የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ ምን ተሠራ?

0
116

የእያንዳንዱን ግለሰብ ፍላጎት የሚመጥን ገቢን በማሳደግ የዋጋ ንረቱ የዜጎችን ሕይወት ወደማያቃውስበት ደረጃ ማድረስ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፤ 6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ተካሂዷል።

ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘንድሮው የዋጋ ግሽበት 14 ነጥብ አራት በመቶ መሆኑን አስታውቀዋል:: ይህም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ከሚያስቀምጡት የዋጋ ንረት ደረጃ ላይ ያልደረሰ መሆኑን ጠቁመዋል:: እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የሚጠበቀው የዋጋ ንረት እስከ 10 በመቶ መሆኑም ተመላክቷል::

በምግብ ነክ ምርቶች የተመዘገበው የዋጋ ንረትም ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋማት ምክረ ሐሳብ በተቃራኒ የተጓዘ ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግንቦት ወርን በማሳያነት ያነሱ ሲሆን ግሽበቱ 12 በመቶ መድረሱን አመላክተዋል:: አሁናዊ የዋጋ ንረቱ ከረጅም ዓመት በፊት የነበረ እና እየተንከባለለ የመጣ እንደሆነ ማሳያ ያደረጉት በ1999 ዓ.ም የነበረውን የምግብ ነክ ምርቶች የዋጋ ንረት 60 በመቶ እንደነበር በማስታወስ ነው::

በኢትዮጵያ የተመዘገበው የዋጋ ንረት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በስምንት ነጥብ አራት በመቶ ዝቅ ያለ እንደሆነ ተመላክቷል::

ዶ/ር ዐቢይ ለዋጋ ንረቱ ዋናዉ መፍትሄ ብለው እንዲሠራበት ያሳሰቡት ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ፣ የገበያ ትትስርም ማጠናከር ነው:: በዚህ ዓመት የዋጋ ንረት የዜጎችን ሕይወት ወደማያቃውስበት ደረጃ ለማድረስ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል አርሶ አደሮች እያመረቱ የሚሸጡባቸው ትልልቅ ቦታዎች መገንባታቸውን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከአንድ ሺህ 400 በላይ የእሁድ ገበያዎች መከፈታቸውን ጠቅሰዋል::

ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ስንዴ እና ሌሎች ምርቶች በስፋት እየተመረቱ መሆኑ እየተነገረበት ባለ የዋጋ መቀነስ /ተመጣጣኝነት/ ለምን አልታየም ብለው እንደሚያነሱ ዶ/ር ዐቢይ አንስተዋል:: ምርት ተመርቶ ዋጋ ከቀነሰ ለምንድን ነው አርሶ አደሩ የሚያመርተው? ሲሉ ደግሞ ሁሉንም በሚዛን ማየት እንደሚገባ ጠቁመዋል::

23 ሚሊዮን ዜጎች ከሴፍቲኔት መውጣታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲገልጹ፣ እነዚህ ወገኖች በአንድም ይሁን በሌላ ወደ ሸማችነት እንደሚመጡ ገልጸዋል:: በየጊዜው ተመርቀው ሥራ የሚይዙትም ሸማች መሆናቸው የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣምን በማምጣት የዋጋ ንረት በሚፈለገው ደረጃ ልክ እንዳይሆን ማድረጉን ጠቁመዋል::

በዋጋ ንረቱ የመንግሥት ሠራተኛው እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች አልተጎዱም ወይ በሚል ከምክር ቤት አባላት የተነሳው ጥያቄ ተገቢነት ያለው መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ችግሩ የተጠቀሱትን ወገኖች ይበልጥ ተጎጂ እንዳያደርጋቸው 350 ቢሊዮን ብር ድጎማ መደረጉን አንስተዋል::

የዋጋ ግሽበትን ከፍላጎት ጋር ማጣጣም የሚቻለው እያንዳንዱ ግለሰብ ፍላጎቱን የሚመጥን ገቢ ማስገባት ሲቻል ብቻ ነው:: ለዚህም አጠቃላይ ዕድገቱን ማረጋገጥ ላይ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የሰኔ 30  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here