የውል እርሻ ለበለጠ ተጠቃሚነት

0
9

ግብርናውን ለማዘመን  እየተተገበሩ ከሚገኙ አሠራሮች መካከል የግብርና ውል እርሻ አንዱ ነው። የውል እርሻ በግብናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ቁልፍ የግብርና ሥራ ችግሮችን መፍታት የሚስችል የአሠራር ስልት ነው:: የውል እርሻ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ከጥንት ጀምሮ ሲተገበር ኖሯል:: ለአብነት በቻይና ከአንደኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የውል እርሻ አሠራር ነበር:: ሕንድ ደግሞ በዘመናዊ ውል እርሻ አሠራር ቀዳሚዋ መሆኗን ጥናቶች ያመላክታሉ:: በአፍሪካ ደግሞ ኬንያ በስፋት ትታወቅበታለች:: በሀገራችን ደግሞ ከ1942 ጀምሮ በትንባሆ፣ ሻይ ቅጠል ሸንኮራ፣ ጥጥ እና ሌሎች ምርቶች ሲሠራበት ነበር:: ነገር ግን በሚፈለገው መጠን ሊያድግ አልቻለም::

የግብርና ምርት ውል በአምራች እና በአስመራቹ መካካል በሥምምነት ለማምረት፣ ለመደጋገፍ፣ ለመግዛት፣ ለመሸጥ  የሚደረግ የቅድሚያ ሥምምነት ነው:: አሠራሩ በአማራ ክልል  ከተተገበረ አራት ዓመታት ገደማ  አስቆጥሯል። በዚህ ዓመት ደግሞ ከ280 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በውል እርሻ የተለያዩ ሰብሎችን እያመረቱ ይገኛሉ።

የውል እርሻ በመሰረታዊነት አላማው የእርሻ ምርትን መጨመር ነው። የግብርና ምርት ውል ሥራዎች አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የምርት ጥራትንም ብዛትንም በከፍተኛ አቅም ማሳደግ የሚያስችል ሲሆን የውል እርሻ አዋጅ ከፀደቀ ጀምሮ የአርሶ አደሮችን የፋይናንስ ችግሮች፣ የእውቀት ሽግግር ችግሮችን መቅረፍ መቻል ጀምሯል።

አርሶ አደር አወቀ አበራ በምዕራብ ጎንደር ቋራ የሚኖሩ አርሶ አደር ናቸው:: ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት አርሶ አደሩ ያመርቱበት የነበረው መንገድ ምርታማነትን ሊያመጣ አለመቻሉን ገልጸዋል:: ምርትን ከራሳቸው አልፈው ለገበያ ማውጣት የሚባለው እሳቤም የማይታሰብ እንደነበር ያስታውሳሉ:: ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው የውል እርሻ ግን ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል::

አርሶ አደር አወቀ በዚህ አሠራር ገበያ ተኮር ሰብሎችን እንዲያመርቱ በመደረጋቸው ከራሳቸው አልፈው ለገበያ ማቅረብ እንደቻሉም አስገንዝበዋል:: የውል እርሻ ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው ያሉት አርሶ አደሩ ከዘር እና ከእርሻ ዝግጅት ጀምሮ የግብዓት እና የምክር አገልግሎት ማግኘት ያስችላል፤ ይህም ውጤታማ ለመሆን ያግዛል ብለዋል::

በፌደራል ግብርና ሚኒስቴር፣ በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ እና የኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት የተዘጋጀ “የግብርና ውል እርሻ” አሰራር ዙሪያ ክልላዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በውል እርሻ  እየተሳተፉ ከሚገኙ አርሶ አደሮች ውስጥ መለሰ ሙሐባው  አንዱ ናቸው። አምራቹ ለአራት ዓመታት ያህል በውል እርሻ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸውልናል። በዚህም ለእርሻ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በወቅቱ እንዲያገኙ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። በሄክታር የሚገኘው ምርትም እንዲያድግ አድርጓል፤ ከምርት በኋላ ደግሞ በወቅቱ ምርቱን ማስረከብ እንዲችሉ ዕድል እንደፈጠረላቸው ነው የገለጹት። በ2017/18 የምርት ዘመንም 20 ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ ሰሊጥ፣ ቦሎቄ እና ማሾ በውል እርሻ እያመረቱ ነው።

በአስመራችነት ላይ ተሠማርተው የሚገኙት መሠረት ልጃለም በ2013/14 የምርት ዘመን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በውል እርሻ ሥራ እንደጀመሩ ገልጸዋል። አሁን ላይ አሠራሩን ወደ አራት ዞኖች እና ሁለት ክልሎች በማስፋት ስድስት አይነት ሰብሎችን በውል እርሻ እያስመረቱ መሆኑን ገልጸዋል።

በ2017/18 የምርት ዘመንም በአማራ ክልል ከ2 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ጋር የሰሊጥ፣ የማሾ፣ የአኩሪ አተር፣ የቦሎቄ ሰብሎችን በውል እርሻ እያስመረቱ ይገኛሉ። ከዚህም 109 ሺህ ኩንታል ለመረከብ አቅደዋል። የትራክተር፣ የኬሚካል እና የገንዘብ ብድር እያቀረቡ መሆኑንም ተናግረዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንት እና ምርት ግብይት ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረጀ አበበ በአቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ በሀገራችን የውል እርሻ በግብርና ስራ አምራች እና አስመራች ህጋዊ ስምምነት ፈጥረው የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሻሻል መንግሽት በስፋት እየሠራበት የሚገኝ እንደሆነ አመላክተዋል።

የኮንትራት እርሻ የግብርና ስራን ቀላል አመቺ እና ውጤታማ ያደርጋል ያሉት አቶ ደረጀ በዚህም አስመራችች ውል ለያዙላቸው አምራቾች የእርሻ ስራ ግብዓቶችን፣ አስፈላጊ ቴክኖሎጂን እና ባህር ተሻጋሪ የገበያ ትስስርን በመፍጠር የማምረት አቅምን ከማሳደጉም በላይ ለኢንደስትሪ ፓርኮች ቋሚ ኢንቨስትመንትን በመፍጠር የጎላ ድርሻ እንዳለው አሳውቀዋል።

በአብክመ ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ሙሽራ ሲሳይ የግብርና ምርት ውል በክልሉ ከተጀመረበት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን ጥቅል የኮንትራት እርሻ አፈፃፀም አስመልክቶ ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን በዚህም የግብርና ምርት ውል ከዘመናዊ ግብርና አሰራር ስልቶች አንዱ ሲሆን ስራውም የማስመረት ሀቅም ያላቸውን አስመራቾች የብቃት ማረጋገጫ እየሰጠ በሒደት ምርትን ሽጦ የማምረት አሰራር እንደሆነ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው የግብርና ውል እርሻ በክልሉ ከተተገበረ አራት ዓመታት ገደማ ማስቆጠሩን ገልጸዋል። አሁን ላይም በ10 ዞኖች በሚገኙ 45 ወረዳዎች በሰሊጥ፣ በአኩሪ አተር፣ በቦሎቄ፣ በጤፍ እና በመሳሰሉ ሰባት ሰብሎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል። 631 አስመራቾች በሥራው ላይ እየሠሩ እንደሚገኙም ነው የጠቆሙት። ከ280 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ውል ወስደው እያመረቱ እንደሆነም ገልጸዋል።

በምርት ዘመኑ በክልሉ ከ783 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በውል እርሻ መልማቱን ያነሱት ምክትል ኀላፊው ከዚህም 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ መታቀዱን አብራርተዋል። ይህም የምግብ ፍጆታን ለማረጋገጥ፣ ለኤክስፖርት እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት ለማቅረብ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል። በቀጣይ በሁሉም አካባቢዎች በሁሉም የሰብል አይነቶች፣ በእንስሳት ሃብት እና ፍራፍሬ ላይ ለመሥራት ታቅዷል ብለዋል። ከዚህ በፊት በአምራች እና አስመራች መካከል ከገበያ ጋር ተያይዞ ይነሳ  የነበረውን ችግር ለመፍታትም አስገዳጅ አዋጅ እና መመሪያ መውጣቱን ገልጸዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) የግብርና የውል እርሻ መሬት በኢትዮጵያ የቆየ አሠራር እንደሆነ ገልጸዋል፤ ይሁን እንጂ በሕግ ማዕቀፍ ባለመታገዙ በአሠራር ሂደቱ ላይ እንቅፋት ፈጥሮ ቆይቷል ብለዋል። ችግሩን ለመፍታትም ከ2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ የውል እርሻ መሬት አዋጅን በማጽደቅ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት አዋጁ የአርሶ አደሮችን ምርታማነት እንዲያሳድጉ አድርጓል፤ አስመጪ እና ላኪዎች የሚፈልጉትን ምርት በጥራት እና በተፈለገው ጊዜ እንዲያገኙ ዕድል ፈጥሯል።  ለኢንዱስትሪዎችም ጥራት ያለው ምርት ለማቅረብ እያገዘ ነው። የውል እርሻ መሬት ከሰብል እና ከሰብል ልማት (ሆርቲ ካልቸር) ባለፈ የተፈጥሮ እና የእንስሳት ሃብቶችን እንደሚያካትትም ገልጸዋል። አሠራሩን እስከ ታች ድረስ ማስተዋወቅ ይገባልም ነው ያሉት።

ሚኒስትር ዴኤታዋ  የውል እርሻ በዓለም ላይ በግብርናው ዘርፍ  ከማምረት እስከ ግብይት ድረስ  ውጤታማ ነው ያሉ ሲሆን በኢትዮጵያ አማራ ክልልም በውል እርሻ አሠራር የተሻለ ተሞክሮ እንዳለው ገልጸዋል። በቀጣይ አርሶ አደሩን እና ባለሀብቱን በሰፊው  ባሳተፈ መንገድ ሊሠራበት የሚገባ አሠራር እንደሆነ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬው ተገኘ (ዶ/ር) የግብርናው ዘርፍ በባሕላዊ አሠራርም ቢሆን ከሀገራዊ ጥቅል ምርት 32 በመቶ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል። ኢንስቲትዩቱ ባሕላዊውን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል። እየሠራቸው ከሚገኙ ሥራዎች ውስጥም በውል እርሻ መሬት አሠራር ምርታማነትን ማሳደግ አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል።

አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም የሚያመርቱትን ምርት ከመካፈል ወጥተው እሴት ጨምረው ለገበያ  እንዲያቀርቡ ማድረግ የቀጣይ ትኩረት መሆኑንም ተናግረዋል። የውል እርሻ መሬት አሠራርን የማስፋት ተግባርም ሌላኛው የቀጣይ ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይት መድረኩ የፌደራል ግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ሶፍያ ካሳ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)ን  ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞን አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩትና የግብርና ቢሮ ዳይሬክቶሬቶች፣ የግብዓት ቡድን መሪ ከሁሉም ዞኖች፣ የፍትህ መምሪያ ኃላፊ፣ የግብዓት እና የሰብል ልማት ቡድን መሪና የውል እርሻን የሚከተል የግብዓት ባለሙያ፣ አምራችና አስመራች ድርጅቶች እና የሚመለከታቸው አጋርና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በመጨረሻም ግብርና ሚኒስትር በምርምር የተደገፉ መረጃዎችን በማቅረብ፣ የኮንትራት እርሻ ስምምነቶች ፍትሃዊ እና ሁሉንም አካላት ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እንዲቀረጹ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የተገለፀ ሲሆን፤ የኮንትራት እርሻን አሰራር ይበልጥ ለማሳደግ፣ ገበሬዎችን ለማሰልጠን እና የገበያ ትስስርን ለማጠናከር በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይም ተደርሷል።

በክልሉ በ10 ዞኖች የውል እርሻ የሚተገበር ሲሆን የሚመረቱ ዋና ዋና ሰብሎችም አኩሪ አተር፣ ሰሊጥ፣ ማሾ፣ ቦሎቄ እና ሌሎችም ይገኙበታል።

 

መረጃ

በሰብል ስብሰባ ወቅት መደረግ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች፡-

የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ ማጨድ እና እርጥበት በሌለበት ቦታ ማከማቸት፣

በስብሰባ (አጨዳ) ወቅት ፍሬያቸው በቀላሉ የሚረግፉ ሰብሎችን መለየት እና ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ፣

የሚታጨዱ ሰብሎችም በደንብ መድረቃቸውን ማረጋገጥ፣

በሚበራይበት ወቅትም የተሸለ የቦታ መረጣ ማድረግ፣

እርጥበት የማያስገባ እና በተባይ በቀላሉ የማይጠቁ ጎተራዎችን መጠቀም፣

በማጓጓዝ ወቅትም ብክነት እንዳይኖር ጥንቃቄ ማድረግ!

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here