የውጭ ግንኙነት እና የኢትዮጵያ ተሰሚነት

0
351

ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን የሥነ መንግሥት ታሪክ አላት። በማንም ሀገር ቅኝ አልተገዛችም፤ ነጻነቷንም በልጆቿ ብርቱ ክንድ አላስደፈረችም። ከራሷም ባለፈ የአፍሪካ ጥቅም አስከባሪ ሆናም ትጠቀሳለች:: በደርግ ዘመነ መንግሥት በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ የደኅንነት ምክትል ሚኒስትር እና የኢንተለጀንስ ከፍተኛ ባለሙያ የነበሩት አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር) ሪፖርተር ጋዜጣ ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም ይዞት በወጣው ዕትሙ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ አቅምና ቁመና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን ነፃ ለማውጣት እና ለማደራጀት እንዲሁም የአፍሪካ አንድነትን ለማቋቋም ትልቅ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል:: ኢትዮጵያ በተለይ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ለበርካታ የአፍሪካ ፀረ ቅኝ ግዛት እና ፀረ አፓርታይድ እንቅስቃሴዎች ፖለቲካዊ ድጋፍ ሰጥታለች:: በቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኀይለ ማርያም ዘመን በደቡብ አፍሪካ፣ በዚምባቡዌና፣ በናሚቢያ ለነበሩ ነፃ አውጪ ድርጅቶች ወታደራዊ ሥልጠና፣ ቁሳዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ርዳታዎች ስለማድረጓ ታሪክ መዝግቦታል።
የጥቁር ሕዝብ ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ የበርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ድርጅቶች መሥራችም ናት:: ለአብነት የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በመመስረት ደማቅ ታሪክ መጻፏንም ታሪክ በማኅደሩ ሰንዶት ይገኛል:: በተጨማሪም ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሰነዶች፣ ስምምነቶች እና ኮንቬንሽኖችንም አጽድቃለች:: እነዚህ ሁሉ እውነታዎች ሀገሪቱ ከፍ ያለ ተሰሚነት እና ተደማጭነትን እንድታተርፍ አድርጓታል።
ይሁን እንጅ ይህንን የታሪክ ተሰሚነቷን እና ተደማጭነቷን እንድታጣ ከጥንት እስከ ዛሬ ከፍተኛ ሙከራ ተደርጎባታል:: ጥንቱንም ለጠላት እጅ ያልሰጠችው ኢትዮጵያ አሁንም ነጻነቷንና በዓለም አደባባይ ያላትን ተሰሚነት አስቀጥሎ ለመጓዝ፣ የሚገጥሟትንም ዓለም አቀፍ ጫናዎች ለመቋቋም የውጭ ግንኙነትን (ዲፕሎማሲ) ዋና መሣሪያዋ በማድረግ እየሠራች ትገኛለች::
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ዋና ማጠንጠኛ ብሄራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ፣ የዜጎችን መብት እና ክብር ማስከበር እንዲሁም የኢትዮጵያን ታሪክ የሚመጥን ተደማጭነቷን ማስቀጠል መሆኑን የቀድሞው የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ደመቀ መኮንን አስታውቀዋል:: በዜጋ ተኮር፣ በኢኮኖሚ፣ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን መድረክም ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር እየተጋች የምትገኝ ሀገር ናት::
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ታሪክ ጅማሮውን የሚያደርገው ንግሥተ ሳባ ወደ እየሩሳሌም ካደረገችው ጉዞ ነው:: ንግሥተ ሳባ ወደ እየሩሳሌም ያደረገችው ጉዞ የዲፕሎማሲ ሥራ ነው የሚለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ወዳጅ የማብዛት፣ የንግድ ዕድሎችን የመፍጠር እና ኢትዮጵያን ከሌላው ዓለም ጋር የማስተሳሰር ሂደት ጅማሮ መሆኑን ያነሳል:: የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ታሪክ የሺህ ዓመታት ጉዞ ይኑረው እንጂ በጉልህ የሚነሳው ግን የ116 ዓመታት ጉዞው ነው::
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ በዋናነት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለሚኖር ግንኙነት ልዩ ትኩረትን ይሰጣል:: ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት እየሻከረ የመጣ ይመስላል። ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር አልፋ መግባት፣ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ታድሶ የነበረው ግንኙነት ዳግም መቀልበሱ፣ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የፈረመቸው የባህር በር የማግኘት ስምምነት በሶማሊያ መንግሥት ተቀባይነት አለማግኘቱ ለግንኙነቱ እየሻከረ መሄድ ማሳያዎች ናቸው::
ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉት አስማማው ቀለሙ ዶ/ር) በተለይ የውስጥ ሰላም ለጠንካራ ዲፕሎማሲ መሰረት መሆኑን አንስተዋል:: ከዚህ በተቃራኒ የሚኖር የጸጥታ ችግር ግን ለሀገራት የውጭ ግንኙነት መሻከር ቀዳሚ ምክንያት እንደሚሆን አብነት እያነሱ ያስረዳሉ:: ሶማሌ በኢትዮጵያ ሦስት ጊዜ ወረራ ፈጽማለች:: ሁሉም ወረራ የውስጥ መዳከም በነበረበት ጊዜ የተፈጸመ ነው:: የእነመንግሥቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በተደረገበት ወቅት ሶማሌ የመጀመርያውን ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ ፈጽማለች:: በደርግ ጊዜም የመንግሥት ግልበጣ ሲሞከር መንግሥት እና ወታደሩ ተዳክሟል ብለው በማሰብ የተፈጸመ እንደሆነ ገልጸዋል::
ሱዳን የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ለወረራ ስትዘጋጅ እንደነበር አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር) ያነሳሉ:: ለዚህም ማስረጃቸው ሱዳን 58 ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቃ በመግባት የጦር ኀይል ማስፈሯን በመጠቆም ነው:: አሁንም ቢሆን ሱዳን በርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መሆኗ እንጂ ኢትዮጵያ ገብታ ወረራ አትፈጽምም ተብሎ እንደማይታሰብ ያምናሉ::
በኢትዮጵያ አሁንም ድረስ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ግጭቶች ቀጥለዋል:: ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በተለያዩ ጊዜያት እልባት ባላገኙ ግጭቶች ንጹሀን ለከፋ ጉዳት እየተዳረጉ መሆኑን በተደጋጋሚ አስታውቀዋል:: መንግሥት ደግሞ በጦርነቱ ንጹሀን ሰለባ እንዳልሆኑ በተደጋጋሚ እየገለጸ ነው:: በሀገር ውስጥ ያሉ ግጭቶች በአጭር ጊዜ መፍትሄ ካልተሰጣቸው የኢትዮጵያ ተሰሚነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲገባ ሊያደርገው እንደሚችል እየተሰጋ ነው::
ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር የወደብ ባለቤት ለመሆን የትብብር ስምምነት ብትፈጽምም የሶማሊያ መንግሥት ግን በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እስከማወጅ የሚደርስ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል:: የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችም አጋጣሚውን እንደ መልካም በመውሰድ ከሶማሊያ ጎን በመሆን እየገፋፉ እንደሚገኙ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው::
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም “ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን ከአፍሪካ መዲና እስከ ዓለም መድረክ” በሚል መሪ ቃል የዲፕሎማሲ ሳምንት ዓውደ ርዕይ በሳይንስ ሙዚየም ባካሄደበት ወቅት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ብዙ ውጣ ውረድን አልፎ ዛሬን መድረሱን፣ ያለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ክፉኛ የተፈተነበት መሆኑን አስታውቀዋል::

ኢትዮጵያ የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ከምዕራቡ ዓለም እና ከዓለም አቀፍ ተቋማት የገጠማትን ጫና እና ከህዳሴው ግድብ ድርድር ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ችግሮችን በአሸናፊነት የተወጣችበትን መንገድ ለሐሳቡ ማጠናከሪያ እንመልከት:: የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ያልተዋጠላቸው ግብጽ እና ሱዳን ግንባታውን ለማስተጓጎል ኢትዮጵያ ከየትኛውም ወገን የገንዘብ ድጋፍ እንዳታገኝ ከማድረግ ጀምሮ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጎን እንዳይሰለፉ ለማድረግ ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም:: ድርድሩም ከአፍሪካ ሕብረት ውጭ ባሉ አካላት እንዲታይ የነበራት አካሄድ የግብጽ እባባዊ አካሄድ ሆኖ ታይቷል::
የኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ተሰሚነት እና ተደማጭነት ዛሬም ለመቀጠሉ ውጥረቱን በሰላማዊ መንገድ ያውም “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚል መርህ እንዲፈታ ያደረገችበት ጥረት ነው:: ጥረቱም ፍሬ አፍርቶ ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት እየታየ ነው:: በእነዚህም ድርድሮች ኢትዮጵያ ከግብፅ እና ሱዳን በስተቀር አብዛኛዎቹን የናይል ተፋሰስ ሀገራት ከጎኗ ማሰለፍ ችላለች:: ግድቡም በራስ አቅም መገንባቱን ቀጥሎ አራተኛው የውኃ ሙሌት በስኬት ተጠናቋል::
ኢትዮጵያ የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ከበርካታ አቅጣጫ የተደረገባትን ጫና ያመከነችበት መንገድ ሌላው የዲፕሎማሲ ስኬት ማሳያ ሆኖ ይነሳል:: በተለይ ኢትዮጵያ ውስጣዊ አንድነቷን ለማስጠበቅ ከሰሜን ኢትዮጵያ የተሰነዘረባትን ጥቃት ለመመከት ያደረገችው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በምዕራቡ ዓለም ከፍተኛ ጫና እንዲደርስባት ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ ጊዜያት ያወጣቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ::
ዓለም አቀፍ ሚዲዎች ሳይቀሩ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት የተዛባ መረጃን በማሰራጨት ኢትዮጵያ ከመሰረተቻቸው መድረኮች ሁሉ ለማግለል ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል:: አሜሪካ ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ሀገራት ከተሰጠው ከቀረጥ ነፃ የገበያ እድል (African Growth and Opportunity Act) ተጠቃሚነት ዝርዝር ውስጥ መፋቋ የጫናው ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል::
ያም ሆነ ይህ ኢትዮጵያ ሁሉንም ጫናዎች ተቋቁማ ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ቋጭታለች፤ የፀጥታ ችግሩ በተለያዩ አካባቢዎች ቢቀጥልም በሰሜኑ ጦርነት ቀጥተኛ ተሳታፊ የነበሩ አካባቢዎችን መልሶ የመገንባትና የማቋቋም ሥራ መጀመሩ ለስምምነቱ ተግባራዊነት ማሳያ ሆኖ እንደሚነሳ መንግሥት በተደጋጋሚ አስታውቋል::
የኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ያላት ተደማጭነት ዛሬም ቀጥሎ በቅርቡ በምጣኔ ሐብት እና በመደመጥ አቅሙ እያደገ የመጣውንና ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካን ያሰባሰበውን ህብረት /ብሪክስ/ ተቀላቅላለች:: ይህም ለኢትዮጵያ ቀጣይ የዲፕሎማሲ ጉዞ ተሰሚነትና ተደማጭነት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ታምኖበታል::
በቅርብ ጊዜ የተገኙ የዲፕሎማሲ ውጤቶች ሀገሪቱን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በፀጥታና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ወደ ከፍታ እንደሚያሸጋግሯት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ስምምነቱን መነሻ አድርገው በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል::
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በታሪክ ሂደት ስሟን በበጎ የሚያስጠሯትን የዲፕሎማሲ ስኬቶች ያስመዘገበች፣ በመሪዎቿ አማካኝነት ተደማጭነቷን ከፍ አድርጋ ዘመናትን የተሻገረች መሆኗን ገልጸዋል:: የውጭ ግንኙነት ሥራውን ከወቅቱ ጋር የሚራመድ እንዲሆን በማድረግ መጓዝ ለወደፊቱ የተሻለ ተስፋ ይዞ እንደሚመጣ አመላክተዋል::
በዓለም አቀፍ ደረጃ ተገቢውን ተቀባይነት በማግኘት ተደማጭነትን ከፍ በማድረግ ወደ ፊት ለመጓዝም ሆነ ዕድገትን ለማረጋገጥ አስቀድሞ ውስጣዊ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል:: የዛሬ እና የነገ የዲፕሎማሲ ሥራን ለማጠናከር ትውልዱ የራሱን አሻራ ማሳረፍ እንደሚጠበቅበትም አስታውሰዋል::
ኢትዮጵያ ለዘመናት የምትታወቅበትን የውጭ ግንኙነት ሥራ አሁንም አጠናክራ መቀጠል እንደሚኖርባት አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር) ጠቁመዋል:: የአመራሩን እና የሕዝቡን ግንኙነት ማጠናከር፣ መሪውን የሚደግፍ ሕዝብ መፍጠር፣ ሕዝቡ ለኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ተሰሚነትና ተደማጭነት በአንድነት የሚቆም እንዲሆን ማስቻል የውጭ ጉዳይ ሥራው ጠንካራ እና የታፈረ ሆኖ እንዲዘልቅ ያደርጋል::
የሀገር ስትራቴጂክ ሀብትና ጂኦግራፊካዊ አቀማመጥን ለጠንካራ የውጭ ግንኙነት ሥራ መጠቀም፣ ለዚህም በውጭ ሀገር የማይገኙ ማዕድናት፣ የባህር ወደብና መሰል ሀብቶች ሲኖሩ መልካም ግንኙነትን መፍጠርና ማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባም አስማማው (ዶ/ር) ጠቁመዋ:: የውጭ ደጋፊ ኀይልን ማብዛት፣ ይህም በቀጣናውና በዓለም አቀፋዊ ኀይሎች ዘንድ የፖለቲካ ተፅዕኖ ሲኖር የመደገፍ ዕድልን እንደሚያሰፋ ያምናሉ::

(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ። See less

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here