የተወለዱት 1926 ዓ.ም በቀድሞው በጌምድር ጠቅላይ ግዛት በደብረታቦር አውራጃ ደራ ወረዳ ዴይማ ሚካኤል ነው:: እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የአብነት ትምህርት ተከታትለዋል:: የሥራ ሰው ናቸው። ሥራን ባሕል ያደረጉ መሸሸጊያ፣ ዋሻ፣ የተቸገረን የሚረዱ፣ አስታራቂ እና ደግ በልጅ አስተዳደግ የተዋጣላቸው መሆናቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ይመሰክራሉ:: የዚህ እትም እንግዳችን በባሕር ዳር ከተማ ለረጅም ዓመታት የኖሩት እና በከተማው ነዋሪዎች በስፋት የሚታወቁት አሥር አለቃ ሁናቸው አያሌዉ ሰንደቁ ናቸው::
ወደ ባሕር ዳር ከተማ መቼ መጡ? በጊዜው ባሕር ዳር ምን ትመስል ነበር?
በ1949 ዓ.ም ነበር ወደ ባሕር ዳር ከተማ የመጣሁት፤ በዛን ወቅት ትንሽ መንደር የምትባል ነበረች። ሕንጻ እንኳን በቅጡ የላትም። በ1940ዎቹ መጨረሻ ከአብዛኞቹ የሀገራችን ከተሞች በአንጻራዊነት ባሕር ዳርን የበለጠ ዘመናዊነትን ሊያላብሳት የቻለ የከተማ ፕላን ተሰርቶላታል:: ይሁንና ፕላኑ ዝርዝር እና ደረጃውን የጠበቀ የከተማ ፕላን መስፈርቶችን ያሟላ አልነበረም:: ፕላኑ የያዘው የገበያ ቦታን እና ጠባብ እንዲሁም አነስተኛ መንገዶችን ነበር:: ከነዚህ መንደሮች ውስጥ በተለምዶ ቀበሌ አምስት እና ስድስት እንዲሁም አራት በከፊል ይገኙበታል::
1950ዎቹ መጀመሪያ ባሕር ዳር መስፋት እና የተለያዩ መሠረተ ልማቶች መገንባት የጀመሩበት ዋነኛ ጊዜ ነው:: ለአብነትም በ1951 በነዳጅ የሚሠራ መብራት ለስድስት ሰዓታት ማግኘት ጀመረች:: ከአምስት ዓመታት በኋላም ከጢስ አባይ ፏፏቴ ከሚመነጨው ኃይል በመሳብ የ24 ሰዓት ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆናለች:: በ1953 ደግሞ ንጹህ የመጠጥ ውኃ በቦኖ ለህዝቡ ማዳረስ ተጀመረ::
በዚህ ጊዜ ለከተማዋ እድገትን ያጎናጸፉ እና ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ መሰረተ ልማቶች መገንባት ቀጥለዋል:: ባሕር ዳርን ውብ ገጽታ ያላበሷት እና የከተማዋ ገጽታ መለያ መሆን የቻሉት ዘንባባዎች በዚህ ወቅት ነው የተተከሉት::
ከደራ ወረዳ እንደመጣሁ የቄሰ ገበዝ ግሩምን ልጅ አግብቼ ቀበሌ አምስት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነበር የምኖረው:: በመንገድ ሥራ ምክንያት መጀመሪያ የሠራሁት ቤት ፈረሰብኝ:: የትዳር አጋሬ ቤተሰቦቼ ባለ ርስት ስለነበሩ ሰፊ መሬት ሰጡኝ:: በዚያም ለረዥም ጊዜ ኖሬያለሁ:: በወቅቱ ቤት የሠራሁበት እና የያዝኩት ቦታ ሰው ስለሌለበት የሁናቸው አያሌው እርድ /የተፋሰስ መውረጃ/ ተባለ:: እርዱ ጣሊያን የጎረደው ነው::
ደቄ መንደር፣ ቁልቋል ሜዳ፣ ጎርደማ የሚባል ቦታ ነበር:: ያንን ሁሉ እያረስኩ እና ከከተማ የሚመጣውን ቆሻሻ ግብርና በሰጠኝ ጋሪ መጎተቻ እያመጣሁ እንደማዳበሪያ ማሳው ላይ እየደፋሁ አለማ ነበር:: ዱባው፣ ማሽላው ዳጉሳው ስፍር ቁጥር የለውም:: ቤቴም ስምንት በስምንት ነበር:: ከጣና ሐይቅ ውኃ በበርሚል በቶዮታ መኪና እየጫንኩ አጠጣለሁ። በዛን ሰዓት መኪና የሚባል አንድ ወይ ሁለት ቢገኝ ነው።
በባሕር ዳር እድገት ውስጥ ጣሊያናዊያን እና ጀርመኖች ድርሻ ነበራቸው፤ ጀርመኖች መንገድ በመቀየስ የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል:: በዚያን ወቅት በመቀየሻ መሳሪያ ከሩቅ ሆነው ይመለከታሉ፤ ዥንጉርጉር እንደ ብረት ያለ ቋሚ እየቸከልኩ ማሳየት ነበር የኔ ሥራ:: ብዙ መንገዶችን አብሬ ሰርቻለሁ:: መጀመሪያ በአውሮፕላን ፎቶ ግራፍ ይነሳል። አለች አንድ ትንሽ አውሮፕላን ዞራ ዞራ ያነሳችውን ለመሬት መሐንዲስ ትሰጣለች፤ መሐንዲሱ በመቀየሻ መሳሪያው እያየ ፕላኑን ያወጣል። ከዛ መንገድ ተቆፍሮ ይሠራል:: አብዛኛው መንገድ የኮሮኮንች ነበር::
ቀጥሎ በዋናነት የዐፄ ቴዎድሮስ ስታዲየምን ተቆጣጣሪ (ፎርማን) ሆኜ አሠርቻለሁ:: በብዙ ድካም የተሠራ ነው፤ በወቅቱ ፎርማን ነበርኩ:: አራት ፊያት ድንጋይ የሚያመላልስ መኪና እና 202 የቀን ሠራተኛ እየተቆጣጠርኩ አሠርቸዋለሁ:: በ1960 ዓ.ም ተጀምሮ በ1966 ዓ.ም ነበር የተጠናቀቀው:: በወቅቱ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በምረቃ ወቅት ተገኝተዋል::
በግንባታው ጊዜ አንድ ሲኞር ላላታ የሚባሉ ጣሊያናዊ ነበሩ:: ግንብ በቱንቢ የሚለኩ ባለሙያ ነበሩ:: በወቅቱ ለቀን ሠራተኛ አምስት ብር ነበር የሚከፈለው። እናም የቀን ሠራተኛውን አንድ አንድ ብር እየተቀበሉ አስቸገሩ። 62 ግንበኛ ከተቀበሉ 62 ብር በቀን ያገኛሉ፤ በዛን ጊዜ ይህ ብር በጣም ብዙ የሚባል ነበር፣ ግንበኛውም ሥራውን ትቶ ሙስና እየሰጠ ቁጭ ብሎ መዋል ጀመረ:: ስለሆነም በዛን ዘመን የባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ ለነበሩት ፊታውራሪ ሃብተ ማርያም ወልደ ኪዳን አቤቱታ አቀረብኩ::
ፊታውራሪ ሃብተ ማርያም ወልደ ኪዳን ጌታቸው የሚባል መሐንዲስ ልከው ለሲኞር ላላታ ማስጠንቀቂያ አስነገሩ:: አቶ ጌታቸውም “ሲኞር ላላታ ግንብ ሲጣመም በቱንቢ ለክተው ማስተካከል እንጂ ሌላ ሥራ የለወትም፤ ሠራተኛ መቅጠር ማስወጣት የሚችል ሁናቸው ነው” ብሎ አስታገሳቸው:: እሳቸውም ደንግጠው ትንሽ ቀን አኮረፉኝ::
ቆይተው አንድ ቀን “አቶ ሁናቸው እኔ ቢራ ይገዛ። እርስዎ ይጠጣ” አለኝ፤ አማርኛ በደንብ አይችልም፤ ማባበያ መሆኑ ነው፤ ለግዜው “እሺ” አላልኩም፤ በስንት ልመና “እሺ” ብየ ተጋበዝኩ:: በወቅቱ በእግሬ ነበር ከሥራ ወደ ቤት የምመላለስ፣ ሮቨር የሚባል ውኃ የመሰለ ጥቁር ሳይክል ገዛሁ:: በዚያ እየተመላለስኩ ስቴዲዮሙን አሠራሁ::
ስታዲየሙ ተሰርቶ ሲያልቅ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በክብር እንግድነት መጡ፤ ፊታውራሪ ሃብተ ማርያም ወልደ ኪዳን የስቴዲየሙን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የከተማውን የመሠረተ ልማት ግንባታ ሪፖርት አቀረቡ:: “ውለታህን የሚመልስልህ እግዚአብሔር ነው፤ እኛ አይደለንም” በማለት በሥራው መደሰታቸውን ገለጹ::
ሰፊ ርስት እንዳለዎት ይነገራል እንዴት አገኙት?
እናት እና አባት ሲያረጁ እነሱን መተው እና ጥሎ መብላት ነውር ነው:: እናት እና አባቴ ኖረው ኖረው ሲያረጁ የሚንከባከባቸው አጡ:: እነሱ ወዳሉበት ሄጄ መሬታቸውን አስጠምጄ አሳርስ ነበር:: የምትንከባከባቸው ሴትም ቀጥሬ እጦራቸው ነበር:: እነሱ ሲሞቱ ርስታቸውን ለእኔ ሰጡኝ በሕይወት እያለ ከጎጃም መጥቶ ስለጦረን ብለው ነው የሰጡኝ:: በኋላ መሬት ሽግሽግ በሚል ብዙ መሬት ተወሰደብኝ:: ከመንግሥት ጋር ተጣላሁ፤ በዚህ ሸፍቼ ጫካ ገባሁ:: ዘመድ “ተው! ተው!” ብሎ ተማጸነኝ። “እሺ” ብየ ተመለስኩ፤ መንግሥት የተለያየ ምርመራ ካካሄደ በኋላ ትንሽ ታስሬ ተፈታሁ:: ከ10 ዓመታት በኋላ በእልህ አስጨራሽ ሙግት አሸንፌ ተፈታሁ፤ ያንን ቦታ አስመለስኩ::
ዘመናዊ ትምህርት ጀምረው ነበር?
አዎ! በዐፄ ሠርፀ ድንግል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርት ጀምሬ ነበር። በወቅቱ ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ፤ በሁሉም ትምህርቶች ጥሩ ውጤት በማስመዝገቤ አስተማሪዎቼ ይወዱኝ ነበር:: የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት እና ውድድሮች ላየ ሳይቀር ጥሩ ተሳትፎ ነበረኘ:: ነገር ግን ቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆኔ ከሥራው ጋር አልሄድልኝ አለ:: በመሆኑም እስከ አራተኛ ክፍል ከተማርኩ በኋላ ትምህርቱን አቋርጨ ወደ ከብት ማርባቱ እና ግብርናው ፊቴን አዞርኩ::
በስምዎት የሚጠራ መንገድም አለ ይባላል?
ወላጆቼ እድሜ እየተጫናቸው ሲመጣ እነሱን መጦር ነበረብኝ:: ቀድሞ ከተወለድኩበት ዴይማ ሚካኤል ኮኮታ ማርያም የምትባል ሌላ ቦታ ኑሯቸውን አድርገው ነበር:: ከባሕርዳር ተነስቸ ወደ አሉበት ለመሄድ መንገዱ ጥርጊያ የወጣለት ባለመሆኑ አስቸጋሪ ነበር:: ከላይ እንዳልኩት ቶዮታ መኪናየን ይዤ ነበር ወላጆቼ ወዳሉበት ለማቅናት የተነሳሁት::
አካባቢው ምንም ቅያስ መንገድ የሌለው በመሆኑ አስቸጋሪ ነበር:: ወቅቱ ሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ራሷን በራሷ መርዳት አለባት የሚል መርሆ ወጥቶ ነበር:: ስለዚህ የአካባቢውን ገበሬ ሰብስቤ እያስቆፈርኩ እና ቁጥቋጦ እያስነቀልኩ እንዲሁም ጋራ እየናድኩ መንገድ አስወጣሁ፤ ከወላጆቼም ደረስኩ::
እኔ ባስወጣሁት መንገድ ደግሞ የጤና ባለሙያዎች እየገቡ የወባ ወረርሺኝ መከላከያ እርጭት እና መድሐኒት ማድረስ ተቻለ:: አካባቢው በወባ የተጠቃ ነበር፤ “ማን አሠራው?” ሲባል “ሁናቸው ነው” ተባለ፤ “ከዚያ ፍየሉ በጉ ወዴት ሄደ?” ሲባል “በሁናቸው መኪና መንገድ ነው የሄደ” እየተባለ “የሁናቸው መንገድ” የሚል ስያሜ ተሰጠው:: 35 ኪሎ ሜትር ይሆናል፤ በዚያው መንገድ እየተመላለስኩ ለእናት እና አባቴ ባሕር ዛፍ ወስጀ ስምንት በስምንት ስፋት ያለው ቤት ሠራሁላቸው፤ የተለያዩ ፍራፍሬዎችንም ተከልኩላቸው፤ እነሱ ሲያልፉ ያንንም ለእኔ አወረሱኝ::
ይቀጥላል
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም