“በግእዝ የሦስተኛ ዲግሪዬን ሠርቼ የተመለስሁት ከጀርመን ነው::በወቅቱም ሚዲያዎች ቃለ መጠይቅ አድርገውልኝ ነበር::ዛሬ የራሴን ቋንቋ ጀርመን ድረስ መጥቼ ተምሬያለሁ፤ ነገ ግን አንድ ቀን በሀገሬ አንድ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ የግዕዝ ትምህርት እንዲሰጥ ጥረት አደርጋለሁ፤ ግቡም ዳር እንዲደርስ ያለኝን አቅም ሁሉ እጠቀማለሁ! ብየ ለራሴ ቃል ገብቻለሁ::ቃሌ ወደ ተግባር ተለውጧል፤ አሁን የቀረው ግዕዝን በዶክትሬት ማስጀመር ነው፤ እሱም ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ደርሷል::ግእዝን ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲማረው እፈልጋለሁ::ይህም የነገ የግእዝ መዳረሻ ዋና አላማዬ ነው” በማለት በቁጭት ሐሳባቸውን ያጋሩን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግዕዝ መምህርና ተመራማሪ ሙሉቀን አንዷለም (ዶ/ር) ናቸው::
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግእዝ ዐውደ ጥናትን ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም አካሂዶ ነበር::የኢትዮጵያውያን ጥንታዊ መግባቢያ ቋንቋ የነበረው እና ታላላቅ ምስጢርን ያዘለው ግእዝ በሀገሩ የሚገባውን ክብር ባለማግኘቱ በውጪ ሀገራት መማራቸው ከፍተኛ ቁጭት ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸውን ሐሳብ ያጋሩን በዚያ ጊዜ ነበር::
የኢትዮጵያን ውስጠ ምስጢር በወጉ ለመረዳት የግእዝ ቋንቋ ዋናው መፍቻ ቁልፍ መሆኑን መምህር እና ተመራማሪው ገልጸዋል::ይሁን እንጂ ትልቁ የኢትዮጵያ ሐብት የሆነው ግእዝ በዓለም ላይ በ31 ዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ሀገራት ስለ ኢትዮጵያ ታሪካዊነት እየተናገሩ መሆኑ ቁጭት ውስጥ ሊያስገባ ይገባል ብለዋል::
መምህርና ተመራማሪ ሙሉቀን አንዷለም እንዳሉት “የራሳችንን ሀብት ሌሎቹ አጥንተው ከሚነግሩን እኛው ራሳችን፣ ባለን መፍቻ ቁልፍ በራሳችን ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ማን እንደሆነች፣ ታሪካችን እንዴት እንደሆነ፣ ማንነታችን እስከምን ድረስ እንደሆነ ማወቅ፣ መረዳት እና ማስረዳት ይገባል::“የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም ግእዝ የኢትዮጵያ ሁለመና የሚገለጥበት መሆኑን በመገንዘብ በአሁኑ ወቅት በአንደኛ እና በሁለተኛ ዲግሪ የግእዝ ትምህርት እየሰጠ ይገኛል::እስካሁንም ዘጠኝ ጊዜ አስመርቋል፤ በሦስተኛ ዲግሪ ለማስተማርም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ዘላለም በላይ የሦስተኛ ዓመት የግእዝ ተማሪ ነው::ግእዝ የያዘውን ዕውቀት በደንብ ተጠቅመው ዓለምን ለማወቅ፣ በጥናት እና ምርምርም ቀዳሚ ለመሆን ዛሬ ላይ ከኢትዮጵያ በላይ በርካታ የውጪ ሀገራት ለግእዝ ልዩ ትኩረት እንደሰጡ ተናግሯል::ግእዝን የሚያስተምሩት የግእዝ ቋንቋን ጥቅምና ከግእዝ የሚገኘውን ዕውቀት በቅጡ ስለተረዱ እንጂ ቋንቋውን ፈልገውት እንዳልሆነም ያምናል::እነዚህ ሀገራት በግእዝ የተጻፉ መጻሕፍት በሀገራቸው ኖረው ሳይሆን በሀገር ማሰስም ሆነ በምርምር ሰበብ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መጻሕፍትን በተለያዩ መንገዶች ወስደው መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ቁጭት ውስጥ የሚያስገባ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
ዘላለም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ለግእዝ የሰጠችው ትኩረት መልካም መሆኑን ይናገራል::ግእዝ በጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች ከመሰጠት አልፎ በአማራ ክልል በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካቶ መሰጠት መጀመሩ ግእዝ ትኩረት እያገኘ መምጣቱንና ጠቀሜታውን ከመረዳት የመጣ መሆኑን ያሳያል ብሏል፡፡
ግእዝ በጊዜ ሂደት አፈ ፈት ተናጋሪ እንዲኖረው እና ቋንቋው ወደ ቀድሞ ክብሩ እንዲመለስ ትምህርቱን ከሕጻንነት ጀምሮ መስጠት ይገባል::የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮም ግእዝን በሥርዓተ ትምህርቱ አካቷል::በዚህ የትምህርት ዘመን ተግባራዊ መደረግም ጀምሯል::በዚህ ዓመትም ትምህርቱ ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ በመሰጠት ላይ ነው፡፡
ለመሆኑ የግእዝ ትምህርት በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ተካቶ ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ መሰጠቱ ፋይዳው እስከምን ድረስ ነው? በማለት ለዶ/ር ሙሉቀን ጥያቄ አንስተንላቸው ነበር::ትምህርት የሚሰርጸው ከሕጻንነት ጀምሮ ነው::አሁን ባለው ሁኔታ የግእዝን ፊደል የማያውቅ የማኅረሰብ ክፍል መኖሩን ጠቁመው፤ ከታች እንዲጀመር መደረጉ አማራጭ የሌለው መፍትሔ በመሆኑ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ለምን ግእዝን ያስተምራሉ? ሕዝቡስ ለምን ዋና ፍላጎቱ አድርጎ ማጥናት ፈለገ? ኢትዮጵያውያንስ ለምን ግእዝን ማጥናት አልፈለጉም? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት እና በአጠቃላይ እኛ እንዳናጠናው ለምን ሆነ የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ ግእዝን መማር እንደሚኖርበት አጽንኦት ሰጥተዋል::ግእዝን መማር የሀገርን ታሪክ፣ ወግ፣ ባህል፣ ማንነት… ማወቅ መሆኑንም ተመራማሪው አስታውቀዋል::
“የግእዝ ቋንቋን በመደበኛነት የሚናገረው እና የሚግባባበት የኅብረተሰብ ክፍል የለም“ በሚል ቋንቋው እንደሞተ ለሚናገሩ ግእዝ አሁን ያለበትን ደረጃ ለማወቅ መታየት ያለባቸው መስፈርቶች አሉ::በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልሳን እና ፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዘላለም ልየው ቋንቋ በደፈናው ሞቷል ወይም ተዳክሟል ሊባል እንደማይችል ገልጸዋል::የአፈ ፈትነት ተናጋሪ ቁጥሩ፣ አገልግሎቱ፣ በትምህርትነት መሰጠቱ፣ ሽግግር (ከትውልድ ትውልድ)፣ ልሳነ ክልኤነቱ፣ ዕድገቱ፣ የጽሑፍ ሰነድ መኖር አለመኖሩ፣ የቃላት እና ሰዋሰው መዛባቱ፣ አመለካከቱ /አዝማሚያ ታሳቢ እንደሚደረጉ አንስተዋል::
ዶ/ር ሙሉቀን በበኩላቸው “ዓለም የሞተ ቋንቋ ሊያጠና አይችልም፤ ግዕዝ አልሞተም::ከብዙ ማሳያዎች ውስጥ ቢያንስ የግእዝ ቋንቋ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በመደበኛነት አገልግሎት እየተሰጠበት ይገኛል” ብለዋል::
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ጥንታዊ የግእዝ ጽሑፎች (manuscripts) በመላው ዓለም ጥናት እና ምርምር እየተደረገባቸው መሆኑን ዶ/ር ሙሉቀን አስታውቀዋል::አካሄዳችን ግን “ከሞኝ ጓሮ ሞፈር ይቆረጣል“ አይነት ሆኗል ያሉት ተመራማሪው፤ አሁንም ግእዝ የኢትዮጵያ ማንነት የሚገለጥበት መሆኑን መረዳት እንደሚገባ ነው ያስታወቁት::
ግእዝ ለአንድ ብሔር መግባቢያነት ብቻ የተፈጠረ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ብቸኛው የጋራ ቋንቋ መሆኑን መምህር እና ተመራማሪው አረጋግጠዋል::በመሆኑም የጋራ መግባቢያ የሆነው ቋንቋ እና የኢትዮጵያ ከፍታ የሚገለጥበትን ቋንቋ ለትንሳኤው በጋራ መረባረብ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ግእዝ ከሃይማኖት ቋንቋነት በላይ መሆኑን መገንዘብም ለግእዝ ትንሳኤ መሠረት እንደሚሆን ጠቁመዋል::ምክንያቱም የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ጥበብ፣ ፍልስፍና፣ ምስጢር የሰፈረው እና ተደብቆ የሚገኘው በግእዝ ቋንቋ በተጻፉ ሰነዶች ላይ በመሆኑ ቋንቋውን ከብሔር እና ከሃይማኖት ባሻገር አስቦ መማር እንደሚገባ ገልጸዋል::“የኢትዮጵያ ታሪክ ከሌላ አካል እየመጣ ነው፤ ይህ የሆነው ለግእዝ ትኩረት የሰጡ ሀገራት መጻሕፍትን እየመረመሩ ከመሆናቸው የተነሳ ነው፤ ይህ ሊያስቆጭ ይገባል::ኢትዮጵያዊ ምሁራንን በራሳችን ዕውቀት በማብቃት እና በማፍራት ኢትዮጵያን ማወቅ ያስፈልጋል” ሲሉ ነው መልዕክት ያስተላለፉት::
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሰብዕ ፋካሊቲ ዲን ዋልተንጉስ መኮንን (ዶ/ር) የግእዝ ቋንቋ በኢትዮጵያ ታሪክ እና መንፈሳዊ ቅርስ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የያዘ እንደሆነ ተናግረዋል::ግእዝ ቋንቋ ለዘመናዊው የዕውቀት መዝገብ ሆኖ ዘመናትን መሻገሩን ጠቅሰዋል::በውስጡም ሰፊ የፍልስፍና፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የታሪክ እና የሳይንሳዊ ዕውቀቶችን አካቶ የያዘ ነው::ይህንን ታላቅ ቅርስ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል::ይህም የግእዝ ቋንቋን ለምርምር እና ለትምህርት ክፍት ለማድረግ የተወሰደ ታላቅ ርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል::
ለግእዝ የተሰጠው ትኩረት የኢትዮጵያን ጥናት በዓለማቀፍ ደረጃ የሚኖረውን ተደማጭነት የሚያሳድግ ነው::በግእዝ ቋንቋ ተቀርጾ የሚገኝ ዕውቀት ሰፊ እና ጥልቅ በመሆኑ በዓለም ላይ የሚገኙ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ግእዝን ዋና የትኩረት አቅጣጫቸው ማድረጋቸውን ጠቁመዋል::የአሁኑ ትውልድ የመንፈሳዊ እና የታሪካዊ ቅርስ ምስጢር የሚገለጥበትን ግእዝ ከዘመናዊ ትምህርት ጋር አቀናጅቶ እንዲማር መደረጉ በጥልቀት ለመማር እና ለመመራመር በር የሚከፍት እንደሆነ ገልጸዋል::ለግእዝ የተሰጠው ትኩረት የበለጠ እንዲሰፋ ለማድረግም የሁሉም ርብርብ ወሳኝነት አለው::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የህዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


