የዕድሜ ማጭበርበር- ሌላኛዉ “ዶፒንግ”

0
79

ሀገራችን ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት በተለይ በረዥም ርቀት ሁሌም ደጋግመን የምንሰማው የሚያኮራ ታሪክ እንዳላት ዓለም ይመሰክራል። ዘርፉ ደካማ መሰረተ ልማት፣  የመልካም አስተዳደር ችግር እና የገንዘብ እጥረት ቢኖርበትም በትውልድ ቅብብሎሽ ግን ከዘመን ዘመን እየተሻገረ ይገኛል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት በየጊዜው ለአዳዲስ ፊቶች እና ባለተሰጥኦዎች ዕድል እየሰጠ አይደለም በሚል በብዙዎች ዘንድ ተደጋጋሚ ትችት ይቀርብበታል።

በዕድሜ የገፉ አትሌቶች ለጀማሪዎች ቦታ ባለመልቀቅ  ቅሬታዎች የሚነሱ ሲሆን የዕድሜ ተገቢነት ጉዳይ በወጣቶች ሻምፒዮና እና ውድድር በተደጋጋሚ የሚነሱ ቅሬታዎች ናቸው። በቅርቡ በድሬዳዋ ከተማ በተደረገው 13ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች እና አራተኛው ከ18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የዕድሜ ማጭበርበር ጎልቶ የታየበት እንደነበረ ከአሚኮ በኵር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሀመድ አለባቸው ተናግረዋል።

ውድድሩ ታዳጊዎች እና ወጣቶች የሚመዘኑበት  ቢሆንም ነባር እና ከ20 ዓመት በላይ የሆኑ አትሌቶች መሳተፋቸውን ይናገራሉ። የአትሌቶችን የዕድሜ ተገቢነት በተመለከተ ክስ ያቀረቡ ተቋማት እንዳሉ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ ቅሬታ ካቀረቡት መካከልም በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ይገኝበታል ብለዋል። በተጨማሪም በርካታ አሰልጣኞች እና የቡድን መሪዎች ቅሬታ ማቅረባቸውን ያስታውሳሉ።

የውድድር ጥቅሞችን ለማግኘት ሆነ ተብሎ የአንድን አትሌት ዕድሜ መቀነስ ነው፤ የዕድሜ ማጭበርበር። ድርጊቱ ስነ ምግባር የጎደለው ተግባር ሲሆን የስፖርቱን ታማኝነት ይጎዳል፤ የሀገራችንን ስምም ያጎድፋል።

ይህ ችግር በብዙ የአፍሪካ እና የእስያ ሀገራት ላይ በስፋት እንደሚስተዋል የዓለም አትሌቲክስ መረጃ አስነብቧል። በአትሌቲክስ ስፖርት የዕድሜ ማጭበርበር ዘርፉን እየገደለ ያለ የስፖርቱ ካንሰር ነው ማለት ይቻላል።

የአትሌቶች የዕድሜ ማጭበርበር ጉዳይ የቆየ እና ባህል የሆነ ድርጊት ነው። አትሌቶች፣ አሰልጣኞች እና የቡድን መሪዎች  ጊዜያዊ ውጤት ፈላጊ በመሆናቸው ከዚህ ባህል ከሆነው መጥፎ ድርጊት ሊላቀቁ አልቻሉም።

አትሌቶች ወደ ክለቦች፣ ማሰልጠኛ ማዕከላት እና ፕሮጀክቶች ሲመጡ የትምህርት ማስረጃ እና መታወቂያ ይዘው መጥተው ይመዘገባሉ። የልደት የምስክር ወረቀት በገጠሩ የሀገራችን ክፍል የተለመደ ባለመሆኑ ትክክለኛውን የአትሌቶች  ዕድሜ  ለማወቅ  አስቸጋሪ ያደርገዋል። ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች ከታች ከፕሮጀክት፣ ከማሰልጠኛ ማዕከላት ጀምሮ ነው የሚነሱት፤ በምዝገባ ወቅት ስህተት  ስለሚሠራ።

በአትሌቲክስ ለምን የዕድሜ ማጭበርበር ይከሰታል? አትሌቶች ትክክለኛ ዕድሜአቸውን በመቀነስ የስፖርት ህይወታቸውን በማራዘም በብሄራዊ ቡድን እና በስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች የመመረጥ ዕድላቸውን ከፍ ለማድረግ አንደኛው ምክንያት መሆኑን ከአሚኮ በኵር ጋዜጣ ስፖርት ዝግጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ማረሚያ ቤቶች አትሌቲክስ ክለብ አሰልጣኝ ኮማንደር ደጀኔ ክፍሌ ተናግረዋል።

በዋናነት ግን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እንዳላቸው አሰልጣኙ ያብራራሉ። የልደት ምዝገባ ስርዓት ደካማ መሆን አትሌቶች ለማጭበርበር ከፍተኛ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። ኢትዮጵያን በመሰሉ ደሀ ሀገራት በተለይም በገጠር አካባቢ ልደት በይፋ በወሳኝ ኹነት ባለመመዝገቡ አትሌቶች ዕድሜአቸውን ለማጭበርበር ይመቻቸዋል ሲል ማህበራዊ ምክንያቱን ያብራራሉ።

ብዙ አትሌቶች ከድህነት ለመውጣት እና ስኬታማ የወደፊት ህይወት ለመምራት ዕድሜአቸውን ይቀንሳሉ። ድህነትን ለማራገፍ የአትሌቲክስ ስፖርትን እንደ ሁነኛ መንገድ እና መፍትሄ አድርጎ ማሰባቸው አትሌቶች ዕድሜአቸውን እንዲያጭበረብሩ ያደርጋቸዋል።  የተሻለ ገንዘብ አግኝተው ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ለመለወጥ እና ኢኮኖሚያዊ ችግራቸውን በፍጥነት ለመፍታት ካላቸው ጽኑ ፍላጎት ነው  በሕገ ወጥ መንገድ የሚጓዙት። የዚህ ጥቅም ተካፋይ የሆኑ አሰልጣኞች እና ወላጆችም በአትሌቶቻቸው ወይም በልጆቻቸው ዕድሜ ማጭበርበር ድርጊት ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተነግሯል።

በውድድር ወቅት የተደራጀ የመረጃ አያያዝ ባለመኖሩ በመጀመሪያው ዓመት የዕድሜ ምርመራ አድርጎ ያላለፈ አትሌት በቀጣይ ዓመት ድጋሚ ሁለተኛ ምርመራ ለማድረግ የሚመጣበት አጋጣሚ ሰፊ ነው ተብሏል።

የዕድሜ ማጭበርበር ውድድሮችን ኢ ፍትሐዊ ያደርጋቸዋል። በወጣት እና ታዳጊ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ትልልቅ አትሌቶች አካላዊ ጥቅም በማግኘት ፉክክሩን በበላይነት እንዲያጠናቅቁ ያስችላቸዋል። ይህም ወጣት ባለተሰጥኦ አትሌቶች ሩቅ ሳይጓዙ ተስፋ ቆርጠውም ከስፖርቱ እንዲሸሹ ያደርጋቸዋል። ታዲያ  ተስፋ ያላቸው ታዳጊ አትሌቶች ተስፋቸው እንዳይከስም ተገቢውን ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አሰልጣኙ ያስረዳሉ።

ካለዕድሜአቸው በመወዳደር የማይገባቸውን ውጤት ለማግኘት የሚፈልጉ አትሌቶች ኃይል የሚሰጥ አበረታች ንጥረ  ነገር (ዶፒንግ) ከሚወስዱት ጋር ተመሳሳይ ድርጊት በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ባይ ናቸው አሰልጣኙ።

በታዳጊ እና ወጣቶች ሻምፒዮና ላይ ክለቦችን ማሳተፍ አግባብ አለመሆኑን የተናገሩት አሰልጣኙ ልምድ ያለውን (በክለብ የቆየ አትሌት) ከታዳጊ እና ወጣት አትሌቶች ጋር ማወዳደር ተገቢ አለመሆኑንም ይጠቅሳሉ።

ዕድሜን ሲያጭበረብሩ የተያዙ አትሌቶች ሽልማታቸውን ይነጠቃሉ፤ ከውድድርም እንደሚታገዱ በሕጉ ተቀምጧል። ነገር ግን ይህ አስተማሪ ድርጊት ተግባራዊ ሲሆን እንደማይታይ አልጣኝ ደጀኔ ይናገራሉ። በርካታ የአፍሪካ እና የእስያ ሀገራት በታዳጊ ወጣቶች ውድድር ላይ የዕድሜ ማጭበርበር ክስ በተደጋጋሚ ሲቀርብባቸው መስማት የተለመደ ነው።

በተለይ ከአህጉራችን የኢትዮጵያውያን፣ ኬኒያውያን እና ናይጀሪያውያን አትሌቶች ባለፉት ዓመታት በእድሜ ማጭበርበር ተጠርጥረው እንደነበር የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመለክታል። እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ በኢትዮጵያ በሁሉም ስፖርት የዕድሜ ማረጋገጫ በጥብቅ ክትትል ተግባራዊ ሲደረግ እንዳልነበረ የሚታወስ ነው። አሁን ላይ ግን ችግሩን ለመፍታት ምንም እንኳ ሙሉ በሙሉ ዘመናዊ ናቸው ባይባልም ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ አሠራሮች እንዳሉ ግን አይካድም።

ዘርፉ ላይ የሚነሱ የዕድሜ ተገቢነት ጥያቄዎችን ለመፍታት የባዮሜትሪክ (ሳይንሳዊ የዕድሜ ማረጋገጫ) ዘዴዎችን የመጠቀም ሥራ ተጀምሯል።  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሁን ላይ ዕድሜን ለመመርመር እየተከተለ ካለው መንገድ መካከል ኤም አር አይ (MRI) ፣ ባዮሎጂካል ምልክቶች እና የጥርስ እድሜ ምርመራ ይገኙበታል። የዕድሜ ምርመራ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከታች ከክለቦች፣ ማሰልጠኛ ማዕከላት እና ፕሮጀክቶች ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበትም አሰልጣኙ ተናግረዋል።

የዕድሜ ማጭበርበር ሲስፋፋ ዓለም አቀፍ ትችት እና ውግዘት ያስከትላል፤ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ላይም አለመተማመን ይፈጥራል። ታዲያ ከዓለም አትሌቲክስ እና ፀረ አበረታች ተቋም ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር ትክክለኛ ዕድሜ ሪፖርት ማድረግ መቻል ችግሩን ለመፍታት አንደኛው መፍትሄ ነው። የዕድሜ ማጭበርበር በአትሌቶች እና በሀገር ላይ የሚያመጣውን አደገኛ መዘዝ ማስተማር እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራትም ችግሩን እንዲቀንስ እንደሚያደርገው አሰልጣኝ ደጀኔ ይመክራሉ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የመረጃ አያያዙን በማዘመን ወደ ዲጂታል መቀየርም ይጠበቅበታል። የተሻሉ የህክምና ቴክኖሎጂዎችንም መጠቀም ያስፈልጋል። ለምሳሌ እድሜን ለመገመት የሚያስችለውን  ኤም አር አይ ((MRI) የህክምና መሳሪያ እንዲጠቀሙ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ከጤና ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት አለበትም ተብሏል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዕድሜ ማጭበርበርን ለመከላከል ጠንካራ ሕጎችን ማርቀቅ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራር መዘርጋት ይኖርበታል። የዕድሜ ማጭበርበር ክሶች የሚያጣራ ገለልተኛ ባለሙያ ወይም ተቋምም ያስፈልጋል። የአጥንት እና የዕድሜ ምርመራ፣ የሆርሞን ትንተና፣ የጥርስ እድሜ ምርመራ፣ የባዮሎጂካል ምልክቶች እና የመሳሰሉትን ሳይንሳዊ እና አስተማማኝ የሆኑትን የዕድሜ ማረጋገጫ ዘዴዎች መጠቀም እንደሚያስፈልግ አሰልጣኙ ያብራራሉ።

ይህንንም ለማከናወን አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ከጤና ተቋማት እና ከስፖርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅበት አሰልጣኙ አጽዕኖት ሰጥተዋል። ታዳጊዎች የሚገኙበትን ትክክለኛ ቦታ መለየት እና እነርሱን ለውድድር ማቅረብ ይገባል። የአትሌቶችን የግል መረጃ በቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ መያዝና ማደራጀት ተግቢ መሆኑንም ይናገራሉ አሰልጣኝ ደጀኔ ክፍሌ። ይህ መሆን ካልቻለ ግን በየጊዜው የሚቀጠሩት አትሌቶች እድሜአቸውን በመቀነስ እንደሚመጡ ተናግረዋል።  ።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here