የዓለም አሰላለፍ እየለየ ነው

0
68

ሀገራት በጂኦፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በወታደራዊ እና በሌሎችም መስኮች ያሏቸው ጥምረቶች፣ ተቃርኖዎች እና ስትራቴጂዎች የሚገለፁት በዓለም የኀይል ሚዛን አሰላለፍ ነው:: በዚህ ረገድ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና  ደቡብ አፍሪካ /ብሪክስ/ን በመሳሰሉ ተቋማት የዓለም የኀይል ሚዛንን እንደገና ለመቅረጽ መሥራት ከጀመሩ ውለው አድረዋል:: አሜሪካ እና ምዕራባዊያን ደግሞ ኔቶን እና ሌሎች ጥምረቶችን በመጠቀም ኀያልነታቸውን እና ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውን ለማስጠበቅ ጥረት ያደርጋሉ::

ህንድ እና ቻይና ባላቸው መጠነ ሰፊ የድንበር አለመግባባት፣ ህንድ ከደመኛዋ ፓኪስታን ጋር ቻይና ያላት ገደብ የለሽ ትብብር ብሪክስን ወደ ወታደራዊ ጥምረት እንዳያሸጋግሩት ፈተና ሆኖባቸው ቆይቷል። ምዕራባውያን ቻይናን በየብስ ማጥቃት ቢፈልጉ ህንድ መተኪያ የሌላት ስትራቴጂክ ሀገር ከመሆኗ የተነሳም አንድ እጇ እና እግሯ በምዕራባውያን የተለያዩ ስትራቴጂክ ጥቅሞች የታሰረ ነው።

የሆነው ሆኖ ከኢራን እና እስራኤል ጋር ፊት ለፊት ያለው አሰላለፍ የሚከተለውን ይመስላል። ቡድን 1:-ኢራን፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ፓኪስታን፣ ሰሜን ኮሪያ እና ሌሎች ሀገራ፡- እነዚህ ሀገራት ብዙውን ጊዜ በጋራ ጂኦፖለቲካዊ ፍላጎቶች (ምዕራባዊ ተፅዕኖን መቃወም) የተቆራኙ ናቸው:: ከዚህ በመነሳት የአንዱ መጠቃት የራስ ጥቃት አድርገው ይወስዱታል። የምዕራባውያን (የአሜሪካ) የበላይነትን በመቃወም ባለብዙ ዋልታ የዓለም ኀይል ሚዛን ግንባታን ይደግፋሉ። ይሁንና የሚፈለገው ተጋዳዳሪ የጋራ ወታደራዊ (ተቋም) ያልመሰረቱ በመሆናቸው በአብዛኛው መደጋገፋቸው በጀርባና በመግለጫ ነው።

ቡድን 2፡- እስራኤል፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ አዘርባጃን ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን እና ሌሎች ሀገራት፡- ይህ የምዕራባዊ እሴቶች ላይ የተመሰረተው ኃይል የአሜሪካ እና የምዕራባዊያን የበላይነትን ለማስቀጠል የተዋቀረ ነው:: በግልጽ የሚደጋገፍ፣ ተቋማዊ እና የዳበረ ትስስር ያለውም ነው። በዚህ ቡድን አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ በኔቶ፣ በተባበሩት መንግሥታት እና በሌሎች ተቋማት በኩል የዓለም ሥርዓትን እየመሩ ይገኛሉ::

እስራኤል በበኩሏ በመካከለኛው ምሥራቅ የደህንነት ስትራቴጂያቸውን እና የኢኮኖሚ ጥቅሞቻቸውን በአሜሪካ ድጋፍ ታጠናክራለች። ህንድ እና አዘርባጃን በበኩላቸው በክልላዊ ፍላጎቶች (ቻይናን የመግታት እና የኢራንን ተፅዕኖ በመቀነስ) ምዕራባውያንን በመደገፍ በተለያዩ መንገዶች ተጠቃሚነትን ያገኛሉ።

ቡድን 3 – ገለልተኞች፡- ቱርክ እና ብራዚል፡- እነዚህ ሀገራት በወታደራዊ እና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የተሻለ ቁመና ላይ የሚገኙ ናቸው። በመሆኑም በጥቅሞቻቸው ላይ የተመሰረተ ገለልተኛ ፖሊሲ ያራምዳሉ። ምንም እንኳን ቱርክ የኔቶ አባል በመሆኗ ብራዝልም በጂኦግራፊ አቀማመጧ ይበልጥ ለምዕራባውያን ብታጋድልም የብሪክስ አባል በመሆኗ የበለጠ ጥቅም ካገኙ ከፈለጉት ኃይል ጋር የመቆም እና ወሳኝ ተፅእኖ የመፍጠር አቅማቸው ከፍተኛ ነው። በቡድን 1 እና 2 መካከል የኃይል ሚዛንን ለማጠናከር የሚያስችል ደረጃ ላይ የሚገኙም ናቸው::

ቡድን 4 – ደጋፊ ኢራን (ገለልተኛ) ኳታር እና ኢራቅ፡- ሁለቱ ሀገራት ከኢራንም ከምዕራባውያን ጋርም ተቀራርበው ይሠራሉ:: በተለይም በነዳጅ ኢኮኖሚ የበለፀገችው ኳታር በኢራን እና በምዕራባውያን መካከል ገለልተኛ ሚና ትጫወታለች:: ኢራቅ በበኩሏ በአብዛኛው በኢራን ተፅዕኖ ሥር የወደቀች ብትሆንም ከአሜሪካ እና ከሌሎች የአረብ ሀገራት ጋርም ግንኙነትቷን እያዳበረች መጥታለች:: የሁለቱ ሀገራት ሚዛን ይበልጥ ወደ ኢራን ያጋደለ ነው:: በተወሰኑ ጉዳዮች ግን ገለልተኛ ፖሊሲን ይከተላሉ::

አሜሪካ ይገዳደረኛል ብላ የፈራችውን ብሪክስ በተለያዩ አጋጣሚዎች ስታስጠነቅቅ ቆይታለች:: የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 አባላትን ካቀፈው የብሪክስ ጥምረት ፖሊሲዎችን ወግነው ከአሜሪካ ጥቅም የሚጻረሩ ሀገራት ተጨማሪ 10 በመቶ ታሪፍ እንደሚጣልባቸው አስጠንቅቀው ነበር። “የብሪክሰ ጥምረት ፀረ-አሜሪካ ፖሊሲዎችን የሚደግፉ ማንኛውም ሀገራት ተጨማሪ 10 በመቶ ታሪፍ ይጠብቃቸዋል። በዚህ ፖሊሲ በልዩ ሁኔታ የሚቀር የለም” ሲሉ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስፍረው ነበር።

ትራምፕ ከብሪክስ ጥምረት ጋር በሚወግኑ ሀገራት ላይ ታሪፍ እጥላለሁ ያሉት፤ የጥምረቱ አባላት የአሜሪካን የታሪፍ ፖሊሲዎች ከመተቸት በተጨማሪ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እንዲሁም ዋነኞቹ መገበያያ ገንዘቦች ላይ የወጡ ተመኖች ማሻሻያ እንዲደረጉ መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው። ትራምፕ፤ ቻይና፣ ሩሲያ እና ሕንድን ጨምሮ የምዕራቡን ዓለም የበላይነት ለመገዳደር እና ፍትሐዊ ዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፍ እንዲሰፍን በሚል ተመሥርቷል የተባለውን ብሪክስን በተደጋጋሚ ሲነቅፉ ተደምጠዋል።

ብሪክስ ከመሥራቾቹ ከብራዚል፣ ከሩሲያ፣ ከሕንድ፣ ቻይና እና ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩትን አረብ ኤምሬቶች በአባልነት በመጨመር ጥምረቱን አስፍቷል።

የብሪክስ አባል አገራት ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ ይሸፍናሉ። በብራዚሏ የሪዮ ዲጄኔሮ የሁለት ቀናት ጉባዔ ያደረጉት የብሪክስ መሪዎች በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም ጥምረቱ በዓለማችን እየተባባሱ ለመጡት የንግድ ግጭቶች እና የጂኦፖለቲካል ውጥረቶች የዲፕሎማሲ መድረከ እንዲሆን አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የብሪክስ አባል ሀገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች ባወጡት መግለጫ ታሪፍ ለዓለም አቀፍ ምጣኔ ሃብት ስጋት ሆኗል ሲሉ የተቹ ሲሆን፤ “በዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ አና የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ እርግጠኛ አለመሆንን አስከትሏል” ብለዋል።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም ከአሜሪካው ዶላር ጋር ተፎካካሪ መገበያያ ገንዘብ የብሪክስ አባል ሀገራት መጠቀም ቢጀምሩ 100 ፐርሰንት ታሪፍ እንደሚጥሉ አስጠንቅቀው ነበር። እስካሁን ድረስ አሜሪካ የታሪፍ ስምምነቶችን የደረሰችው ከዩናይትድ ኪንግደም እና ከቬትናም ጋር ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር የተደረሰው ስምምነት አሜሪካ የምታስገባቸው ብረቶችን ያካተተ አይደለም። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኛዎቹ ሀገራት ሸቀጦች ላይ 10 በመቶ ታሪፍ መጣላቸው ይታወሳል።

ትራምፕ ፍትሐዊ ያልሆነ የንግድ ፖሊሲን ተከትለዋል ያሏቸውን “የለየላቸው አጥፊዎች” ብለው በጠሯቸው ሀገራት ላይ ደግሞ ከፍ ያለ ታሪፍን ጭነዋል። ታሪፉ የተሰላው አሜሪካ ከሀገራት ጋር ያላትን የንግድ ጉድለት (ትሬድ ዴፊሲትን) ለማጥበብ በሚል ሲሆን፣ ትራምፕ እነዚህ ታሪፎችን በመጠቀም የሀገሪቱን የንግድ ሚዛን ጉድለት በማስተካከል የሀገሪቱን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲያብብ እና ሥራዎችን ለመፍጠር ነው ተብሏል::

አሜሪካ በጣለችው ከፍተኛ ታሪፍ ከተጎዱ ሀገራት መካከል ሕንድ አንዷ ናት:: ሕንድ በከፍተኛ ደረጃ እያደገች ምትገኝ ሀገር ናት፤ እያደጉ ከሚገኙ ዘርፎቿ መካከል ደግሞ ቴክስታይል ኢንደስትሪው አንዱ እና ዋነኛው ነው:: ዘርፉ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ የሥራ ዕድል 21 በመቶ፣ አራት በመቶ የዓለምን የአልባሳት ንግድ እንዲሁም ከዓለም 24 ከመቶውን የጥጥ ምርት የያዘ ነው:: ነገር ግን አሜሪካ የጣለችው ታሪፍ የቴክስታይል ኢንደስትሪውን እጅግ እንደጎዳው ኢኮኖሚክ ታይምስ ዘግቧል::

ይህን ተከትሎ ይመስላል ሕንድ ከዚህ ቀደም ትከተለው ከነበረው የምዕራባዊያን ደጋፊነት በሚጻረር መልኩ የሩሲያን እና ቤላሩስን ወታደራዊ ልምምድ ተቀላቅላለች:: ዛፓድ 2025 ሚል ስያሜ በተሰጠው ወታደራዊ ልምምድ ኢራንን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት መታደማቸውንም ታስ የተሰኘው የሩሲያ መገናኛ ብዙኀን ዘግቧል::

የሕንድ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው 65 የታጠቁ ወታደሮችን በስልጠናው እንዲሳተፉ ልኳል:: በወታደራዊ ልምምዱ ላይ የተለያዩ  የኒኩሌር የጦር መሣሪያዎች እና በአለፈው ዓመት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የሞከረችው “ኦርሺኒክ” የተሰኘው ከድምጽ ፍጥነት በላይ የሚምዘገዘገው ሚሳኤል ተሞክረዋል ሲል ደግሞ የቤላሩስ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል::

ሕንድ ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ ልምምድ ስታደርግ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፤ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2021 ማለትም የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት በይፋ ሳይጀመር ሕንድ ወታደሮቿን ልካ የጋራ ልምምድ አድርገዋል:: የልምምዱ አላማም ጸረ ሽብር እና የጋራ ተልዕኮዎችን ማስፈጸም ላይ ያነጣጠረ ነው:: ነገር ግን የአሁኑ የቶር ልምምድ የሕንድ እና የአሜሪካ ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱን ተከትሎ መሆኑ ለየት ያደርገዋል:: አሜሪካ፣ ሕንድ ከሩሲያ የምትገዛውን ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ዘይት እንድታቆም እና በዩክሬን ላይ የምታደርገውን ዘመቻ በግልጽ እንድትቃወም በተደጋጋሚ ስታሳስብ ነበር::

የምዕራባዊያን ተንታኞች የሕንድን ድርጊት አሜሪካን እና አውሮፓን ለማስፈራራት ነው ሲሉ ገልጸውታል:: የህንድ ቤላሩስን እና ሩሲያን መቀላቀል በሰሜን ቃልኪዳን አባል ሀገራት (ኔቶ) ላይ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል ሲል ፋይናንሻል ኤክስፕረስ ዘግቧል:: ይህም የዓለምን ውጥረት የበለጠ ሊያባብሰው ይችላል ተብሎ ተፈርቷል::

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here