
እንደ ሀገር በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱት ውስጥ ከግማሽ በላይ ማሳለፍ የተቻለው በ2012/13 የትምህርት ዘመን ነው። በወቅቱም 55 ነጥብ 7 በመቶ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተዋል:: ከዚያን ጊዜ በኋላ ባሉት ዓመታት ግን ከፍተኛ የሆነ የውጤት ማሽቆልቆል ተመላክቷል::
ለማሽቆልቆሉ ዋና ምክንያት ተደርጎ የተወሰደው ደግሞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ በተወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የፀጥታ ችግሩ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መስፋፋቱ ነው:: ይህን ተከትሎም በ2012 ዓ.ም ምንም እንኳ የተሻለ ቁጥር ያለው ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ ማስገባት ቢቻልም ከቦታ ቦታ ለመጓጓዝ የጸጥታ ስጋት ተፈጥሯል:: በዚህም ሁሉን የማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡ ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርሲቲ ማስገባት አልተቻለም:: ይህም ቀጣዩ የትምህርት ዘመን ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት እንደሚገጥመው ማሳያ እንደነበር ከዚያን ጊዜ በኋላ ባሉ ዓመታት የተመዘገቡ ውጤቶች ማረጋገጫ ናቸው::
አሁንም ድረስ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቀጠሉ ግጭቶች የትምህርት ሥርዓቱን በእጅጉ ፈትነዋል:: የትምህርት ተቋማት በከፍተኛ ደረጃ ለጉዳት ተዳርገዋል፤ ግብዓትን በወቅቱ እና በሚፈለገው ልክ ማሟላት አልተቻለም፤ መምህራንም ሆኑ ተማሪዎች ተረጋግተው መማር ማስተማሩን ማከናወን አልቻሉም::
በተለያዩ አካባቢዎች የቀጠሉ ግጭቶች በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠራቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ አስታውቀዋል:: ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የትምህርት ሚኒስቴርን የ2016 በጀት ዓመትና የአንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን ባለፈው ጥቅምት በገመገመበት ወቅት ነው::
ሚኒስትሩ ችግሩ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ ሲያስረዱ በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት ከነበረባቸው ተማሪዎች መካከል 26 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆኑት በጦርነት፣ በድርቅ፣ በጎርፍ እና መሰል አደጋዎች መምጣት አለመቻላቸው ነው::
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት አመራር መምህርና ባለሙያው ሸጋው ሞላ በበኩላቸው ግጭት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ክፉኛ እንደሚፈትን ገልጸዋል:: ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉና ለጦርነት ዓላማ እንዲውሉ ያደርጋል:: ለተጽኖው ማሳያ ያደረጉትም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሽፋን በእጅጉ እየቀነሰ መምጣቱን ነው::
“ባለፉት ሁለት ዓመታት ሀገሪቱ ካስፈተነቻቸው ተማሪዎች ውስጥ 96 ነጥብ 7 በመቶ ወደ ዩኒቨርሲቲ አልገቡም። 1ሺህ 600 ትምህርት ቤቶችም ያስፈተኗቸውን ሁሉንም አላሳለፉም:: ይህም ለችግሩ ፈጥኖ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ የማንቂያ ደወል ነው” ብለዋል::
በ2013 ዓ.ም እንደ ሀገር 617 ሺህ 991 ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና እንዲወስዱ ተመዝግበው ነበር:: ባጋጠመው የጸጥታ ችግር ግን በሁለት ዙር በተሰጠው ፈተና ከተመዘገቡት ውስጥ ፈተናውን መውሰድ የቻሉ 599 ሺህ 3 ተማሪዎች (96 በመቶ) ብቻ መሆናቸውን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል:: በወቅቱ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ፈተና በሁሉም ትምህርት ቤቶች በሚባል ደረጃ የውጤት መመሳሰልና ግሽበት ስለታየበት የፈተና ውጤቱ ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ መወዳደሪያነት እንዳያገለግል መወሰኑም ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቷል::
ትምህርት ሚኒስቴር በ2014 ዓ.ም ደግሞ 896 ሺህ 520 ተማሪዎች አስፈትኗል:: 50 በመቶና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት 29 ሺህ 909 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸው የውጤት ማሽቆልቆሉ ከዓመት ዓመት እየቀነሰ ለመምጣቱ ማሳያ ነው::
በ2015 ዓ.ም በተሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናም 845 ሺህ 099 ተማሪዎች ተፈትነዋል:: 817 ሺሕ 838 ተማሪዎች ከ50 በመቶ በታች ውጤት ሲያስመዘግቡ የማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡት 27 ሺሕ 267 ተማሪዎች ብቻ ናቸው::
ለውጤቱ ማሽቆልቆል ዋና ምክንያት ሆኖ በብዙኃኑ ዘንድ በስፋት ሲነሳ የነበረው አስተማማኝ ፀጥታ በሌለበት ሁኔታ ተማሪዎች ለፈተና መቀመጣቸው ነበር:: የጸጥታ ስጋቱ ግን አሁንም ቀጥሏል:: በተለይ በአማራ ክልል ከሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ የተከሰተው የሰላም መደፍረስ በክልሉ ከሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች አሁንም ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ ማድረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ዋቢ ነው::
ችግሩ በትምህርቱ ዘርፍ የሚኖርን ሀገራዊ ተወዳዳሪነት ይገድበዋል:: በተለይ ባለፉት ዓመታት በክልሉ ከዓመት ዓመት እየተመዘገበ ያለውን ዝቅተኛ ውጤት ለማሳደግ ከፍተኛ ሥራ እየተከናወነ በነበረበት ወቅት የጸጥታ ችግሩ መፈጠሩ ነገሩን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” አድርጎታል::
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በጎንደር፣ በደብረ ብርሐን እና በሌሎችም ከተሞች ከሚገኙ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው የክልሉ አካባቢዎች ትምህርት ለማስጀመር ከመሥራት ጎን ለጎን በትምህርት ላይ የሚገኙ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለፈተና ዝግጁ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል:: የፈተና አሰጣጥ ውሳኔው የትምህርት ሚኒስቴር ነው ያሉት ኃላፊዋ፣ እስካሁን ትምህርት ያልጀመሩ ተማሪዎች ግን ለፈተና እንደማይቀመጡ ገልጸዋል:: በቀሩት ጊዜያት ትምህርት አስጀምሮ ይዘቶችን በአግባቡ ሸፍኖ ለፈተና ብቁ ማድረግ አለመቻሉን ምክንያት አድርገው አቅርበዋል:: በትምህርት ላይ ያሉትን ግን ለፈተና ዝግጁ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አረጋግጠዋል::
የትምህርት ሚንሥትሩ ፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋ ለውጤቱ ማሽቆልቆል ኩረጃ ስለቀረ ነው ብለው ያምናሉ:: በተለይ ፈተናው በትምህርት ቤት ደረጃ በሚሰጥበት ወቅት ይፈጸም የነበረው የተደራጀ ሥርቆት የተማሪዎችን ትክክለኛ አቅም ለማወቅ እጅግ አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰዋል::
ሚንስትሩ አብነት ጠቅሰው ሲያስረዱ “ፈተናዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርሲቲ መሰጠታቸውን ተከትሎ የተመዘገበው ውጤት እንደ ሀገር የሚያሳዝን ነበር:: ቢሆንም የትምህርት ሥርዓቱ ሥር የሰደደ መሠረታዊ ችግር ያለበት መሆኑን አመላክቷል::” በየዓመቱ እየተመዘገበ ላለው ዝቅተኛ ውጤት ተጠያቂው የትምህርት ሚንስቴርን ጨምሮ ሚዲያው፣ ወላጆች እና ሌሎች አካላት ጭምር ናቸው ብለው ያምናሉ::
ፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋ በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት የመምህራን አቅም ማሳደግ፣ የመጻሕፍት አቅርቦት ችግርን መፍታት፣ የትምህርት መሠረተ ልማትን በሚፈለገው ልክ ማሟላት፣ መምህራን እና ዳይሬክተሮች ከፖለቲካ ሥራ ወጥተው ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ማስቻል ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራም ገልጸዋል::
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) “አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡት ኩረጃ ስለቀረ ነው፤ ለውጤቱ ዝቅተኛ መሆንም ተጠያቂው ሁሉም አካል ነው” ተብሎ በፕሮፌሰር ብርሐኑ የተነሳውን ሐሳብ እንደማይቀበሉት ገልጸል:: “ይልቁንም ሚንስቴሩ ለውጤቱ መበላሸት ሁሉም ተጠያቂ ነው ከማለት ወጥቶ በተሰጠው ኃላፊነት ልክ ‘ችግሩ የእኔ ነው’ ብሎ ኃላፊነት ወስዶ በመሥራት ክፍተቱን ሊያርም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ማረጋገጥ በይደር የሚተው ጉዳይ አይደለም:: የትምህርት ሥርዓቱ ልክ እንደ አሁን አይነት ችግር በሚያጋጥመው ወቅት መማር ማስተማሩ ሳይቋረጥ የነበረን ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል የትምህርት ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ መደገፍ እንደሚገባ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት አመራር መምህርና ባለሙያው ሸጋው ሞላ አስገንዝበዋል:: ቴክኖሎጂ በጸጥታ መታወክ የተቋረጠውን መማር ማስተማር ሁሉም ተማሪ ባለበት በማስቀጠል ተማሪዎችን፣ ወላጆችን እና መምህራንን ከሥነ ልቦና ጉዳት ከመታደጉም ባሻገር ዓለም የምትፈልገው ትውልድ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ጠቁመዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)