የዓድዋ ዜመኞች

0
217
ታሪክ እንደሚነግረን አፍሪካ የሚባለውን አሕጉር እንዴት እንቀራመተው በሚል እቅድ ተነድፎ ነበር:: ይህ ደግሞ በርሊን ጀርመን ላይ ሒሳብ ተሰልቶ እንዴት እንከፋፈለው ተብሎ የኛዋን ኢትዮጵያን ደግሞ ጣሊያን ለኔ ናት ብላ ጨርሳ ነበር:: አንቀጽ 17 ምናምን የሚሉት የማታለያ ምክንያት ሆነ እንጂ ጣሊያን ኢትዮጵያን በሐሳቧ በልታ ጨጓራዋ ውስጥ ካስቀመጠች ቆይታለች::
በዚያ በየካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከጠዋት እስከ ማታ ተዋግተው በድል አሸነፉ:: ዘንድሮም የ ዓድዋ ድል በዓል ለ128ኛ ጊዜ ይከበራል:: ዓድዋን በሚመለከት በርካታ የታሪክ ድርሳናት፣ የምርምር ስራዎች፣ የኪነ ጥበብ ተግባራት፣ ሙዚቃዎች፣ ቴአትሮችና መሰል ሥራዎች ተሰናድተዋል:: ለዛሬ ዓድዋን በሙዚቃዎቻችን መልክ እንመለከተዋለን::
መልካም ንባብ!
በሙዚቃው ረገድ ቀደምት የሀገረሰብ ሙዚቃዎቻችን ሽለላ፣ ፉከራ፣ ቀረርቶና ጃሎታዎች ከ ዓድዋ ድል የጀግንነትና የአትንኩኝ ባይነት መንፈስ መውሰዳቸው ርግጥ ነው:: መነሻቸው ‘የአባቶቼ ልጅ ነኝ፤ ማን ደፍሮኝ’ የሚል ጀብዱ ነው:: በሀገር ፣ በርስትና በሴት የመጣን አትታገሰው፤ እንደረመጥ እሳት ለብልበው ይላሉ:: በእነዚህ ከመጣብህ አንገትህን ለስለት እስከ መስጠት ተፋለም፤ ቅደም እንዳትቀደም የሚል መንፈስ አለው::
ዓድዋ በሚል በባህላዊ ዘፈኖቻችን ውስጥ ዘፈኖች ባይቀርቡም የዓድዋን የድል መንፈስ ግን ማስተዋል ይቻላል:: የ ዓድዋ ድል በተቃረበ ቁጥር እንደገና አንደ ዓድዋ ድል አዲስ ሆኖ የሚደመጠው የእጅጋየሁ ሽባባው /ጂጂ/ ዓድዋ ሙዚቃ ነው:: እጅጋየሁ በ ዓድዋ ዘፈኗ ቀደምቱ እናት አባቶቻችን ለ ዓድዋ የከፈሉትን መስዋእትነት፤ መስዋእትነቱ ሀገርን ለማስቀጠል ስላመጣው ነፃነትና ክብር፤ የ ዓድዋ ን ሁልጊዜ አዲስነት፤ የተሰውትን ጀግኖች በማመስገን ታዜማለች::
ማንኛውም ሀገር በፀሎት ብቻ አልተገነባም:: ጀግኖች ሀገር አሁን አለኝ የምትለውን ግዛት ለማስከበር በየጥሻውና ጋራው ወድቀዋል:: የዛሬን ትውልድ የሞቀ ሀገርና ቤት የሰሩለት ለህይወታቸው ሳይሳሱ መስዋእትነት የከፈሉ ጀግኖች ናቸው:: “ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን ሰውን ሲያከብር” በሚል ዋናውን ሐሳብ ‘ ዓድዋ ሰው ነው ‘ ብላ ነው የተነሳችው እጅጋየሁ::
“የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት”
የሚለው የጂጂ ሐሳብ ዓድዋ ትናንት የተከፈለ የዛሬ ዋጋ፤ ለትውልድ የተቀመጠ የታሪክና መስዋእትነት አደራ መሆኑን ያስረዳል:: ሀገሬን ጠይቋት፤ እንዲህ በኩራትና በክብር ከፊታችሁ የቆምሁት በማንም አይደለም በአባቶች አጥንትና ደም ግብር እንጂ ነው የምትለን:: ትናንት ሊበትን፤ ሊገዛና ሊያጎሳቁል የመጣን ወራሪ ጠላት ለመፋለም ሲባል ያለፉትን ጀግኖች የሞት ሲቃ አልፌ፤ እነሱ የመከራ መሻገሪያ ድልድይ ሆነውልኝ ዛሬ ኑሮዬን ተመልከቱት ኩራት፣ ክብር፣ ደስታ፣ፍቅርና ድል ሞልተቶኛል ትላለች::
በኩራት በክብር በደስታ በፍቅር
በድል እኖራለሁ ይኼው በቀን በቀን
ደግሞ መከራውን ያን ሁሉ ሰቀቀን
ዓድዋ ሁነቱ፣ ክስተቱ ትናንት ይሁን እንጂ ለዛሬ ነጻነት ያቀዳጁን ጀግኖች ሁልጊዜ በትውልድ ልቦና የሚታወሱና የሚመሰገኑ ስለመሆናቸው ዘፋኟ ታዜማለች:: ከእጅጋየሁ በመቀጠል ዓድዋ ን በምስልና በድምጽ ይዞልን የመጣው ቴዎድሮስ ካሣሁን ነው:: ይህ ዘፈን ዓድዋ ን በፊልም አከል ሥራ ለማሳየት የተሞከረበት፤ በተለይም የጦርነቱን አመራርና አሰላለፍ፤ ንጉሡን ዳግማዊ ምኒልክን፤ ንግሥቲቱን እቴጌ ጣይቱን፤ ደጅ አዝማች ባልቻ አባ ሳፎን፤ ፊትአውራሪ ሀብተጊዮርጊስን፤ አሉላ አባ ነጋን እና ራስ መንገሻ ከነበራቸው ሚና እና የአመራር ጥበብ ጋር ያሳያል:: ቴዎድሮስ “ጥቁር ሰው” በሚል ያቀረበው ሙዚቃው አጼ ምኒልክን መነሻ አድርጎ ጦሩ የተመራበትን የትብብርና የአንድነት መንፈስ ለማሳየት የሞከረ ነው::
ኑ ዓድዋ ላይ እንክተት ያ ጥቁር ንጉሥ አለና
የወኔው እሣት ነደደ ለአፍሪካ ልጆች ድል ቀና
ጥቁር ሰው ዘፈን ነጭ አውሮፓዊ ወራሪ በትዕቢት ባህር ተሻግሮ፣ ድንበር አቋርጦ ርስት ሊያጠፋ ነውና ሕዝቤ ሆይ ተነስ፣ ክተት ብለው አጼ ምኒልክ አዋጅ ማስተላለፋቸውን ተጠራን’ኮ በሚል ይጀምራል:: የጥቁር ንጉሥም የእኛ የተበዳዮች፤ ፍትህን በእጃችን የያዝን ህዝቦች ንጉሥ ጠርቶናልና ዓድዋ ላይ እንገኝ የሚለውን የሚገልጽበት ነው::
ወደ ዓድዋ ሲሄድ ምኒልክ ኑ ካለ
አይቀርም በማርያም ስለ ማለ
ይህ የአጼ ምኒልክ የጥሪ አዋጅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባለው አቅም እንዲተባበር የጠየቁበትን ያስታውሳል:: ይህ ሳይሆን ቀርቶ ወስልተህ የቀረህ ካለህ ግን “ማርያምን አማላጅ የለኝም” ብለው ነበር:: የምኒልክን ጥሪ ሰምቼ አቤት ባልል ኖሮ ዛሬ ማንነቴ ኩሩ ኢትዮጵያዊ አይሆንም ነበር ይላል:: ”ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ ግብሩ እንቁላል ነበር ይኽን ጊዜ አበሻ” ተብሎ እንደሚነገረው የምኒልክ የጦር አመራር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ያስከበረና ያስቀጠለ ነው::
እቴጌ ጣይቱ የራሷን ጦር ይዛ በአውደ ውጊያ ተሳትፋለች::
የንብ ቀፎ ሲቆጣ ስሜቱ
ከፊት ሆና መራችው ንግሥቲቱ
እቴጌ ጣይቱ ጦርነት አልወድም ሴት ነኝ ቢሉም እንኳን ጠላት ገፍቶ ሲመጣ ግን ለሀገር ክብር የተዋጉና የድል ቀን እንዲመጣ የታገሉ መሆናቸውን ቴዲ በዘፈኑ ያነሳል::
ሮፍናን “ኑሪ ሠከላ” በሚል ያቀረበው ዘፈን ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ለነጻነት የከፈሉትን ዋጋ የሚያመሰግንበት ነው:: ከምንም በላይ ደግሞ አባቶች ለዛሬ የነጻነት ቀን የከፈሉልኝን አደንቃለሁ፡፡ አባቶቼ በመሐል የጀግኖች አያቶቼን መስዋእትነት ዋጋ አሳጥተውታል ይላል:: ምንም እንደ አያቶቼ ባልሆን የተሰበረውን በይቅርታ እጠግናለሁ ይላል፤
እሯ በል አንተ፣ እሯ በልዬ
የዚያ ጀግና ሰው፣ የዚያ ሰውዬ፤
ይድረስ ለዚያ ሰው
ወራሪውን ለመለሰው
እያለ የጀግኖችን አደራ ያስታውሳል:: ምኒልክን ጨምሮ ሌሎች ጀግኖችን በማንሳት ለኢትዮጵያ አንድነት የተከፈለውን መስዋዕትነት በዚህ ትውልድም በፍቅርና በይቅርታ ስለማስቀጠል ይተርካል::
ጦቢያ ለይቅርታ ቅደም
ቀድመህ እንዳትተወው ድገም፤
ደግሞ ቢያስቀይምህ ሠልስ
የአባትህን አደራ መልስ፤
ያኔ በላይ ይዘልቃል
ያን ጊዜ ቴዎድሮስ ይደግማል፤
ያን ጊዜም አሉላ ራስ ነው
ምኒልክ ዛሬም ንጉሥ ነው
የሮፍናን ዘፈን ዋናው ማጠንጠኛው ይህ ትውልድ አያቶቹ የሰጡትን የደም መስዋእትነት ረስቶ ቀደምት መሪዎቹን በየ ግሉ ለመከፋፈል ያደረገውን ከንቱ ሙከራ ይኮንናል:: አባቶቹ ጥልና ጥላቻ ውስጥ ገብተው ከአባቶቻቸው አንሰው መታየታቸው ቅሬታ ፈጥሮበታል::
የይቅርታ መንገድ ነው ምኒልክና ዮሐንስን ንጉሥ፣ አብዲሳንና አሉላን ቆራጥ የሚያደርጋቸው ይላል::
እንግዲህ እኔ ልሻል
መርዙን በይቅርታ ልሻር
ከአባቶቼም ባይሆንልኝ
ከአያቶቼ አንድነት ልማር
ቀጥለን የምንመለከተው የ ዓድዋ መዘክር የዳኜ ዋለ ”የደም ፀሐይ” ሙዚቃ ነው:: የ ዓድዋ ድል የመላው አፍሪካዊያን ድል ነው ሲባል እውነትም ማሳያዎች አሉት:: ነጭን እንደ አምላክ ይቀበሉት ለነበሩት ጥቁር አፍሪካዊያን ቅኝ ገዢን፤ በዘመኑ የሠለጠነን ጦር ማሸነፍ ትልቅ የአልገዛም ባይነት ስንቅ ሆኗል:: አፍሪካዊያን ከቅኝ ግዛት እንዲወጡ የአፍሪካ ህብረት እንዲመሰረት ኢትዮጵያ ትልቁን ሚና ተጫውታለች::
የ ዓድዋ ሰማይ ሲፈካ
ማለዳ ሆነ ለአፍሪካ
ብሎ ዳኜ የሚገልጸውም ለዚህ ነው::
የግዞት ድርሳን ነጋሪ
ቀዳሽ ነኝ ብሎ ፎካሪ፤
ውዳሴ ከንቱ ሲደግም
አሜን እንዳንል ቃሉ ግም፤
ምኒልክ ደጀ ሠላሙ
የጦር ማህሌት ቢቆሙ
ጣልያን ከሸፈ ድጋሙ
አጼ ምኒልክ የጣሊያንን ከንቱ የማታለያ አንቀጽ 17 አልቀበልም ማለታቸውን፤ ኢትዮጵያም ፍትሕን በእምነቷም በጉልበቷም ነጻ መውጣቷን ግጥሙ ያሳያል:: ክተት ብሎ ሠራዊት ከጠላት አንገት ጋር ትንቅንቅ ሲገጥም አንገቱ ሲቀላ፤ ገላው ሲበጣጠስ፤ እርሳስ በሰውነቱ ሲገባበት ቅጽበቱ ጨለማን፣ ዘመኑ መከራን፣ ከባድ ጊዜን ይመስላል:: ጨለማውን አልፎ ደመናውን ገፎ ጀግኖች ወድቀው የደም እና የህይወት ዋጋ ሰጥተው የድል ፀሀይ መውጣቱን ሙዚቃው ያወሳል::
መድፈኛው ግፋ ሲል መሬት እያራደ
የምኒልክ ፈረስ ክንፍ አብቅሎ ሄደ
ባየር በሰማይ ሲንደቀደቅ
ወድቆ ከምድር ሲደባለቅ
መብረቅ የጣለ ሰማይ ይመስል
ስንት አለ ጀግና ከባንዲራው ስር
ድብልቅልቅ ባለ ጦርነት ውስጥ የጠላትን አንገት ቆርጦ በድል ለመመለስ የተደረገን በሳንጃ መማዘዝን ያሳያል:: ከድል በኋላ ኢትዮጵያ ባንዲራዋን አደባባይ ላይ በአሸናፊነት ሰቅላለች::
ነፍስ የገበሩ
ሀገር አኖሩ፤
ለሀገር አለፉ
ከሞት ተረፉ እየረገፉ
የሚለው ግጥም ጀግኖች ሞታቸው የሀገር ሕልውና ነው:: የጅል ሞት አይደለም የሚለውን የሚያጸና ነው::
ብስራት ሱራፌልም ዓድዋ ን በሚመለከት ዘፍኗል:: አብዲስ አጋ እና ዘርዓይ ድረስን በማንሳት ጣሊያን የደረሰባትን ሽንፈት ተከትሎ ደግሞ ለመውረር ያደረገችው ሙከራ እንዳልተሳካ ያነሳል:: ኢትዮጵያ ጣሊያን ድጋሜ ከ40 አመታት በኋላ የቃጣችባትን ወራሪ የመከተችበት ሚስጥር ዓድዋ ነው ይላል:: በድጋሚ ከ1928-1933 ቆይታ ጣሊያን በኢትዮጵያ ልጆች ትብብር ተሸንፋ ወጥታለች::
የዚህ ሁሉ ሚስጥር የዳግም ድል ብርታት
የዚህ ሁሉ ሚስጥር የዳግም ድል ብስራት
መነሻ ዓድዋ
መድረሻ ዓድዋ
ይላል ብስራት በዘፈኑ::
ከሰሞኑ ለአድማጭ ተመልካች የደረሰው የአስቻለው ፈጠነ አልበም ዓድዋ ን በዘፈን አካቷል:: በአማርኛ፣ ኦሮሞኛ፣ በትግርኛ የቀረበው ዘፈን የአጼ ምኒልክን የክተት አዋጅ በማውሳት ይጀምራል:: ይህን ተከትሎ ህዝብ አዝማቹን ተከትሎ ወደ ዓድዋ ውጊያ ሲጓዝ ያሳያል:: ውጊያው ተደርጎም ጠላት ተረታ:: ወራሪ ይሉንታ ቢስ ነው፣ እምነት፣ ቋንቋ፣ አገር፣ ሰፈር፣ መንደር በክብር እንዲቆይ አያደርግም:: አጼ ምኒልክ የነገሩት የ”ተነሱ እንነሳ” አዋጅ በሚወዷት ማርያም ጠርተውኝ አልቀርም፣ እንዴት በኔ እምነት ሲያሳድሩ እኔስ እምቢ እላለሁ ይላል አስቻለው:: እከታለሁ፣ እንዲያውም ብቻውን አይደለም፣ የአካባቢየን ሰው ቀስቅሼ፣ ታጥቄ ነው ይላል:: በዚህ ስንኝ ውስጥ አስቻለው እሽ ንጉሥ ሆይ አዋጁን ሰምቻለሁ ሌሎችንም ይዤ ነው በወኔ ተሞልቼ የምሰለፈው ሲል እናያለን::
እምዬ ምኒልክ ተናገሩ
በእምዬ ማርያም እየማሉ
“ተማምነው በእምነት ጠርተውኝ
እኔስ በእምዬ ኮራሁኝ
እመጣልሃለሁ ካ’ገሬው መክሬ
ነጋሪት ጎስሜ ግዝት አስነግሬ
እደርስልሃለሁ በሥምህ ፈክሬ
ንጉሥ ሆይ በዚህ ትገረማለህ ወይ፣ያንተን ቃል ሰምቶ የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር ከየጎራው የተጠራራውን መቼ አየኸውና እያለ ይገረማል::
ኧረ ምኑን አየሕ፣ምኑን አየህና
ራስ ፊት አውራሪው ያው መጣልህ ገና
ግራ ቀኝ አዝማቹ ከተተልህ ገና
በመሣሪያና በአጠቃላይ የጦርነት ግብዓት (ሎጂስቲክስ) ዓድዋ ጦርነት ላይ የዋለው የኢትዮጵያና ጣሊያን አቅም ለውድድር የሚቀርብ አይደለም:: ጣሊያን በሰፊው ታጥቃ፣ ዘመናዊ መሣሪያ ይዛ ነው የመጣችው:: አትዮጵያዊ ደግሞ ጎራዴና ሰይፍ ነበራቸው:: ይዘውት የመጡትን መሣሪያ ነደውበት ተመለሱ:: ጠላት ያሉትን ኢትዮጵያዊ በምርኮ አስታጠቁበት::
እምነትን ሊያጠፋ የከተመው ጠላት
ባመጣው መሣሪያ ገናን ክንድ አርፎበት
የወደቀው ወድቆ ታሪክ ተጽፎበት
የነጻነት ቀርቶ የድል ቀን በራበት
ኢትዮጵያዊያን በየገደሉ ዘምተው ጠላትን አሸነፉ፣ በድል አደባባይ ቆሙ:: ምርኮኞችን እንኳን በክብር አስቀመጧቸው፣ ሰው የመሆንን ክብር፣ ድህነትን ጀግንነት ምን መልክ እንዳለው አሳዩአቸው:: ምርኮውን ጣሊያንን በመጣበት እግሩ መልሰው ሰደዱት:: ይህንን ተከትሎ ዓለም ለጥቁር ያለውን ዕይታ ለወጠ:: ዓድዋ አይደፈሬነትን አስተማረ፣ የነጻነት ጮራ ሆነ::
‘‘ሰውና ሰው ወርዶ ግጥም በዋለበት
ጥቁር አሸንፎ ክንዱን አሳየበት
በነጩ ሰማይ ላይ ዓለም ተማረበት
አስቻለው ፈጠነ ዓድዋ ላይ ሽንፈትን ተከናንበው የተመለሱት ጣሊያኖች እንደ አንበሳ በግርማ ተሞልተው መጥተው እንደ ጅብ ኮስሰው ሲመለሱ፣ ጣሊያናዊያን ደግ አረገ ምኒልክ፣ ደግ አደረገች ጣይቱ እያሉ እንደቀለዱባቸው ያነሳል:: ዓድዋ ታሪኩ ብዙ ነው፣ ድምጻዊያን በተረዱት መጠን አቅም በፈቀደላቸው መጠን ዘፍነው ለአዲሱ ትውልድ ለማሳወቅ ጥረት አድርገዋል:: ዓድዋ ታሪኩ መልኩ ሐይቅ ነው፣ ገና ብዙ ታሪኮች በሙዚቃ ይተረካሉ:: ሐተታ ዓድዋ ችን በዚህ አበቃ::
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here