የሁለት ሺህ ሀያ ሦስቱ የአፍሪካ ዋንጫ በ ኮትዲቯር አሸናፊነት ተጠናቋል። ግዙፉ የእግር ኳስ ድግስ ትንፋሽን የሚያስውጡ፣ልብን የሚያሞቁ፣ ያልተጠበቁ ድራማዊ ክስተቶች ታይተውበት አልፏል። የአፍሪካ የእግር ኳስ አውራ ብሄራዊ ቡድኖች ከውድድሩ ውጪ የሆኑበት፣ ጨዋታዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በሴት ዋና ዳኝነት የተመሩበት፣ የተንቀሳቃሽ ምስል ዳኝነት (VAR ) ቴክኖሎጂ ሙሉ በሙሉ ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ የሆነበት ነው፤ 34ኛው የኮትዲቯሩ የአፍሪካ ዋንጫ። ኮትዲቯራውያን ለዚህ ድግስ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ውጪ አድርገዋል።
ይህ ድካማቸው እና ልፋታቸው መና ሳይቅር በዋንጫ ታጅቦ ተጠናቋል። አስደናቂ በነበረው የእግር ኳስ ድግስ ዝሆኖቹ ህዝባቸው እና ደጋፊያቸው የሚኮራበትን አዲስ ክብረ ወሰንም ጭምር ጽፈዋል። እ.አ.አ በ2006 ግብጽ የመድረኩን ዋንጫ አስተናግዳ ዋንጫውን ካነሳች በኋላ ኮትዲቯር ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደችውን ዋንጫ በማንሳት አዲስ ታሪክ አስመዝግባለች። የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከመጀመሩ በፊት ኦፕታ አናሊስት (OPTA ANALYIST) የተባለው ድረ ገጽ የአፍሪካ ዋንጫውን ማን ሊያነሳ እንደሚችል ግምቱን ሲያስቀምጥ ከሴኔጋል ቀጥሎ ኮትዲቯር 34ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ የማንሳት ሰፊ ዕድል እንዳላት በመረጃው አመላክቶ እንደነበር ይታወሳል። ይሁን እንጂ ኦፕታ አናሊስት ይህንን ግምቱን ቢያስቀምጥም በምድብ ጨዋታዎች የዝሆኖቹ አቋም እምነት የሚጣልበት እንዳልሆነ በማመን ብዙዎቹ የእግር ኳስ ተንታኞች በተለየ ጎራ ተሰልፈዋል።
ዝሆኖቹ በምድብ ጨዋታዎች ደካማ አቋም በማሳየታቸው ምርጥ ሦስተኛ ሆነው ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ የግድ የሌሎቹን ውጤት መጠበቅ ነበረባቸው። በመጨረሻም ተሳክቶላቸው ጥሎ ማለፉ ደርሰዋል። በጥሎ ማለፉም ሁሉንም የምድብ ጨዋታዎች አሸንፈው ጥሎ ማለፉ ከደረሰው የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን ቢገናኙም ዝሆኖቹ ለሴኔጋል እጅ አልሰጡም።
ዕድል የቀናቸው ኮትድቯሮቹ አሸንፈው ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀል ቻሉ። በሩብ ፍጻሜው ማሊን፣ በግማሽ ፍጻሜው ደግሞ ዲሞክራቲክ ኮንጎን በማሸነፍ ለመጨረሻው የፍጻሜ ትንቅንቅ ደርሰዋል። በአራቱም የዓለም ማዕዘን ከአንድ ቢሊዮን ሕዝብ በላይ በተመለከተው የፍጻሜ ጨዋታ የናይጀሪያን ብሄራዊ ቡድን 2ለ1 በማሸነፍ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ የመድረኩን ዋንጫ አንስተዋል።
ኮትዲቯር ከዚህ በፊት በ1992 እና 2015 እ.አ.አ የመድረኩን ዋንጫ ማሳካታቸውን ታሪክ ያወሳል። ብሄራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎው ታሪክ የካበተ ልምድ ካላቸው ሀገራት መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይሰለፋል። 25 ጊዜ በተሳተፈበት መድረክ አስር ጊዜ ግማሽ ፍጻሜ ድረስ ተጉዟል። አራት ጊዜ ደግሞ ለፍጻሜ ቀርቦ ሦሰት ጊዜ በዋንጫ ታጅቦ አጠናቋል። ዘንድሮ ከምድቡ ምርጥ ሦስተኛ ሆኖ አጣብቂኝ ውስጥ በመግባት ጥሎ ማለፍ የደረሰው የኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን ዋንጫውን ያነሳል ብሎ ማንም የገመተ አልነበረም። የዝሆኑ ወድቆ መነሳትም መላው ኮትዲቫራውያንን ጮቤ አስረግጧል። በሄራዊ ቡድኑ በመጨረሻም ህልማቸውን እውን አድርገዋል። ኮትዲቯሮቹ አሠልጣኝ ጂያን ሊዊስ ጋሴትን አሰናብተው ምክትሉን ኤምሬ ፋኤን ቡድኑን እንዲመራ ኃላፊነት ሰጡት። ጊዜያዊ አሰልጣኙ ፋኤም አደራውን ተረክቦ ለኮትዲቫራውያኑ ዋንጫውን አስረክቧል። ይህ ደግሞ በዓለም አቀፍ ውዽድር ዋንጫ ያነሳ ብቸኛው ጊዜያዊ አሰልጣኝ አድርጎታል።
የሀገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን አሰልጣኙን ያባረረበት ምክንያት በዚህ ውድድር መጥፎ የተባለውን ውጤት በማስመዝገባቸው ነው። ኢኳቶሪያል ጊኒ በምድብ ጨዋታው ዝሆኖችን 4ለ0 ማሸነፏ ለአሰልጣኙ መነሳት መንሴው እንደሆነ ተዘግቧል። ከዚህ በፊት በመድረኩ ታሪክ የትኛውም ሀገር በውድድሩ መሀል አሰልጣኝ ያሰናበተ ብሄራዊ ቡድን የለም። በስብስብ ደረጃ የዝሆኖቹ ስብስብ ወርቃማ ተብሎ የሚጠራ ነው። ፍራንክ ኬሴዬ ፣ ማክስል ግራዴል፣ ሲሞን አዲንግራ፣ ሰባስቴያን ሀለር፣ ሴኮ ፎፎናን እና የመሳሰሉትን አካቷል።
በእነዚህ ኮከቦች መሪ ተዋናይነት፣ በዲዲየር ድሮግባ አበረታችነት እና መካሪነት በመታገዝ ከጨዋታ ጨዋታ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በመረዳት ለድል በቅተዋል። በአላሳን አውታር ስቴዲየም ሰማይ ስር የደጋፊዎቹ ፌሽታ እና ደስታም አስተጋብቷል። ፊታውራሪው ሰባስቲያን ሀለር ደግሞ የመድረኩ የሰርክ ወግ ሆኗል። ግዙፉ አጥቂ ሰባስቲያን ሀለር በግማሽ ፍጻሜ እና በፍጻሜ ጨዋታዎች የማሸነፊያ ግቦችን ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።
ካንሰርን ያሸነፈው የ28 ዓመቱ አጥቂ ኮትዲቯራውያን ሦስተኛቸውን የመድረኩን ዋንጫ እንዲያነሱ ከፍተኛ ድርሻ ተወጥቷል። ተጫዋቹ በ2022እ.አ.አ ከአያክስ አምስተርዳም ወደ ቦርሲያ ዶርትሙንድ ኢዱና ሲግናል ፓርክ ካመራ በኋላ የቴስቲኩላር ካንሰር ህመም አጋጥሞት እንደነበር ይታወሳል። ይህ ዜና ሲሰማም የእግር ኳስ ህይወቱ በ28 ዓመቱ እንደሚቋጭ ተገምቶ ነበር። ነገር ግን የተገመተው ሳይሆን ቀርቶ ከ18 ወራት በኋላ ካንሰርን ድል በመንሳት ወደ ሜዳ የመመለሱን መልካም ዜና የስፖርት የመገናኛ አውታሮች አበሰሩ። ያ አስቸጋሪ እና ጭንቅ ጊዜ አልፎ በኮትዲቯሩ ድግስ ተጫዋቹ ጀግና መሆኑን አሳይቷል።
በምድብ ጨዋታዎች ጉዳት ገጥሞት የነበረው ሀለር በወሳኙ የግማሽ ፍጻሜ እና የፍጻሜ ጨዋታ የማሸናፊያ ግቦችን በማስቆጠር ሀገሩን ለትልቅ ክብር አብቅቷል። ከሞት ወደ ህይወት የተሸጋገረው ሰባስቲያን ሀለር ዝሆኑም ከአንቀላፋበት የመነሳቱን ዜና በወሳኝ ግቦቹ አብስሯል።
ሌላኛው የመድረኩ ኮከብ ሲሞን አዲንግራም በዚህ የእግር ኳስ ድግስ ድንቅ ተሰጥኦቸውን ካሳዩ እና ለኮትዲቯር ትልቅ ውለታ ከሠሩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። የ22ዓመቱ የብራይተኑ አጥቂ ከእነ ዲዲየር ድሮግባ እና ያያ ቱሬ በኋላ በሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች እኩል ተወዳጅ የሆነ ተጫዋች ነው። ዘ አትሌቲክም “አዲሱ የኮትዲቯር ጌጥ” ሲል አሞካሽቶታል። ንቁ፣ ፈጣን እና እግር ኳስን በደንብ የተረዳ ሲሉ ብዙዎቹ ይገልጹታል። በፍጻሜው ጨዋታ ባሳየው አስደናቂ ብቃትም ከእድሜው በላይ የበሰለ ተጨዋች ስለመሆኑ አሳይቷል። በሳውዲ ሊግ የሚጫወተው ፍራንክ ኬሲዬም በዚህ ውድድር ድንቅ ብቃታቸውን ካሳዩት ውስጥ ይገኝበታል።
በ1984 እ.አ.አ ኮትዲቯር የአፍሪካ መድረክ ዋንጫን አስተናግዳ እንደነበር ይታወሳል። ስምንት ሀገራት ብቻ በተሳተፉበት የእግር ኳስ ድግስ አስተናጋጇ ሀገር ከምድቡ መሻገር ተስኗት በጊዜ ከውድድሩ ውጪ እንደነበረች የታሪክ ማህደሯ ያሳያል። ከ40 ዓመታት በኋላ ዘንድሮ ድጋሚ ድግሱን በማስተናገድ ዋንጫውን ማንሳት ችላለች። ጠንካራ የነበረው የናይጀሪያ ብሄራዊ ቡድን ሁለተኛ፣ ደቡብ አፍሪካ ሦስተኛ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ አራተኛ ደረጃን ይዘው የዘንድሮው መድረክ ተጠናቋል።
የናይጀሪያ ብሄራዊ ቡድን አምበል እና የመሀል ተከላካዩ ዊሊያም ትሮስት ኢኮንግ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተሸልሟል። የኢኳቶሪያል ጊኒው አጥቂ ኢሚሊያኖ ኑስ በአምስት ግቦች ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ጨርሷል። ተጫዋቹ በኮትዲቯሩ መድረክ ባሳየው ያልተገባ ባህሪ ሀገሩ ኢኳቶሪያል ጊኒ ይህንን አጥቂ ከስብስቧ ማገዷን መረጃዎች አመልክተዋል። የደቡብ አፍሪካው ግብ ጠባቂ ሮዋን ዊሊያምስ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ ሲመረጥ ኮትዲቯራዊው አጥቂ ሲሞን አዲንግራ የወጣት ኮከብ ተጫዋች ክብርን አግኝቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ በእግር ኳስ አሰልጣኝነት ህይወቱ በዋና አሰልጣኝነት ከሩብ ፍጻሜ ጀምሮ ቡድኑን በመምራት በድል ያጠናቀቀው አምሬ ፋኤ የውድድሩ ምርጥ አሰልጣኝነት ክብርን ተጎናጽፏል። የ2025ቱን የአፍሪካ ዋንጫም ከ37 ዓመታት በኋላ የሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ ድጋሚ የምታስተናግደው ይሆናል።
ዘአትሌቲክን ስካይ ስፖርት እና ቢቢሲ ስፖርትን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም