የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብ ጥራትና ደህንነቱ የተረጋገጠ የግብርና ግብዓት መጠቀም ድርሻው የላቀ ነው። ይሁን እንጂ የክልላችን አርሶ አደር እየቀረበለት ያለው የግብርና ግብዓት በመጠን አነስተኛ ከመሆኑም ባሻገር በጥራት ቁጥጥር ሥርዓት ያለፈ አለመሆኑ ፈታኝ አድርጎት ቆይቷል። ይህም የክልሉ ምርትና ምርታማነት በሚፈለገው ልክ እና ፍጥነት እንዳያድግ እንቅፋት ሆኗል።
የክልሉ መንግሥትም ይህንን በመረዳት በግብርና ግብዓት ላይ የጥራት ቁጥጥር ሥርዓትን በባለቤትነት የሚያስተባብር ተቋም በአዋጅ ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በማግኘቱ የግብርና ጥራትና ደህንነት ባለሥልጣንን በአዋጅ ቁጥር 208/2006 እንዲቋቋም አድርጓል። ይህም በግብርና ግብዓት ላይ ይስተዋል የነበረውን የጥራት መጓደል እንዲሻሻል አድርጓል። ለአብነትም ምርጥ ዘርን እንኳን ብናነሳ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እናት ዘር፣ ቅድመ መሥራች፣ መስራች እና የተመሰከረላቸው ዘሮች ጥራት እና ደረጃቸው ተጠብቆ መመረታቸውን ይከታተላል፤ ያረጋግጣል እንዲሁም ከጥራት ደረጃ በታች ሆነው ሲገኙ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ያደርጋል። እንዲሁም በሕገ ወጥ የግብርና ግብዓት አምራች እና አቅራቢዎች ላይ ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ ወደ ሕጋዊነት እንዲመለሱ ያደርጋል።
ጥራት የሌለው ዘር የሚያመርቱ እና የሚያከፋፍሉ ሲገኙ እስከ ፈቃድ መንጠቅ ይደርሳል። በተጨማሪም የጥራት ደረጃ መስፈርትን የጠበቁ መሸጫ እና ማከማቻ መጋዝኖች እንዲገነቡ ይከታተላል። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በምርጥ ዘር፣ በፀረ ኬሚካል፣ በአፈር ማዳበሪያ እና በሌሎች የግብዓት ስርጭቶች ላይ የብቃት ማረጋገጫ ይሰጣል፣ ያድሳል፣ አሠራር ሲጣስ ደግሞ ይሰርዛል። አስተማማኝ ዘር እንዲመረት ቁጥጥር ያደርጋል። ከአርሶ አደር ማሳ እስከ መጋዝን ያሉ ዘሮችን ይመረምራል፤ ያረጋግጣል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ርምጃ ይወስዳል፤ ያሽጋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአማራ ክልል የግብርና ጥራትና ደህንነት ባለሥልጣን በምርጥ ዘር ብዜት እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች እና መፍትሔዎች ዙሪያ በምርጥ ዘር ብዜት ከተሠማሩ ድርጅቶች፣ ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር ከሰሞኑ በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አድርጓል። በውይይቱም ጥራት ያለው ዘር በማባዛት ለአርሶ አደሮች ማሰራጨት እንደሚገባ ተነስቷል:: ከአቅርቦት፣ እጥረት እና ከጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የዘር ብዜት ማዕከላትን አቅም ማሳደግ እና መደገፍ እንደሚገባ ተመላክቷል።
በውይይት መድረኩ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) የምርጥ ዘር አቅርቦት ለግብርና ሽግግር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። ግብርና በዕውቀት መመራት አለበት ያሉት ቢሮ ኃላፊው ምርጥ ዘር የሚባዛው በኃላፊነት እና ፍላጎትን መሠረት አድርጎ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።
በዘር አምራቾች የሚታዩ አጠቃላይ ሂደቶችን በመገምገም እንደ ክልል ጥራት ያለው ዘር ለማቅረብ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስገንዝበዋል። በክልሉ የቅባት ሰብሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የጥራጥሬ ዘሮችን በማባዛት በኩል ውስንነቶች መኖራቸውን አመላክተዋል። የዘር ጥራት ጉድለት በአርሶ አደሩ ዘንድ ቅሬታ እየፈጠረ በመሆኑ ችግሩን ከመሰረቱ ማረም እንደሚገባ አሳስበዋል። ዘር አምራቾች እርስ በርስ በመደጋገፍ ለክልሉ ግብርና ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል የግብርና ጥራትና ደህንነት ባለሥልጣን በአመራረት እና በማከማቻ ወቅት ያለውን የዘር አያያዝ እና ጥራት የመስክ ምልከታ (የዳሰሳ ጥናት) አድርጓል። በጥናቱም ዘር አቅራቢ ድርጅቶች በዝቅተኛ፣ በመካከለኛ እና በከፍተኛ ደረጃ መለየታቸውን የክልሉ የዘር ጥራት ቁጥጥር ባለሙያው አቶ ሰለሞን ሽገድብ ተናግረዋል። የዘር ጥራት ችግር በአመራረት እና በአያያዝ ወቅት እንደሚከሰት ጠቁመዋል። በመሆኑም ትክክለኛ ችግሩን ለመለየት የሚያስችል ጥናት መደረጉን ገልጸዋል።
በጥናቱ መሠረት ከደረጃ በታች በሆኑ አምራች ድርጅቶች ላይ ድክመቶችን በማረም በአንፃሩ በጥንካሬ የተለዩ አምራቾችን በማበረታታት ልምዱን የማስፋት ሥራ እንደሚከናወን አመላክተዋል። የውይይት መድረኩ ልምድ ያላቸው አምራቾች ልምድ ለሌሎች ለማካፈል እና ተሞክሮ ለመለዋወጥ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል አብዛኛው ዘር የሚመረተው በአርሶ አደሮች ማሳ በኮንትራት ውል መሆኑን አንስተዋል። ይህም ለጥራት ጉድለት ምክንያት ነው። ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ዘር ማባዛት አለመቻል፣ የበጀት እጥረት፣ ጥራቱን የጠበቀ የዘር ማሸጊያ አለማዘጋጀት፣ የቤተ ሙከራ (ላብራቶሪ) መፈተሻ ጉድለት፣ ሕገ ወጥ የዘር ዝውውር፣ ምቹ የሆነ የዘር መሬት አለመምረጥ፣ የዘር ማበጠሪያ (ማዘጋጃ) መሳሪያ እጥረት፣ ደረጃውን የጠበቀ የዘር ማከማቻ መጋዝን አለማሟላት እና መሰል ችግሮች ለዘር ጥራት እና ብዜት ፈተና መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ባለሙያው እንዳብራሩት የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ማፍለቅ እና ማላመድ ላይም ድክመቶች እንዳሉ አመላክተዋል።
ዘርን ለምግብነት ማዋል፣ ከባዕድ ነገር ጋር መቀላቀል እንዲሁም ማሸጊያዎችን በመጠቀም አስመስሎ ማቅረብ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ማዘዋወር፣ ቀለም በመቀባት ዘር ያልሆነን ዘር ነው ብሎ ለአርሶ አደሩ መሸጥ በምርታማነት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል:: እንደ አቶ ሰለሞን ሽገድብ ማብራሪያ የግብርና ምርት፣ ጥራት እና ደህንነት ጉዳይ በአንድ ተቋም ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ የሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ፣ ድጋፍ፣ ትብብር እና ቅንጅት ይጠይቃል። በመሆኑም እነዚህን ጉድለቶች በመለየት ከአምራቾች ጋር ውይይት በማድረግ ለማስተካከል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በትኩረት እየሠራ ስለመሆኑ አመላክተዋል።
በውይይት መድረኩ ከተሳተፉት የዘር ጥራት ደረጃን ካሟሉት ዘር አምራቾች መካከል በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚገኘው የአየሁ እርሻ ልማት አንዱ ነው። የእርሻ ልማቱ ሥራ አስኪያጅ ማስረሻ እንግዳ ለበኵር እንደተናገሩት የእርሻ ልማቱ በስድስት ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ጥራቱን የጠበቀ ዘር እያመረተ ነው። የክልሉን የዘር አቅርቦት ችግር ለመፍታት በትኩረት እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል። ዘር የማምረት፣ የማበጠር፣ የማሸግ እና የማሠራጨት ሥራዎችንም ያከናውናል ብለዋል።
ድርጅቱ ከውጭ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የምርጥ ዘር ፖኬጅን በማሟላት ጥራት ያለው ዘር እያመረተ መሆኑን ጠቁመዋል። አዳዲስ የውጭ ዝርያዎችን ጨምሮ በማባዛት፣ በማምረት እና ለአርሶ አደሮች በማሰራጨት የክልሉን የዘር አቅርቦት ችግር ከመሠረቱ ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህ ዓመት ከዛምቢያ መነሻ ዘር በኃላፊነት በማምጣት ቢ ዜድ ኤም ኤች (BZMH) 721 የተባለ ጥራቱን የጠበቀ ሌሎች ዘሮችን ሊተካ የሚችል የበቆሎ ዝርያ እና በሄክታር በአማካኝ እስከ 120 ኩንታል ሊያስገኝ የሚችል ምርታማ ዘር በ300 ሄክታር እየለማ መሆኑን ገልፀዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን የጉና የዘር ብዜት እና ግብይት ኅብረት ሥራ ዩኒየን የጥራት ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ አቶ ያለው ኀይሌ ለበኩር እንዳሉት ድርጅቱ ምርጥ ዘርን በማባዛት እና በማምረት ስምንት ዓመታትን አስቆጥሯል። ጤፍ፣ ሩዝ፣ የቢራ ገብስ፣ ስንዴ እና በቆሎን ጨምሮ ከስድስት በላይ የአዝርዕት ዘሮችን በጥራት እያባዛ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በስድስት ሰብሎች 47 ሺህ ኩንታል ዘር ሰብስቦ ለአርሶ አደሩ አሰራጭቷል።
ጥራት ያለው ዘር ለማምረት በክልሉ የተቀመጡ የዘር ጥራት ደረጃዎችን አሟልቶ እየሠራ ስለመሆኑም አቶ ያለው የተናገሩት በቀጣይም ከዚህ በበለጠ ጥራት ያለው ምርጥ ዘር በማቅረብ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚተጋ ቃል ገብተዋል።
የአማራ ክልል የግብርና ጥራትና ደህንነት ባለሥልጣን ኃላፊ ፈንታሁን ስጦታው ጥናቶችን ዋቢ አድርገው እንዳብራሩት ምርጥ ዘር መጠቀም ከ30 እስከ 50 በመቶ ምርት ይጨምራል። የክልሉ የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ ሥርጭት እና አጠቃቀም እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም አሁንም የተጠቃሚውን ፍላጎት በተሟላ ሁኔታ ለማርካት አልተቻለም።
የክልሉን የምርጥ ዘር ተደራሽነት ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል። ምርጥ ዘር በወቅቱ፣ በዓይነት፣ በብዛት እና በጥራት ለተጠቃሚው ማቅረብ ከተቻለ የክልሉን የሰብል ምርታማነት ማሳደግ እንደሚቻል አብራርተዋል።
እንደ አቶ ፈንታሁን ገለጻ በክልሉ 10 ሺህ 677 ሄክታር መሬት ለምርጥ ዘር አልሚዎች ዘር እንዲያለሙበት ተሰጥቷል። ነገር ግን በምርጥ ዘር እየለማ ያለው ሦስት ሺህ 889 ሄክታር መሬት ብቻ ነው። በመሆኑም ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር በባለሃብቶች እጅ ያለውን መሬት በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ ነው። የዘር ብዜት መሬት ያላገኙት ዘር አልሚዎችም ምቹ መሬት እንዲያገኙ ለማድረግ በቀጣይ በትኩረት ይሠራል::
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሚመረተውን ዘር በየደረጃው ቁጥጥር እንደሚያደርግ የተናገሩት አቶ ፈንታሁን ጥራት የሌለው ዘርን የሚያመርቱ እና የሚያከፋፍሉ ሲገኙ ርምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝበዋል:: ዘር አምራቾች ዕውቀትን እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም አርሶ አደሮችን ለውጤት የሚያበቃ ጥራቱን የጠበቀ ዘር በማምረት ማቅረብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
እንደ አቶ ፈንታሁን ማብራሪያ በክልሉ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥ የዘር ዝውውር ለመከላከል እየተሠራ ነው። በአንድ አንድ የግል ድርጅቶች ላይ ትርፍን ብቻ መሠረት በማድረግ ከማሳ ጀምሮ እስከ መሰብሰብ እና ማከማቸት ባሉት ሂደቶች በርካታ ችግሮችም አሉ። ይህ መንገድ ትክክል አለመሆኑን በመረዳት ወደ ትክክለኛው መስመር መመለስ ይገባል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ለባለሥልጣኑ ብቻ የሚተው ሥራ ባለመሆኑ የሚመለከታቸው አጋር እና ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አቶ ፈንታሁን አሳስበዋል:: ችግሩን በማያርሙ አምራቾች ላይ አስተማሪ ርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል። ጥራቱን የጠበቀ ዘር እንዲመረት እና ተጠያቂነትን በማስፈን አርሶ አደሩ ምርታማ እንዲሆን መሥራት ይገባልም ነው ያሉት።
በዘር አምራቾች የሚታዩ አጠቃላይ ሁኔታዎችን በመገምገም እንደ ክልል ጥራት ያለው ዘር ለማቅረብ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል። አርሶ አደሩ ክረምት ከበጋ ደክሞ ሠርቶ ጥራቱን ባልጠበቀ ዘር ለኪሳራ መዳረግ እንደሌለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘር ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ፈንታሁን የዘር ጥራትን በዘላቂነት በማሻሻል በጥራት፣ በዓይነት፣ በብዛት እና በወቅቱ ለተጠቃሚው እንዲደርስ ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር ጠንካራ የጥራት ቁጥጥር ሥርዓት መገንባት እንዳለበት ተናግረዋል። አምራች ድርጅቶች የአርሶ አደሮችን ልፋት እና ተጠቃሚነት አስበው መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል። የምርምር ተቋማት የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ማፍለቅ እና ማላመድ እንደ ሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል::
የዘር ሕጎች በተገቢው ሁኔታ እንዲታወቁ ማድረግ፣ በዘር ሕጎች በተፈጠረው ዕውቀት ልክ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ፣ የዘር አምራች ድርጅቶችን ለተሻሉት ዕውቅና መስጠት እንዲሁም ከስህተታቸው የማይታረሙትን ደግሞ ማሰናበት፤ የዘር ማዘጋጀት፣ ማከማቸት እና ላብራቶሪ ፍተሻ ራሱን በቻለ ብቃት እንዲሠራ ማድረግ፣ ለቤተሙከራ ዕቃዎች የደረጃ መግለጫ (ስታንዳርድ ስፔሲፊኬሽን) ማዘጋጀት፣ ለምርምር ተቋማት፣ ለዩኒቨርሲቲዎች እና ለመንግሥት ኢንተርፕራይዞች የብቃት አሰጣጥ ሂደትን ወጥ ማድረግ የቀጣይ የትኩረት ተግባራት መሆናቸው ተመላክቷል።።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም