ኖዓም ቾምስኪ የተባለ ሰው “ሚዲያን የሚጠቀም የሰዎችን አዕምሮ ይቆጣጠራል” በማለት ተናግሯል። እንደተባለውም ዛሬ ላይ የዓለምን መልክ እና ቅርጽ ያወቅነው በሚዲያ በመሆኑ ጉልበቱን እናይበታለን። 1987 ዓ.ም ታኅሳስ ሰባት ቀን በመታተም የአማራ ክልል ሕዝብ እና መንግሥት ልሳን ሆና የቀጠለችው በኩር ጋዜጣ በክልሉ ብሎም በኢትዮጵያ መልክ ላይ የራሷን አሻራ አትማለች። በከፍታም በዝቅታ፤ በሰላምም በቀውስም ወቅት በኩር ጋዜጣ ከአማራ ሕዝብ ጋር ተጉዛለች።
በበኩር ጋዜጣ የ30 ዓመታት ጉዞ ውስጥ የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጆች በመሆን የሰሩትን አባትሁን ዘገዬ እና ጥላሁን ቸሬን ጥቂት ጉዳዮችን አንስተንላቸው ተጨዋውተናል። በኩር በ30 ዓመታት ጉዞዋ ምን ሚና ነበራት የሚለው ቀዳሚ ጉዳያችን ነው። ያለፉት ዓመታት የጋዜጠኝነት ፈተናዎች እና የበኩር የወደፊት ጉዞም ተቃኝቷል። መልካም ንባብ።
ጋዜጠኛ እና ደራሲ አባትሁን ዘገዬ
አባትሁን ዘገዬ በ1988 በመጽሔት ዝግጅት ክፍል በኩል ዋና አዘጋጅ በመሆን ነው አሚኮን የተቀላቀለው። በኋላም ወደ በኩር ጋዜጣ ክፍል በመዛወር ከ 1989 እስከ 1992 ዓ.ም የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል። በአሁኑ ጊዜም የበኩር ጋዜጣ መዝናኛ አምዶች ምክትል ዋና አዘጋጅ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል። “ጋዜጣዋ ያበረከተችው አስተዋጽኦ የማይተካ ነው” በማለትም የበኩርን አሻራ ይናገራል። በክልሉ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፤ ልማት እንዲፋጠን፤ ባህል፣ ቋንቋ፣ ስነ ጽሑፍ እንዲያድግ ሁሉ አቀፍ ድርሻ መጫዎቷን ይገልጻል። በተለይም በጋዜጣዋ ምስረታ ሰሞን “ጋዜጣችን ምን ሕትመት ይዛ ወጣች” ይባል እንደነበር ያስታውሳል። “በኩር የመልካም አስተዳደር እንከን ይዛ ከወጣች ሰው ተመድቦ፤ ተጣርቶ ርምጃ ይወሰድ ነበር፤ በዚህም ከስልጣን የወረዱ የዞን አስተዳዳሪዎችን እናስታውሳለን” ይላል አባትሁን። በበኩር ዘገባ ብዙ ፍርድ የተዛባባቸው ሰዎች መብታቸው ስለመረጋገጡ በመጥቀስ ጋዜጣዋ የሕዝብ ድምጽነት ሚና ነበራት ይላል።
ሙያዊ ነጻነትን ከኀላፊነት ጋር በማጣጣም የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በመዘገብ 30 ዓመታትን ዘልቀናል የሚለው አባትሁን ዘገዬ፤ በኩር ጋዜጣ ፊት ለፊት በሚል አምዷ በመልካም አስተዳደር እና መሰረተ ልማት ተደራሽነት ላይ ትኩረት አድርጋ ሰርታለች። “ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በኩር አብዮቱ ሲቀጣጠል በግንባር ቀደምትነት ሰርታለች” የሚለው አባትሁን በኩር ለውጥ አማጪ በመሆን ሚናዋን መወጣቷን ይናገራል።
የጋዜጠኝነት ሙያ በብዙ ገጠመኞች የተሞላ ነው። የሚዲያ እውቀት ባልዳበረበት ዘመን የተመሰረተችው በኩር ጋዜጣ ከሕብረተሰቡም ይሁን ከመሪዎች በኩል የሚመጡ ለጋዜጠኞች አዳዲስ ፈተናዎችን እንዲያልፉ አድርጋለች። መላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ መሪነት የፖለቲካ ፕሮግራሙን ያስተዋውቅ ነበር። የብአዴን መሪዎች ባሉበት መድረክ በባህርዳር ውይይት ያደርጋል። ይህንን ለመዘገብ የቀድሞው የአሚኮ ስራ አስኪያጅ ታቦር ገብረ መድኅን (ዶክተር) እና አባትሁን ዘገዬ ስብሰባውን ታድመዋል። ርዕሰ አንቀጹን አባትሁን ዘገዬ የክልሉን መንግሥት አቋም በማሳየት ጻፈው ፤ መሪዎችም ወደዱት። በአንጻሩ ታቦር ደግሞ የሁለቱን የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት በዜና አቀረበው። በዚህ የብአዴን ሰዎች በጣም ተበሳጩ። ያንን ጊዜ አባትሁን እንዲህ ያስታውሳል “ የክልሉ መሪዎች ጠርተውን ‘ጋዜጣችንን መጫዎቻ አድረጋችኋት አይደል፤ መአሕድ ማን ስለሆነ ነው ሐሳቡን በጋዜጣ የሚያስተላልፈው?’ ብለው ተቃውሞ አቀረቡ” ይላል አባትሁን። በጋዜጠኝነት መርሆች ላይ ሲከራከሩ ረጅም ጊዜ አሳለፉ። መሪዎችን ለማሳመን ሞከሩ። ምሽት ዘጠኝ ሰዓት የጀመሩት ክርክር ማታ ሁለት ሰዓት እንደተጠናቀቀ አባትሁን ያስታውሳል። በወቅቱ ስለ ጋዜጠኝነት ግንዛቤ ከማጣት ሐሳባቸውን እንደተናገሩም አባትሁን ይገልጻል።
ሌላው የአባትሁን ትውስታ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳዳሪ ላይ የተደረገው የምርመራ ዘገባ ነበር። በኩር የመልካም አስተዳደር ጉዳዩን ዘገበችው። አስተዳዳሪውም ክልል ቢሮ መጥቶ ስሜ ጠፍቷል ብሎ ይከስሳል። በኩር መረጃ ሳይኖራት አትዘግብም፣ ይጣራ ተብሎ መረጃው ሲጣራ አስተዳዳሪው አንድን ቦታ ለሦስት ሰዎች በመስጠት በስልጣኑ መባለጉ ተረጋገጠበት። “በዚህም ሰውዬው ከስልጣኑ ተነስቷል” ሲል አባትሁን ያስታውሳል።
ባለፉት 30 ዓመት የቴክኖሎጂ ለውጥን ተከትሎ ሚዲያ በፈጣን እድገት ላይ ነው። አሁን ጋዜጦች በማህበራዊ ሚዲያው ከፍተኛ ጫና ውስጥ ገብተዋል። ማህበራዊ ሚዲያ የራሱ የሆነ ታዳሚን መስርቷል። ኢንስታንት ግራቲፊኬሽን ( አሁንም አሁንም መርካት) አጫጭር መረጃዎችን በማህበራዊ ሚዲያ በብዛት ማግኘት ተለምዷል። በኩር እንዴት ከቴክኖሎጂ ጋር ተስማምታ ትቀጥላለች የሚለውን አባትሁን ይናገራል። “የዘመኑ አንባቢ አጭር፣ ምጥን ያለ ጽሑፍ ይፈልጋል” የሚለው አባትሁን ማህበራዊ ሚዲያ ለበኩር እድል እንደሆነ ይናገራል። 10ሺሕ ኮፒ ከማሳተም በማህበራዊ ትስስር ገጾች በሚሊዮኖች እጅ መድረስ ይቻላል ብሎ ያምናል።
ጋዜጣ በዚህ ዘመን በሕልውናው የሚቀጥልበትን አማራጭ ሐሳብም ያነሳል። “ከሕብረቱሰቡ የእለት ከእለት ህይወት ጋር የተያያዙ ችግር ፈቺ ዘገባዎችን ማቅረብ፤ ከማህበራዊ ትስስር ገጾች ከፍ ያለ ዘገባ፤ የዳበረ መረጃን ይዞ በመስራት አሸናፊ ሆኖ መቀጠል ይቻላል” ሲል ይናገራል። “በኩር አሁን ዘመናዊ ሆናለች፤ ከሰማይ በታች የማትዳስሰው ምንም ጉዳይ የለም፤ የሚወጡት ዘገባዎች ሳቢ፣ አስተማሪ፣ መረጃ ሰጪ፣ እና ያደጉ ናቸው” ይላል።
ጋዜጠኛ ጥላሁን ቸሬ
ጥላሁን ቸሬ በአሚኮ ስልጠና እና ምርምር ማእከል የይዘት ምክትል ዳይሬክተር በመሆን በአሁኑ ጊዜ በመስራት ላይ ይገኛል። በ1997 ዓ.ም ነበር አሚኮን የተቀላቀለው። በሬዲዮ ክፍል ፕሮግራም አዘጋጅ በመሆን ስራውን ጀምሯል። 2000 ዓ.ም የበኩር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልን በዜና ዘጋቢነት ተቀላቀለ። ከ አምስት ዓመታት በኋላ በ2005 ዓ.ም የበኩር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆነ። እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ በኩር ጋዜጣን በዋና አዘጋጅነት መርቷል። በኩር ጋዜጣ በክልሉ ያበረከተችውን ሁለንተናዊ ሚና አጫውቶናል። “የጋዜጣዋ ዋና ዓላማው የነበረው መንግሥት እና ሕዝብን ማገናኘት ነበር። ከዚህ አኳያ ስናየው የሕዝብን ቅሬታዎች ለመንግሥት በማቅረብ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች” ብሏል። በኩር ጋዜጣ የመንገድ ግንባታ ተደራሽነት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የትምህርት ተደራሽነት እና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች ይላል።
“የለውጡን መንግሥት በመደገፍ፤ እጥረቶችን በማሳየት፣ ኢፍትሐዊ የሆነውን የሀብት ክፍፍል በማጋለጥ በኩል በኩር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች”ም ይላል። ማን ይጠየቅ በሚል አምዷ የሕዝብ ጥያቄዎችን እንዳነሳች፤ ማህበረሰቡ የሚሳተፍበት “ሐሳቤ” የሚል አምድ በመክፈት ሐሳቦች በነጻነት እንዲንሸራሸሩም መስራቷን ጥላሁን ቸሬ ይናገራል።
ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን ለውጥን ለማምጣት በቀደመው ስርዓት ላይ ሰይፍ የመዘዙበት ነበር ማለት ይቻላል። በዚህም በርካታ ሰዎች ፌስቡክን በመጠቀም ሕዝቡን ማታገል የጀመሩበት ጊዜ ነበር። በአደባባይም በመውጣት በስርዓቱ ላይ ተቃውሟቸውን የሚያሰሙበት ነበር። አፈና እና ጭቆና ብዙዎችን ወደ አክቲቪስትነት ቀይሯቸውም ነበር። በዚህ ጊዜ ሙያዊ መርህን አክብሮ መስራት በተለይ በጋዜጠኞች ዘንድ ፈተና እንደነበር ጥላሁን ይናገራል። ጋዜጠኛው ከሙያው ሸርተት ብሎ የማህበረሰብ አንቂነት ሚና ውስጥ መግባቱ፤ መንግሥት ደግሞ ጉድለቴን እንዳታሳዩብኝ ብሎ መወሰኑ ጋዜጠኝነትን ፈተና ውስጥ አስገብቶት እንደነበርም ይገልጻል። “መንግሥት ችግሮቹን ከሀገር ሉዓላዊነት እና ከብሔራዊ አንድነት ጋር በማያያዝ የጋዜጠኞችን ነጻነት ይጋፋ ነበር” ሲል ይተርካል። ጋዜጠኞችን ማንገራገር፣ ችግሮች እንዳይነገሩ መፈለግ፣ እና ማንገራገር ጥላሁን ቸሬ የበኩር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆና በሰራባቸው ዓመታት የገጠሙት ፈተናዎች ነበሩ።
ጋዜጣ ሞቷል፤ ዘመኑ አልፎበታል በሚል የሚሞግቱ ብዙ ናቸው። አሁን ማህበራዊ ሚዲያ እና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው (ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ) ለጋዜጣው ማደግ እና መነበብ እንቅፋት የሆኑበት ዘመን ተደርጎ ይወሰዳል። ጋዜጣ አሁን አንባቢ የለውም እስኪባል ድረስ፤ የሕትመት ሚዲያው ተቀዛቅዟል። ጋዜጦች እና መጽሔቶች ተዘግተዋል። ማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም በስማቸው ከቴክኖሎጂው ጋር ቀጥለዋል።
ጥላሁን ቸሬ “ጋዜጣ አልሞተም” ብሎ ያምናል። በኩር ጋዜጣ ከቴክኖሎጂው ጋር ራሷን አላምዳ ተነባቢ ሆና ልትቀጥል የምትችልባቸውን ዘዴዎችም ይናገራል። “ማህበራዊ ሚዲያው አጫጭር መረጃዎችን በመስጠት ነው የሚታወቀው” የሚለው ጥላሁን፤ “እንደ በኩር ዓይነቱ ጋዜጣ ጥልቀት ያለው ዘገባ መስራት ነው የሚያስፈልገው” ብሏል። ጥልቅ ትንታኔዎችን እና የምርመራ ዘገባዎችን በመስራት በማህበራዊ ሚዲያ በኩል የሚታየውን ክፍተት ሞልቶ መምጣት እንዳለበትም ገልጿል። “ዛሬ ሁሉም በእጁ መረጃ ያገኛል፤ በተለያዬ አቀራረብ፣ አንግል፣ በባለሙያ ትንታኔ በመስራት አሸናፊ መሆን ይቻላል” ብሏል
ከሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን እና ማህበራዊ ሚዲያው የተለየ አሰራርን መከተል ለበኩር የማሸነፊያ መንገድ መሆኑን ይናገራል ጥላሁን። በኩር ተነባቢ ሆና ለመቀጠል ነጠላ ጭብጥን በመያዝ መስራት እንዳለባትም ጠቁሟል። “ትላልቅ ጉዳዮችን አንስተን በጥልቀት ዘግበን እናውቃለን” የሚለው ጥላሁን ሙያዊ መርህን ከኀላፊነት ጋር አጣጥሞ መስራት ተገቢ ነው ብሏል። ጥልቀት ያላቸው ትንታኔዎች የበኩር ጋዜጣ የተነባቢነት ምክንያቶች በመሆናቸው ዘገባዎችን ከሁነት ባሻገር ተንትኖ መስራት ተገቢ ስለመሆኑ ተናግሯል።
በሉ ደግሞ በኩር ስልሳ ዓመት ሲሞላት እንገናኝ።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የታኅሳስ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም