የዓሣ ወንዝ ሸለቆ በአፍሪካ አህጉር በናሚቢያ ደቡባዊ ግዛት ይገኛል፡፡ ሸለቆው በትልቅነቱ በአፍሪካ ቀዳሚ ሲሆን በዓለም በአሜሪካ ከሚገኘው ታላቁ ሸለቆ “ግራንድ ካንዬን” ቀጠሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
የዓሣ ወንዝ ሸለቆ ርዝመቱ 160 ኪሎ ሜትር፣ ስፋቱ ከፍተኛው እስከ 27 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ጥልቀቱ 550 ሜትር ተለክቷል፡፡
የዓሣ ወንዝ ናሚቢያ ግዛት ውስጥ የሚቀር /ድንበር ተሻግሮ የማይወጣ/ ረዢም ርቀት ተጓዥ ወንዝ ነው፡፡ ከፍታ ያላቸው ሜዳማ ቀጣናዎችን ሸርሽሮ ደረቅ፣ የዓለት ግድግዳዎች ያፈጠጡበት መልካዓምድርም ፈጥሯል፡፡
ሸለቆው በበጋ ድርቅ ተቋቋሚ ቁጥቋጦዎች የሚታዩበት ሲሆን በክረምት በሸለቆው ወለል ላይ ቀጫጭን ወይም ጠባብ ኩሬዎች ተቀጣጥለው ይታዩበታል፡፡
ለማንኛውም ኗሪ ጐብኚ ክፍት ሆኖ የሚፈቀደው በሆባስ አቅራቢያ 70 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ማረፊያ ቦታ (ካምኘ) ነው፡፡ ሌላው 90 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍነው ቀጣና በግል ባለቤትነት የተያዘ መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡
የዓሣ ወንዝ ሸለቆ በሁለት ቀጣና የተከፈለ ነው፡፡ የላይኛው ቀጣና በወንዝ ተሸርሽሮ ያፈጠጠ አለት የተነጠፈበት ሲሆን የታችኛው ቀጣና የዓፈር መሸርሸር የተገታበት ንጣፍ አለትን የያዘ ነው፡፡
ሸለቆው ጥንት ከ650 ሚሊዬን ዓመታት በፊት በምድር ላይ በተከሰተ ውስጣዊ እንቅስቃሴ የተፈጠረ መሆኑን ባለሙያዎች አረጋግጠዋል፡፡ ማንኛውም በእግር ተጓዥ ጐብኚ ሆባስ በተሰኘው መግቢያ ቦታ ቀርቦ ቀድሞ ማስታወቅ እና ፈቃድ ማግኘትም ግድ ይለዋል፡፡ የዓሣ ወንዝ በክረምት ያለማቋረጥ በሸለቆው ግርጌ የሚፈስ ሲሆን በበጋ ፍሰቱ ተስተጓጉሎ ዝቅተኛ ጉድጓድ የሰሩ መውረጃዎቹ ውኃ አቁረው ኩሬዎች እንደሚታዩበት ነው የተገለፀው፡፡
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ኢንፎናሚቢያ፣ ሳሪስ አፍሪካ እና ናቢያ አኮሞዴሽን ድረገፆችን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም