ስለውርስ ሕግ ምንነት እና ወራሽ ማን ነው? ስለሚለው በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የፍትሐብሄር ጉዳዮች ባለሙያ አቶ እንደግ ሰውነትን ጠይቀናቸዋል:: እንደባለሙያው ማብራሪያ የውርስ ትርጉም በሀገራችን የውርስ ሕግ ውስጥ በቀጥታ ተተርጉሞ ባናገኘውም ከሕጉ ጠቅላላ መንፈስ መረዳት የሚቻለው ውርስ ማለት በሞት የተለየን ሰው ሀብት፣ ንበረት እና ሊተላለፉ የሚችሉ መብትና ግዴታዎች በሕይወት ላሉ አንድ እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ሰዎች የሚተላለፉበት መንገድ ነው:: ወይም የሟች ሀብት እና በሀብቱ ላይ ያለው መብትና ግዴታ በሕይዎት ላሉት ወራሾች የሚተላለፍበት ሕጋዊ የአሠራር ሥርዓት ነው::
የውርስ ሕግ ምንድን ነው?
አቶ እንደግ ሕጉን መሰረት አድርገው ሲገልጹ የሀገራችን የውርስ ሕግ በ1952 ዓም በወጣው የፍትሐብሔር ሕግ ከአንቀጽ 826 እስከ 1125 ድረስ ተደንግጎ ይገኛል::
ከዚህ ሕግ እንደምንረዳው የውርስ ሕግ ጠቅለል ባለ አገላለጽ የሟች መብቶች እና ግዴታዎች በሕይወት ወዳሉት ወራሾች የሚተላለፍበት ነው:: ይህ ማለት ደግሞ የሟች ውርስ መቸ? እና የት ቦታ ይፈጸማል?፣ ወራሾቹ እነማን ናቸው? ወራሽነትን የሚያሳጡ ምክንያቶች ምን ምን ጉዳዮች ናቸው?፣ የሟች ኑዛዜ ምን ማሟላት አለበት? ፣ ውርሱ እንዴት እና በማን ይጣራል?፣ የውርስ ክፍያው እንዴት እና በማን ይፈጸማል?… ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ ነው::
ወራሽ ማን ነው? ከተባለ ደግሞ ወራሽ ለመሆን የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች (ለወራሽነት የሚያበቁ መስፈርቶች) በዋናነት ወራሹ በሕይወት ያለ መሆን እና ለወራሽነት የማይገባ አለመሆን ተብሎ በሕጉ መስፈሩን ባለሙያው አብራርተዋል:: በሕጉ የተጠቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች ሳያሟሉ በስመ ተወላጅነት ወይም ወላጅነት ብቻ ወራሽ መሆን እንደማይቻልም አክለዋል::
በሕይወት ያለ መሆን በፍትሃብሔር ሕግ ቁጥር 830 ላይ እንደተደነገገው አንድ ሰው ወራሽ ለመሆን አውራሽ በሚሞትበት ጊዜ በሕይዎት ያለ መሆን አለበት የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ በልዩ ሁኔታ በፍትሃብሔር ሕግ ቁጥር 834 ላይ ተደንግጓል :: ይህም ሟች ከመሞቱ በፊት ተጸንሶ የነበረ ልጅ ተወልዶ 48 ሰዓት በሕይወት ከቆየ በሕይወት እንደነበረ ተቆጥሮ ሟችን የመውረስ መብት አለው::
ሌላው ደግሞ ለወራሽነት የማይገባ አለመሆን የሚለው ነው፤ ይህም ወራሽ ለመሆን ከሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ለወራሽነት የማይገባ አለመሆን ነው::
ይሕ ማለት ምን ማለት ነው? ከተባለ ደግሞ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 838 ላይ እንደተደነገገው ወራሽ ለመሆን ሟችን ወይም የሟችን ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆች ወይም ወደላይ የሚቆጠሩ ወላጆች ወይም የሟችን የትዳር አጋር ከእነዚሀ ውስጥ አንዱን አስቦ በመግደሉ ወይም በመግደል ሙከራው የተፈረደበት ወይም በሀሰት በመወንጀል ወይም በሀሰት በመመስከር ከእነዚህ ሰዎች በአንደኛው ላይ የሞት ፍርድ ወይም ከአስር ዓመት የበለጠ የጽኑ እስራት ቅጣትን ለማስከተል የሚያሰጋ ሆኖ የተቀጣ ከሆነ ወይም በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 840 እንደተደነገገው ሟች በነጻነት እንዳይናዘዝ ተፅኖ ማሳደር፣ አውራሽ ከመሞቱ በፊት ባሉት ሦስት ወራት ውስጥ የአውራሽን ሁኔታ ከግምት አስገብቶ ኑዛዜ እንዳይደረግ፣ ኑዛዜ እንዳይለወጥ ወይም እንዳይሻር የከለከለ እንደሆነ ወይም አስቦ ያለሟች ፈቃድ የመጨረሻውን ኑዛዜ ያበላሸ፣ እንዳይገኝ ያደረገ፣ ያጠፋ ወይም ጉዳዩን በማወቅ በሃሰት ኑዛዜ የተጠቀመ እንደሆነ፣ ለወራሽነት የማይገባ ሰው ለወራሽነት የሚገባ በመሆን እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን መጥፎ ተግባራት የፈጸመ ሆኖ የተገኘ ሰው ነው ተብሎ ተገልፆል::
ከነዚህ በላይ የተጠቀሱት እንደተጠበቁ ሆነው ያለኑዛዜ ወራሽ ለመሆን፣ በበፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር ከአንቀጽ 842 እስከ 847 በተጠቀሱት የዝምድና ሀረጎች መሠረት ዘመድ ሆኖ መገኘት በኑዛዜ ወራሽ ለመሆን ከአውራሽ ኑዛዜ የተደረገለት ሰው ሆኖ መገኘት ነው::
የውርስ ዓይነቶች፦
በሀገራችን በውርስ ሕግ ውስጥ ሁለት አይነት የውርስ ማስተላለፊያ መንገዶች አሉ::
ያለ ኑዛዜ ውርስ
በኑዛዜ ውርስ
ሳይናዘዝ የሞተ ሰው ውርስ በአንቀጽ 842 መሠረት የሟች ልጆች የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ ሆነው ይወርሳሉ:: በአንቀጽ 843 መሠረት ደግሞ ሟች ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆች የሌለው እንደሆነ እናት እና አባቱ ሁለተኛ ደረጃ ወራሾቹ ናቸው::
በአንቀጽ 845 መሰረት ሟች ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆች ወይም አባት እና እናት ወይም የእናትና አባቱ ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆች (እህትና ወንድም) የሌሉት እንደሆነ አያቶቹ ሦስተኛ ደረጃ ወራሾቹ ሆነው ይወርሳሉ::
በአንቀጽ 847 መሠረት ደግሞ የሟች ሦስተኛ ደረጃ ወራሾች ከሌሉ የሟች ቅድመ አያቶች አራተኛ ደረጃ ወራሾች ሆነው ይወርሳሉ::
በአንቀጽ 852 መሠረት የሟች ከአንደኛ እስከ አራተኛ ደረጃ የተጠቀሱት ዘመዶች የሌሉ እንደሆነ የሟችን ሃብት መንግሥት ወራሽ ይሆናል:: የኑዛዜ ውርስ ደግሞ ሟች ከመሞቱ በፊት ንብረቱን በፍላጎቱ መሠረት ለኑዛዜ ወራሾቹ የሚያስተላልፍበት ሕጋዊ የአሠራር ሥርዓት ነው::
በመጨረሻ ግን ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ እንዳለ ባለሙያው ጠቁመዋል:: በሕጉ አንቀጽ 857 መሰረት ኑዛዜ ጥብቅ የሆነ የግል ጠባይ ያለው ጉዳይ ነው:: በመሆኑም ኑዛዜ የሟች ጥብቅ የሆነ ራሱ የሚፈጽመው ሥራ እንጅ በሌላ ሰው በውክልና ኑዛዜ እንዲያደርግ ፣ እንዲለውጥ ወይም እንዲሽር ሥልጣን ሊሰጠው እንደማይቻል አስገነዝበዋል::
( ማራኪ ሰውነት)
በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም