የውኃ ሀብትን በመጠበቅ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው

0
91

የውኃ ሀብታቸውን በመጠበቅ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በትኩረት እየሠሩ መሆኑን በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ የውኃ እና መሬት ሀብት ማዕከል የተባለ የምርምር ተቋም ስልጠናን ጨምሮ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ገልጸዋል።

በምርምር ተቋሙ ስልጠና ከተሰጣቸው መካከል በቆጋ መስኖ ልማት ተጠቃሚ የሆኑት አርሶ አደር ዘውዱ ወርቁ ይገኙበታል። አርሶ አደሩ እንዳሉት በመስኖ ፕሮጀክቱ ያለው የመስኖ ካናል ካልተጸዳና በአግባቡ ካልተያዘ የውኃው ብክነት ከፍተኛ ነው። የምርምር ተቋሙ በሰጣቸው ስልጠና ግንዛቤ ተፈጥሮላቸዋል።  በመሆኑም የውኃ ሃብቱ እንዳይባክን እየተንከባከቡ ነው። በዚህም ያለውን የውኃ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እያዋሉ ተጠቃሚነታቸውም እየተሻሻለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሌላዋ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ ተጠቃሚ አርሶ አደር ሃይማኖት ያደላ ውኃ እንዳይሰርግ እና በደለልም እንዳይሞላ በአርሶ አደሩ ዘንድ አደረጃጀት ተፈጥሮ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ይህም የውኃ ሀብታቸውን ከብክነት በማዳን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እንዳስቻላቸው ነው የገለጹት።

የሰብል ልማት ባለሙያዋ ሻሺቱ ጫኔ በአካባቢው ፍትሃዊ የውኃ አጠቃቀም እንዲኖር የተሠራው ተግባር ውጤታማ ስለመሆኑ ተናግረዋል።  አርሶ አደሩም የውኃ ሀብትን የመንከባከብ ግንዛቤው ማደጉን ነው ያነሱት።

የውኃ እና መሬት ሀብት ማዕከል ተመራማሪ ሙሉጌታ ፈረደ እንዳሉት የቆጋ መስኖ ግድብን ከደለል የመከላከል አሠራር ተግባራዊ እንዲሆን ከተጠቃሚ አርሶ አደሮች ጋር እየሠሩ ነው። የከርሰ ምድር ውኃ አማራጭ እንዲሆንም እየተጠና ስለመሆኑ አክለዋል። ለዚህ ደግሞ የመሬት ቴክኖሎጂዎችን እንደሚጠቀሙ  አስገንዝበዋል።

የከርሰ ምድር እና የገጸ ምድር ውኃን በአግባቡ ለመጠቀም ለአርሶ አደሮች ተከታታይ ስልጠና እየተሰጠ ነው። በጥናት የተደገፈ እና ቴክኖሎጂን  መሠረት ያደረገ የውኃ ሀብት አጠቃቀምን ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂነት ያለው የመስኖ ልማትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የውኃ እና መሬት ሀብት ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ሐና አላምረው (ዶ/ር) ናቸው። ለዚህ ደግሞ በዘርፉ ያሉ ውጤታማ ተሞክሮዎችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ማላመድ ዓላማ መደረጉን ነው ያብራሩት።

(እያያው ተስፋሁን)

በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here