የዘንድሮውን የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ማን ያነሳል?

0
106

 ሰማዩ ከበድ ብሎ የዝናብ ጠብታዎች በስታዲየሙ የብርሃን ዘንግ ውስጥ እንደ አልማዝ በሚንጠባጠቡበት ምሽት የቤኔፊካው ዩክሬናዊ ግብ ጠባቂ አናቶሊ ትሩቢን አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል። ኹነቱም ከስቴዲየም አልፎ በዓለም የእግር ኳስ አፍቃሬዎች ዘንድ ዋና መነጋገሪያ ሆኖ ሰነብቷል። 98ኛው ደቂቃ ላይ የደረሰው ጨዋታ ሊጠናቀቅ ዳኛው ፊሽካውን በአፉ በደገነበት ቅጽበት ትሩቢን የራሱን የግብ ክልል ለቆ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በመሮጥ የእግር ኳስን አስደሳች ገጽታ አሳየ። አናቶሊ ትሩቢን በግንባሩ ገጭቶ ኳሷን የሪያል ማድሪድ መረብ ላይ ሲያሳርፍ የተሰበረው የሎስብላንኮዎቹ ልብ ብቻ ተሰበረ፤ ያ ግብ ለዐስርት ዓመታት የአውሮፓ እግር ኳስን ተቆጣጥሮት የነበረው የበላይነት እያከተመ መሆኑን ያሳየ ምልክት ነበር።

የዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተለየ፣ ያልተጠበቀ እና አዲስ ገጽታን የተላበሰ መሆኑን አብስሯል። የአውሮፓ እግር ኳስ አሁን የሽግግር ወቅት ላይ ይገኛል፤ አሮጌዎቹ ነገሥታት እየደከሙ አዲሶቹ ደግሞ ጡንቻቸውን እያፈረጠሙ ይገኛሉ። አሁን ወደ ቡዳፔስት ፑሽካሽ አሬና የሚወስደው መንገድ ክፍት ሆኗል፤ በመንገዱ ግን የአዲስ ነገሥታት ኮቴ ዳና እየሰማን መሆኑን የጎል ዶት ኮም መረጃ ያመለክታል።

2025/26 ሻምፒዮንስ ሊግ በአሰልጣኞች ታክቲክ ረገድም አዳዲስ አብዮቶችን እያሳየን ነው። አርሰናል እና ባርሴሎና የመከላከል መስመራቸውን ወደ መሀል ሜዳ በማስጠጋት ተጋጣሚን በኦፍሳይድ ወጥመድ የመያዝ ስልት በስፋት እየተጠቀሙ ነው ። ይህም እግር ኳስን ወደ አዲስ የቼዝ ጨዋታ ቀይሮታል። በዚህ የለውጥ ማዕበል ውስጥ በአውሮፓ እግር ኳስ በአሁኑ ሰዓት በብዛት እና በጉልህ እየተነሳ ያለው ስም አርሴናል ነው። ሚኬል አርቴታ በሰሜን ለንደን የገነቡት ይህ ፕሮጀክት አሁን ከእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አልፎ አውሮፓን ለመቆጣጠር በትክክለኛ ጉዞ ላይ መሆኑን የኦፕታ አናሊስት መረጃ ያስነብባል። አርሴናል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሻምፒዮንስ ሊግ የሊግ ምዕራፍ ስምንቱንም ጨዋታዎች በማሸነፍ 24 ነጥቦችን በመሰብሰብ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅሏል። ይህ የአርሴናል  ስብስብ ጥሩ እግር ኳስ ተጫዋች ግን ለስላሳ ከሚለው የድሮ ትችት ተላቆ ወደ ጨካኝ አሸናፊነት የተሸጋገረበትን ምዕራፍ በግልጽ ያሳያል።

የመድፈኞቹ ጥንካሬ ዊሊያም ሳሊባ እና ጋብሪኤል ማጋሌስ የፈጠሩት የማይደፈር የመከላከል አጥር ነው። በአውሮፓ ውስጥ እጅግ ጠንካራው ይህ የኋላ ክፍል  በስምንት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ነው የተቆጠሩበት፤ ቡድኑ የታላቁን መድረክ ዋንጫ ለማንሳት የሚያስችል አቅም ላይ መሆኑን ያሳያል። “ማጥቃት ጨዋታን አሸነፊ ያደርጋል፤ መከላከል ግን ዋንጫን አሸናፊ ያደርጋል” የሚለው የሰር አሌክስ ፈርጉሰን ዝነኛ አባባል  ለአርቴታ ቡድን ዘንድሮ እየሰራ ይመስላል።

ከዴክላን ራይስ እስከ ሚኬል ሜሪኖ፣ ከቡካዮ ሳካ እስከ ጋብሪኤል ማርቲኔሊ፣ እንዲሁም እንደ ዙቢሜንዴ፣ ቲምበር እና ራያ ያሉ ተጫዋቾች ያሳዩት ብቃት ቡድኑ በጉዳት እና በድካም እንዳይዝል አድርጎታል። ኦፕታ ሱፐር ኮምፒውተር ዘንድሮ  አርሴናል የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን የማሸነፍ እድሉ  30 ነጥብ 64 በመቶ እንደሆነ ያስነብባል። ይህ ቁጥር የሚያሳየው አርሴናል በዘንድሮው ዓመት በመድረኩ አጃቢ ሳይሆን ዋነኛ ተፎካካሪ መሆኑን ያሳያል።

ሌላው የጀርመኑ ኃያል ክለብ ባየር ሙኒክ ዘንድሮ በሻምፒዮንስ ሊጉ መደረክ ወደ ቀድሞ ግርማ ሞገሱ ተመልሷል። ባለፈው የውድድር ዘመን በአውሮፓ መድረክ ደካማ  የነበረው ባየር ሙኒክ በዚህ ዓመት በቪንሰንት ኮምፓኒ ስር አዲስ እና አስፈሪ ማንነትን ተላብሶ ብቅ ብሏል። ኮምፓኒ ወደ አልያንዝ አሬና ሲመጣ ብዙዎች ቅንድባቸውን ከፍ ዝቅ አድርገው ተጠራጥረውት እንደነበር አይዘነጋም፤ ነገር ግን እርሱ ያመጣው ዘመናዊ እግር ኳስ ከባቫሪያኑን ክለብ ባህል  እና መንፈስ ጋር ተዋህዶ ውጤታማ ሆኗል።

ኮምፓኒ ከቀድሞው አሰልጣኝ ቶማስ ቱህል በተለየ ቡድኑ በተዳጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል እንዲደርስ እና ኳስ ሲያጣ በከፍተኛ ጫና መልሶ እንዲቀማ ያደረገ ታክቲካዊ ለውጥ አድርጓል። ይህ ደግሞ በተለይ እንደ ጃማል ሙሲያላ እና ማይክል ኦሊሴ ላሉ ፈጣን  ተጫዋቾች ተመችቷቸዋል። የባየር ሙኒክ ትልቁ መሳሪያ ግን እንግሊዛዊው አጥቂ ሃሪ ኬን ነው። ኬን በእግር ኳስ ህይወቱ ያጣውን የዋንጫ ክብር ለማግኘት የሚያደርገው ተጋድሎ ለመላው ቡድኑ ተጨማሪ ጉልበት ሆኗል። እስካሁን ባለው የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ብቻ 11 ግቦችን ማስቆጠሩ በወሳኝ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ላይ ልዩነት ፈጣሪ እንደሚሆን ያመላክታል።

ኦፕታ ለባቫሪያኑ ክለብ የሰጠው 15 በመቶ ግምት ከአርሰናል ቀጥሎ ለዋንጫ የታጨ ሁለተኛው ክለብ አድርጎታል። የጀርመኑ ክለብ በኤምሬትስ ስታዲየም ሽንፈትን ቢቀምስም ያ ጨዋታ ትልቅ ትምህርት እና መነሳሳት እንደሆናቸው ኮምፓኒ መናገሩ አይዘነጋም። እናም ባቫሪያውያኖቹ አሁን ያላቸው የቡድን ስነ ልቦና ዋንጫውን ወደ ሙኒክ ከተማ ለመመለስ ያለሙ ይመስላል።

የዘንድሮው የታላቁ መድረክ ፉክክር ትልቁ ድራማ እና መነጋገሪያ የአርሴናል እና የባየርን ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን የሪያል ማድሪድ እና የማንቸስተር ሲቲ መዳከም እና ከዙፋናቸው መውረድ ጭምር ነው። የሁለቱ ክለቦች አቋም መዋዠቅ ልክ እንደ ሮማ ግዛት ውድቀት ቀስ በቀስ ሲንከባለል መጥቶ አሁን ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል። በአልቫሮ አርቤሎዋ የሚመራው ሪያል ማድሪድ ትልቁ ችግሩ በሁለተኛው የሜዳ ክፍል ነው። የቶኒ ክሩስ እና የሉካ ሞድሪች ዘመን ካበቃ በኋላ እንደ ጁድ ቤሊንግሀም እና ፌዴ ቫልቬርዴ ያሉ ተጫዋቾች ቢኖሩም የቡድኑን ሚዛን የሚጠብቅ እና የጨዋታውን ምት የሚቆጣጠር ሁነኛ ተጫዋች ጠፍቷል።

ማድሪድ ከኳስ ውጪ በሚሆንበት ጊዜ የሚታይበት የሜዳ ላይ ክፍተት እና የተጫዋቾች መዘናጋት ከቤኔፊካ ከፈረንሳዩ ክለብ ሊል እና ከኤሲ ሚላን ጋር በነበረው ጨዋታ በግልጽ ታይቷል። የኦፕታ አንድ ነጥብ 66 በመቶ ግምትም ይህንን ያረጋግጣል። ሎስብላንኮዎቹ ዘንድሮ በወጣት ጉልበት ባላቸው እና በታክቲክ በበሰሉ ቡድኖች እየተፈተነ ነው። የሊዝበኑ ሽንፈት ንጉሡ አርጅቷል፤ ዘውዱም እየከበደው መጥቷል የሚለውን ሀሳብ በደንብ ያጠናክራል።

የፔፕ ጋርዲዮላው ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ የመሰላቸት እና የአካል ብቃት ችግር እንዳለበት ጎል ዶት ኮም አስነብቧል። ላለፉት አምስት ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ እና ጫና ውስጥ የተጫወቱት ሮድሪ እና በርናርዶ ሲልቫ ዘንድሮ ጉልበታቸው ዝሏል፤ የማሸነፍ ረሃባቸውም የቀነሰ ይመስላል። ምንም እንኳን ኤርሊንግ ሀላንድ ግብ ማስቆጠሩን ቢቀጥልም ቡድኑ እንደ ድሮው ተጋጣሚን መፈናፈኛ የማሳጣት እና የመቆጣጠር አቅሙ ወርዷል።

ዐስር ነጥብ 99 በመቶ ዋንጫውን የማሸነፍ እድል እንዳለው ኦፕታ አናሊስት ግምቱን አስቀምጧል። ጋርዲዮላ በቡድኑ ውስጥ እስካለ ድረስ ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ ከግምት ውጪ ማድረግ ባይቻልም በማንቸስተር ከተማ የወጣችው ፀሐይ ግን እየጠለቀች እንደሆነ ምልክቶች እየታዩ ነው።

በጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ፉክክሩ ይበልጥ እየከረረ እንደሚመጣ በርካታ መረጃዎች ያመለክታሉ። በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ላይ ስህተት አይታረምም፤ ሁለተኛ እድልም የለም። እናም በዚህ ወሳኝ ወቅት የአርሴናል ትልቅ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ይጠበቃል፤ የባየር ሙኒክ ልምድ ደግሞ እዚህ ላይ ወሳኝ ይሆናል ተብሏል።

ይሁን እንጂ ያልተጠበቀ ቡድን ዋንጫ ሊያነሳ እንደሚችል መዘንጋት የለብንም። እ.አ.አ በ2004 ፖርቶ በሞሪንሆ አማካኝነት ማንም ሳይገምተው የመድረኩን ዋንጫ ማንሳቱ የሚታወስ ነው። እ.አ.አ 2012ትም ዲ ማቲዮ ቼልሲን ተረክቦ ሳይጠብቅ ዋንጫውን ማንሳቱን የስታንፎርድ ብሪጅ ታሪክ ይዘክረዋል። በዘንድሮው (2025/26) ይህ ታሪክ ሊደገም ይችል ይሆን? አብረን የምናየው ይሆናል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here