በሪሰርች ጌት ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የአካዳሚክ ውጤት ለአንድ ተማሪ ቀጣይ የትምህርት ጉዞ ወሳኝ መለኪያ ነው። የዛሬ ውጤት የጉዞው ማብቂያ ሳይሆን ለቀጣዩ ስኬት እንደ መመርመሪያ እና መነሻ ተደርጎ የሚወሰድ መሆን እንዳለበትም ጽሁፉ አስፍሯል::
የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ውጤት እንዴት እና በምን አግባብ ለቀጣይ ውጤት እንደሚያበቃ የድረ ገጹ ጥሁፍ በጥልቀት ያስረዳል:: የተገኘውን ውጤት በጥልቀት መተንተን ደግሞ ክፍተቱን በመረዳት ለምን? የሚለውን ጥያቄ ለማንሳት ያስችላል:: ውጤቱ ዝቅ ያለባቸውን ቦታዎች ለይቶ ምክንያቱን ማወቅ መፍትሔውን በግማሽ ያቃልለዋል። ችግሩ የመጣው ከጥናት ጊዜ ማነስ፣ ጥያቄዎቹን ከለመረዳት ወይስ የትምህርት አሰጣጥ ክፍተት ነበር የሚሉትን ሐሳቦች ሁሉ መርምሮ ምላሽ ለመስጠት የውጤት ትንተና ትልቅ አቅም ይሆናል::
የቀደመው አካሄድ የሚፈለገውን ውጤት ማስገኘት ካልቻለ መንገዱን መቀየር የግድ እንደሚልም ትምህርታዊ ሐሳቦች ይጠቁማሉ:: ለጥናት በየቀኑ የተወሰነ ሰዓት መመደብ፣ የጥናት ዘዴን ማስታወሻ ከመያዝ ባለፈ ለሌላ ሰው እንደማስተማር አድርጎ መለማመድ፣ ግልጽ ያልሆኑ ነጥቦችን መምህራንን ወይም ጓደኞችን በጊዜ መጠየቅ እንደ መፍት መውሰድ ይጋበል:: ግብ ማስቀመጥ ለተሻለ ውጠየት ያበቃል::
ትልቁ ስህተት ካለፈው ስህተት አለመማር ነው። የዛሬው ውጤትህ ትላንት የነበረህን ዝግጅት እንጂ፣ የነገውን ማንነትም ሆነ አእምሯዊ ብቃትን አይወስንም።
ተማሪዎችም በእስካሁን ጉዟቸው ያስመዘገቧቸውን ውጤቶች መሠረት አድርገው ለቀጣይ የተሻለ መሆን በዕቅድ እየተመሩ መሆኑን ተናግረዋል::
በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ የሚገኘው የይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዋ ቢታኒያ ብርሀኑ ቀድሞ የነበራት የተሻለ የትምህርት አቀባበል ትምህርት ቤቱን እንድትቀላቀል እንዳስቻላት ተናግራለች:: ከታችኛው የክፍል ደረጃ ጀምሮ የነበራት ጠንካራ የጊዜ አጠቃቀም፣ የአጠናን ስልት፣ የወላጅ ክትትል እና አላማ ለውጤት ያበቋት ምክንያቶች ናቸው::
ትምህርት ቤቱ በየዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያስፈትናቸውን ሁሉንም ተማሪዎች ማሳለፉ መነሳሳት እንደፈጠረባት ተናግራለች:: ከዚህ በተጨማሪም በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ያስመዘገበችው ውጤት መልካም መሆኑ ለቀጣይ መነሳሳት እንደፈጠረባት ነው የተናገረችው:: የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ክትትል ለተመዘገበው ውጤት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግራለች::
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የመሽሃ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪው ኤፍሬም ኃይሌ በበኩሉ በቀጣይ የሚሰጠውን ሀገር አቀፍ ፈተና መሠረት በማድረግ እያከናወነ ያለው ዝግጅት ከወዲሁ ትልቅ ተስፋን እንዲሰንቅ እንዳደረገው ተናግሯል:: ከመሠረቱም ቢሆን የተሻለ የመረዳት አቅም ያለው ተማሪው ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እየተሸለመ መምጣቱን አስታውቋል:: በክፍል ደረጃ የሚሰጡ ፈተናዎችን የራሱ ዝግጁነት መገምገሚያ አድርጎ የሚቆጥረው ኤፍሬም ዋና ግቡ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተሻለ ውጤት አስመዝግቦ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን መቀላቀል እንደሆነም አስታውቋል:: መምህራን በየምዕራፉ ጥያቄዎችን እያዘጋጁ መስጠታቸውም ለአላማው ዳር መድረስ ትልቅ አቅም እንደሚሆነው ያምናል::
በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የተማሪዎችን ተሳትፎ እና ውጤታማነት ለማረጋገጥ የመምህራን እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት (ወላጆች፣ የትምህርት አመራሮች እና አማካሪዎች) ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልልን ጨምሮ በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ተጠናቆ የሁለተኛው ግማሽ ዓመት መማር ማስተማር እየተከናወነ ይገኛል:: በክልሉ የሚገኙ ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና ወረዳዎችም የግማሽ ዓመት የትምህርት ሥራቸውን በመገምገም የጠለያዩ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል::
የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የትምህርት መምሪያ ኅላፊ ደስታ አስራቴ በበኩላቸው ትምህርት የብዙ አጋር አካላትን ተሳትፎ የሚፈልግ ጉዳይ ነው ብለዋል። በግማሽ ዓመቱ መልካም የትምህርት አፈጻጸም የነበር ቢሆንም እንኳን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ላይ ግን በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል። ችግሩን ለመቅረፍ ትልቅ ኅላፊነትን መውሰድ አግባብ ነው ተብሏል። የክልል አቀፍ እና የሀገር አቀፍ ተፈታኝ ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡም ትኩረት እንደተሰጠ በግምገማ መድረኩ ላይ ተነስቷል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያም ግማሽ ዓመቱን ቃኝቶ የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል:: የትምህርት መምሪያ ኃላፊው አቶ ፀጋዬ እንግዳወርቅ ትምህርት እንደ ሀገር ህልውናን አስጠብቆ ለመቆየት እንዲሁም ካለንበት ቀውስ ለመውጣት ዋነኛው የመወዳደሪያ መስፈትና ቁልፍ መሆኑን ተገንዝበን ተማሪዎች ውጤት ላይ እጅ እና ጓንት ሆኖ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል:: የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሪ ቁጥር መቀነስ የትምህርት ቤቶቹን ሥጋት ከመሆን አልፎ ዞኑን የተማረ ኃይል እንዳይኖረው የሚያደርግ አደገኛ ችግር መሆኑን አስታውቀዋል:: በቀጣይ የትምህርት ዘርፉ ወላጆችን እና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር ርብርብ ማድረግ ይገባልም ብለዋል::
አሁናዊ አቅጣጫው በትምህርት ላይ ያሉትን ተማሪዎች ለውጤት ማብቃት መሆኑን ተናግረዋል:: ባለፈው ዓመት በተሰሩ ጠንካራ ሥራዎች በተለይ በ12ኛ ክፍል የማለፊያ ውጤት ምጣኔን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ችለናል ብለዋል።
ያም ሆኖ የዞኑ ተማሪዎች ውጤት ከክልሉ የማለፊያ ውጤት ምጣኔ ጋር ስላልደረሰ አሁን ላይ መግባባት ያለብን ከቻልን ከክልሉ በላይ ካልሆነ ደግሞ ከክልሉ እኩል ለመሆን መሆን ይገባል ነው ያሉት:: ይህ እንደሚቻል ደግሞ ክክልሉ የማለፊያ ምጣኔ በላይ ያሳኩ እና ምርጥ ተሞክሮ ያላቸው ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን አስታውቀዋል::
በአጠቃላይ ተማሪዎች ከመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የጥናት ስልት ውጤታማነትን፣ የጊዜ አጠቃቀምን፣ የትምህርት አይነቶች ልዩነትን፣ ራስን የመምራት ብቃትን ይማራሉ:: እነዚህንም እንደ አስፈላጊነቱ በመከለስ ለተሻለ ውጤት መብቃት እንደሚችሉ ሪሰርች ጌት ላይ የወጣው ጥናት ጠቁሟል::
ሪሰርች ጌት ድረ ገጽ የመጀመሪያው ውጤት ትልቅ ትምህርት መሆኑን መምህራን፣ ወላጆች እና የትምህርት ባለድርሻ አካላትም በትኩረት በመመልከት ለተማሪዎች ብቁነት ሊተጉ እንደሚገባ ምክረ ሐሣቡን ጋራል:: በለይ መምህራን ከተማሪዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ የቸልተኝነት ምልክቶችን ቀድሞ የመለየት ቀዳሚ ኃላፊነት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁሟል:: ተማሪው የመጀመሪያውን ዋና ፈተና እስኪወስድ ከመጠበቅ ይልቅ ቀድሞ የክፍል ስራዎችን በመስጠት ውጤታቸውን ማሳወቅ፤ በክፍል ውስጥም ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያደርጉ የማስተማር ስነ ዘዴዎችን በመጠቀም የተማሪውን ስሜት ከትምህርቱ ጋር ማገናኘት እንደሚጠበቅባቸው ተመላክቷል።
ወላጆችም ለልጆቻቸው የስነ-ልቦና ድጋፍ በመስጠት፣ ውጤትን በቅርበት በመከታተል እና ከመጠን በላይ ጫና ባለመፍጠር ለተሻለ ውጤት መመዝገብ የበኩላቸውን እንዲወጡ የድረ ገጹ የጥናት ውጤት መክሯል::
መረጃ
የውጤት ትንተና ፋይዳዎች
የቀጣይ ትምህርት መሠረት ይሆናል
የጥናት ስልትን ለማስተካከል
ውጤትን ማሻሻል
ማህበራዊ እና አካዳሚያዊ ትስስር ለመፈተሸ
ምንጭ፡- ሪሰርች ጌት፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


