፈጡ። ከደቂቃዎች ግብግብ በኋላ ባንዲራው ወደ ቦታው ተመለሰ። የፌዴሬሽን ሰዎች ገብተው እስኪያረጋጉ ድረስ ሁኔታው አስፈሪ ነበር። ጨዋታው ቀጠለ ነገር ግን በጋና ሁለት ለባዶ አሸናፊነት ተጠናቀቀ” መንግስቱ ወርቁ እንዲህ ማለቱን በጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ ፍትሐዊ የጠጅ ክፍፍል መጽሐፍ ተቀምጧል። ሽንፈቱ ቢያማቸውም ዋልያዎቹ ሜዳ ላይ ሰንደቅ ዓላማቸውን ለማስከበር የሰሩት ጀብድ ከውጤቱ በላይ ጎልቶ ታየ።
ከጨዋታ በኋላ ነገሮች ተቀየሩ። ጋና ሁለተኛ ጨዋታዋን ከቱኒዚያ ጋር አቻ ወጣች፤ ይህ ማለት ኢትዮጵያ በመጨረሻው ጨዋታ ቱኒዚያን ካሸነፈች ጋና ለፍጻሜ (ለዋንጫ) ታልፋለች። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ሆነ ብላ በቱኒዚያ ከተሸነፈች ወይም አቻ ከወጣች ጋና ከውድድሩ ውጪ ትሆናለች። እናም ጋናውያን በዚህ ጉዳይ ስጋት ስለገባቸው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ላይ ያደረጉትን በደል ለማካካስ መሯሯጥ ጀመሩ። ቡድኑን ካረፈበት ሆቴል በማስውጣት በዋና ከተማዋ ከሚገኙ ምርጥ እና ቅንጡ ሆቴል ውስጥ በአንዱ አስገቡት። መስተንግዶውም ልዩ ሆነ። ይህ ሁሉ እንክብካቤ ግን የተጫዋቾችን በደል እና ቂም መሻር አልቻለም። ዋሊያዎቹም “ምንም ቢደረግልን ጋና ለፍጻሜ አታልፍም፤ ለቱኒዚያ እንለቃለን” ብለው ዛቱ።
የወቅቱ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ታላቁ የስፖርት ሰው ይድነቃቸው ተሰማ ተጫዋቾቹን ሰብስበው እንዲህ አሉ፤ “ልጆች! ስሜታችሁ ይገባኛል። ነገር ግን እኛ እዚህ የመጣነው ሀገርን ወክለን ነው። ዛሬ ለቱኒዚያ ብንለቅ ታሪካችን ይበላሻል። ሁለተኛ ደግሞ ጋና ከወደቀች ይህ በስሜት የሰከረ ደጋፊ በሰላም ወደ ሀገራችን እንድንመለስ ይፈቅድልናል ወይ? አሸንፋችሁ ጀግና ሁኑ እንጂ ተሸንፋችሁ ታሪክ አታበላሹ።” ይህ ምክር የቡድኑን ልብ አራራው። ህዳር 26 ቀን 1955 ዓ.ም ኢትዮጵያ እና ቱኒዚያ ተገናኙ። ዋልያዎቹ ብሶታቸውን እና ብቃታቸውን አቀናጅተው ሜዳውን ተቆጣጠሩት። አምበሉ ሉቺያኖ ቫሳሎ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር መንግስቱ ወርቁ እና ጌታቸው ወልዴ ቀሪዎቹን ሁለት ግቦች ከመረብ አገናኙ። ውጤቱም በኢትዮጵያ አራት ለሁለት አሸናፊነት ተጠናቀቀ። ይህ ውጤት ለጋናውያን ሰርግና ምላሽ ነበር።
ኢትዮጵያ በማሸነፏ ጋና ለፍጻሜ አለፈች። ዋሊያዎቹን ሲሰድቡና ሲያዋክቡ የነበሩት የጋና ደጋፊዎች ጨዋታው እንዳለቀ ሜዳ ገብተው የኢትዮጵያ ተጫዋቾችን ተሸክመው “ናሽናል ሂሮ! (ብሄራዊ ጀግኖች) እያሉ ስቴዲየሙን አደበላለቁት። ዋሊያዎች ሙያዊ ስነ ምግባርን በመጣስ ሆነ ብለው ተሸንፈው ቢሆን ኖሮ ከሜዳ በሰላም ላይወጡ የሚችሉበት እድል ሰፊ እንደነበር መንግስቱ ወርቁ ተናግሯል። በፍጻሜው ጋና ሱዳንን አሸንፋ ዋንጫውን ስትወስድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በግብፅ ሦስት ለባዶ ተሸንፎ አራተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቆ ወደ ሀገሩ ተመልሷል።
በአራተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ዋንጫውን ባታነሳም ልጆቿ ለሰንደቅ ዓላማው ያደረጉት ተጋድሎ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ሲዘከር ይኖራል። ያ ትውልድ ለሀገር ክብር ለሰንደቅ ዓላማ ፍቅር እና ለእግር ኳስ ጥበብ የነበረውን ታማኝነት በጋና ምድር አስመስክሮ አልፏል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የታህሣስ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


