የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ጋር በመተባበር የተሻሻለውን የዘር አዋጅ 1288/2015 የማስተዋወቅ እና የሕገ ወጥ ዘር ቁጥጥር ላይ በባሕር ዳር ከተማ ምክክር አድርጓል።
ሕገ ወጥ የዘር ዝውውር ቁጥጥር በአማራ ክልል ያለበት ሁኔታ፣ ለመከላከል የሚደረግ ጥረት እና ተግዳሮቶችን በተመለከተ በውይይቱ ተነስቷል። በክልሉ የሚገኙ የፍትሕ አካላት፣ ግብርና ቢሮ፣ የሕገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ ኃይል፣ ንግድ ቢሮ፣ የመንግሥት እና የግል ዘር አምራች ድርጅቶች ተወካዮች፣ የአማራ ግብርና ጥራትና ደህንነት ባለስልጣን የጥራት ቁጥጥር አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለታቸው አካላት ተገኝተዋል።
በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው ናቸው። የምክክር መድረኩ አንዱ ዓላማ መደበኛ የዘር አቅርቦት የሚመራበትን ሥርዓት ማሳለጥ መሆኑን ተናግረዋል። የአማራ ክልል ምጣኔ ሀብት የተመሠረተው በግብርናው ዘርፍ በመሆኑ ግብርናውን መደገፍ እና ማዘመን ይጠበቅብናል ብለዋል። በዋናነትም የተሻሻለ ዘር በማቅረብ ምርታማነትን ለማሳደግ የምርጥ ዘር አጠቃቀም ሽፋንን ማሳደግ ክልሉ ከሚሠራባቸው የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ ስለመሆኑ ነው ምክትል ቢሮ ኃላፊው ያስታወቁት።
ለክልል ዘር በሁለት መንገድ (በመደበኛ እና በኢመደበኛ) እንደሚቀርብ ያመላከቱት አቶ አጀበ በመደበኛ የዘር አቅርቦት ሥርዓት የሚቀርበው ምርጥ ዘር ከ10 በመቶ እንደማይበልጥ አስታውቀዋል። “በዘር አቅርቦት ላይ መዘናጋት በግብርናው ምርት ላይ ዋጋ ያስከፍላል” ብለዋል። በአርሶ አደሮች ባሕላዊ ሥርዓት የሚቀርበው መደበኛ ያልሆነ የዘር አቅርቦት ያለበትን ውስንነት በማሻሻል ወደ መደበኛ ሥርዓቱ መለወጥ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
አቶ አጀበ እንዳሉት ምርትን በሚፈለገው መንገድ ለማሳደግ በጋራ መሥራትን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ ሕገ ወጥ የዘር ዝውውርን እና አቅርቦትን ለመከላከል በአዋጅ ሕጋዊ ድጋፍ ማግኘቱ ከፍተኛ አበርክቶ አለው። ዘርን ለምግብነት ማዋል፣ በሕገ ወጥ መንገድ ማዘዋወር እና ቀለም በመቀባት ዘር ያልሆነን ዘር ነው ብሎ ለአርሶ አደሩ መሸጥ እንቅፋቶች መሆናቸውን አመላክተዋል። ይህ ደግሞ በምርታማነቱ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ ዘላለም ልየው በመድረኩ አጋር አካላት በተሻሻለው የዘር አዋጅ ላይ በመወያየት ሕገ ወጥ የዘር ግብይትን ለመቆጣጠር ተባብረው የሚሠሩበት ዝግጅት እንደሚደረግ ተናግረዋል። ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በአዋጅ ከተሰጠው ተግባር እና ኃላፊነት አንዱ ከምርምር የሚወጡ ዘሮችን ጥራት እና ደኅንነት ተጠብቆ ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ ማድርግ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም በክልሉ በሚመረቱ ምርጥ ዘሮች ላይ የጥራት ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ነው ያነሱት፡፡ የፍትሕ አካላት ተባብረው በመሥራት ሕገ ወጥ የዘር ዝውውርን እና ግብይትን በመከላከል አርሶ አደሩን ከጉዳት የማዳን ኃላፊነት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም