“ምናልባትም በጋዛ የመጨረሻ ሰዓታትን እና ቀናትን እያሳለፍን ሊሆን ይችላል፤ እርግጥም ነው፡፡ የትውልድ ቀዬዬን ለቅቄ ስለመሰደዴ፣ ሁላችንም ስለመሰደዳችን እርግጥ እየሆነ ነው። አዎ እርግጥ ሆኗል። እናም ላንመለስብሽ እንችላለንና ጋዛ ደህና ሁኚ።” ይህን ስሜቷን በደብዳቤ ያጋራችው ሳሚራ ጃሚል ትባላለች፣ ፍልስጤማዊ ተማሪ ናት። የእስራኤል – ሃማስ ጦርነት ሕይወታቸውን ካመሰቃቀለባቸው ፍልስጤማዊያን መካከል አንዷ ናት። መኖሪያ ቀዬዋን እንድትለቅ መነገሩን ተከትሎ ነበር ክፉኛ የተጎዳውን ስሜቷን በደብዳቤ የገለጸችው።
አካባቢው ከጦርነት ተላቆ አያውቅም፤ በዚያው ልክ ደግሞ ሰላምን ለማስፈን የትየለሌ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሰላም እንደራቀው ይገኛል – መካከለኛው ምሥራቅ፡፡
አካባቢው የዓለም ኃያላን ፍላጎት የተጫነው መሆኑ ደግሞ ለሰላም እጦቱ አባባሽ እንደሆነ ይነገራል።
እስራኤል በሃማስ ላይ እየወሰደች የሚገኘው ወታደራዊ እርምጃ ሦስት ዓመታትን ሊደፍን የቀናት ዕድሜ ብቻ ቀርተዋል፤ ከ60 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያንን ሕይወት የቀጠፈው፣ ከአንድ መቶ ሺህ በላዩን ያቆሰለው እና ከሁለት ሚሊዮን የሚልቁትን ደግሞ ያፈናቀለው ጦርነት መንስኤ መቀመጫውን ጋዛ ውስጥ ያደረገው የሃማስ ታጣቂ ቡድን እስራኤል ውስጥ ዘልቆ በመግባት ለበዓል በተሰባሰቡ እስራኤላዊያን ላይ ጥቃት መፈጸሙ እና ማገቱ ነበር፤ ይህን ተከትሎ ታዲያ እስራኤል ሳትውል ሰታድር ነበር የአጸፋ ምላሽ መስጠት የጀመረችው።
በእስራኤል የአጸፋ ምላሽ በርካታ የሃማስ መሪዎች ተገድለዋል፤ አለፍ ሲልም ለሃማስ ድጋፍ ያደርጋሉ በተባሉ ጎረቤት ሀገራት ላይ ጭምር ጥቃት በመሰንዘር ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ደርሷል፤ ለአብነትም ኢራን በርካታ የጦር መሪዎቿን አጥታለች፣ ሶሪያም በተመሳሳይ ከፍተኛ ውድመትን አስተናግዳለች።
የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም እንዲሉ የሃማስ ታጣቂ ቡድን በእስራኤል ግዛት ውስጥ ዘልቆ ጥቃት ከመሰንዘሩ በዘለለ በፍልስጤማውያን ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ መታደግ አልቻለም። ይባስ ብሎ ሰቆቃቸው እየከፋ ነው የሄደው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጋዛ ያንዣበበው የረሃብ አደጋ የከፋ ጉዳት ማስከተሉን በመጥቀስ ከዚህም በላይ በእጅጉ ሊከፋ እንደሚችል አስጠንቅቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጦርነቱ ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፤ የፍልስጤማዊያን ሰቆቃም እንዲሁ፤ ጦርነቱ ተባብሶ በቀጠለበት ታዲያ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበው የሰላም ዕቅድ የፍልስጤማዊያንን ሰቆቃ ያስቆማል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
ዳሩ ከዚህ በፊት የተደረጉት የሰላም ዕቅዶች ጉንጭ ከማልፋት የተሻገረ ውጤት እንዳላስገኙ ያስታወሰው ቢቢሲ ነው። አዲሱ ዕቅድ ደግሞ በበርካታ ሀገራት ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘ ሆኗል፤ ይህን መነሻ በማድረግም በፕሬዚዳንት ትራምፕ የቀረበው የሰላም ዕቅድ የሚኖረውን ተስፋ ቢቢሲ አስነብቧል።
ዘገባው እንዳመላከተው አዲሱ የሰላም ዕቅድ በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተቀባይነትን አግኝቷል።
በአጠቃላይ የጋዛ የሰላም ዕቅድ ዋና ዓላማ የህዝቡን ህይወት ከእንቅፋት እና ከጦርነት መውጣት ማስቻል እና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የሰላም መንገድ መፍጠር ነው።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በቅርቡ በነጩ ቤተ መንግሥት ተገናኝተው ጋዛን በተመለከተ መክረዋል፤ የሲ ኤን ኤን ዘገባ እንዳመላከተው የሁለቱ መሪዎች ውይይት በጋዛ ያለውን ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ያለመ ነበር፡፡ ሃያ ነጥቦችን ያካተተ ሰላምን ያወርዳሉ የተባሉ የመፍትሔ ሐሳቦችንም ይፋ አድርገዋል።
ዕቅዱን በተመለከተ በሃማስ በኩል ምንም አይነት ምላሽ አልተሰጠም፤ ይሁን እንጂ የዓረብ ሀገራትን (ሳኡዲ አረቢያ፣ ጆርዳን፣ ግብጽ) ጨምሮ በበርካታ የዓለም ሀገራት ዘንድ ድጋፍ እንደተቸረው ዘገባው ያመላክታል፡፡ ዕቅዱንም “ለሰላም መልካም አጋጣሚ፣ አዲስ ተስፋን የሰነቀ” ሲሉ ነው ይሁንታ የቸሩት።
በዕቅዱ ከተካተቱት ነጥቦች መካከል የተኩስ አቁም ማድረግ፣ የታጋቾች ልውውጥ፣ የእስራኤል ወታደሮችን ደረጃ በደረጃ ከጋዛ ማስወጣት፣ ሃማስን ትጥቅ ማስፈታት እና ሰብዓዊ እርዳታ፣ አዲስ የጋዛ አስተዳደር እንዲሁም መልሶ ግንባታ የሚሉት ይገኙበታል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሁሉም ወገን የመፍትሔ ሐሳቦችን እንዲተገብር አሳስበዋል፤ በነጩ ቤተ መንግሥት የተገኙት ኔታንያሁም ዕቅዱን እንደተቀበሉት በማንሳት አመስግነዋል።
እስራኤል እና ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በአስቸኳይ እንዲተገብሩ ያሳሰቡት ፕሬዚዳንቱ ይህም ጦርነቱን ለመቋጨት ያስችላል ነው ያሉት።
የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ ታዲያ ሃማስ ያገታቸውን እስራኤላዊያንን በ72 ሰዓታት ውስጥ መልቀቅ እንዳለበት ነው በዕቅዱ የተመላከተው፤ በአጸፋው ደግሞ እስራኤል የያዘቻቸውን እና የዕድሜ ልክ እስራት የተበየነባቸውን 250 እስረኞችን እና 1700 ከጋዛ የተወሰዱ ፍልስጤማዊያን የሚለቀቁ ይሆናል።
በተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ጸጥታ ኃይል (ሰላም አስከባሪ) በጋዛ እንዲሰማራ የተቀመጠ ሲሆን የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ የሚወጡትም ይህ ኃይል ሲሰማራ መሆኑ ነው የተመላከተው።
በሌላ በኩል አዲስ የጋዛ አስተዳደር የሚቋቋም ሲሆን በዚህ ግን ሃማስ ምንም ሚና እንደማይኖረው በፕሬዚዳንት ትራምፕ ይፋ የተደረገው አዲሱ የሰላም ዕቅድ ያብራራል፤ ይህ ታዲያ በሃማስ በኩል ተቀባይነት አይኖረውም በሚል ስጋትን ፈጥሯል።
በተመሳሳይ ሃማስ የሚጠቀምባቸው ማናቸውም የጦር መሣሪያዎች፣ የጦር መሣሪያ የሚያመርትባቸው መሠረተ ልማቶች፣ ወታደራዊ መተላለፊያዎች እና መሰል ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሶች ሁሉ የሚወገዱ ይሆናል፤ ይህም በገለልተኛ ወገን መረጋገጥ እንዳለበትም ነው የተመላከተው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሰ,ዲሱን የሰላም ዕቅድ በተመለከተ ሃማስ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል፤ “አዲሱን ዕቅድ በተመለከተ ምላሽ ለመስጠት ጊዜ ያስፈልገኛል” ሲልም ነው ያስታወቀው፡፡
ኳታር እና ግብጽ ሃማስ አዲሱን ዕቅድ እንዲቀበል በአደራዳሪነት ተሰይመዋል፤ አዲሱን ዕቅድም ለወታደራዊ ቡድኑ ማቅረባቸውንም አልጀዚራ ዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲሱ የሰላም ዕቅድ ከስጋት የተላቀቀ አልሆነም፤ ስለ ተግባራዊነቱ ቁርጥ ያለ ጊዜ አለመቀመጡ፣ የእስራኤል ጦር ከጋዛ መቼ እንደሚወታጣ አለመነገሩ፣ ሃማስም እስካሁን በዝምታ ውስጥ መገኘቱ የስጋት ምንጮች ናቸው፡፡ይህም እንደከዚህ ቀደሞቹ ሙከራዎች ሁሉ ተግባራዊነት ሊርቀው ይችላል ነው ያስባለው።
በዚህም ተባለ በዚህ የሰላም ዕቅዱ ይፋ ቢደርግም እስራኤል በሃማስ ላይ የምታደርገውን ጥቃት ቀጥላለች፤ በጋዛ ያለው ሰቆቃም እንዲሁ።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ “ሃማስ አዲሱን የሰላም ዕቅድ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ መቀበል አለበት፤ መቀበል ብቻ ሳይሆን በቶሎ መተግበር ይገባዋል፤ ይህ ካልሆነ ግን ከምድረ ገጽ ይጠፋል፡፡ እስራኤልም ጀመረችውን የቤት ሥራ ትጨርሳለች” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም