የዝነኛው ክለብ ውድቀት

0
154

በደቡብ አሜሪካ ስድስተኛው ዝነኛ ፣ስመ ጥር እና ስኬታማ ክለብ ነው፤የዓለምን እግር ኳስ የተቆጣጠሩ የላቀ ተሰጥኦ ያላቸውን ተጫዋቾችንም አፍርቷል። በብራዚል ከሚገኙ ሦስት አንጋፋ እና ኃያል ክለቦች መካከል በቀዳሚነት ይቀመጣል። የ20ኛው ክፍለ ዘመን ቀዳሚው ስኬታማ ክለብ ተብሎ ተወድሷል። በማራኪ አጨዋወት ባህሉ የሚታወቁ ብዙ ደጋፊ ካላቸው ክለቦች ቀዳሚውም ነው- ሳንቶስ እግር ኳስ ክለብ።
በቅጽል ስሙ አሳው (Fish) ተብሎ የሚጠራው ሳንቶስ ክለብ በብራዚል ውስጥ ሁለተኛው ውድ ስብስብ ያለው ክለብ ነው። በዓለማችን ደግሞ 38ኛው ውድ ስብስብ የያዘ ክለብ መሆኑን ብራንድ ፋይናንስ የተባለ ተቋም መረጃ ያመለክታል። ከተጫዋቾች እና ከትኬት ሽያጭ ፣ ከማስታወቂያ እና መሰል ገቢዎች በዓመት ከፍተኛ ገንዝብ ወደ ካዝናቸው ከሚያስገቡ ክለቦች መካከልም ተቋሙ አራተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል።
ሚያዚያ 14/ 1912 እ.አ.አ በሰሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ የግዙፏ ስመ ጥር ታይታኒክ መርከብ የመስመጥ ወሬ በመላው ዓለም ተሰማ። ይህ ቀንም ለምድራችን ትልቅ ሀዘን ሆኗል። በደቡብ ምስራቅ ለምትገኘው ሳንቶስ ከተማ ለሚኖሩት ሕዝቦች ግን ይህ ዕለት ግማሽ ሀዘን ግማሽ ደስታ ሆኖ አልፏል። በዕለተ ቀኑ አካባቢያቸውን፣ ሕዝባቸውን የሚወክል የእግር ኳስ ክለብ ተመስርቷልና ነው። አንደኛው ግዙፍ ሲሰጥም ሌላኛው ተወልዷል፡፡
በዓለማችን ተወዳጅ ከሆኑ ስፖርቶች መካከል የእግር ኳስ ስፖርት በቀዳሚነት ይቀመጣል። ይህንን ስፖርትም እንግሊዛውያን እንደፈጠሩት ይነገራል። ስፖርቱ በብራዚል አድጎ ፣አውሮፓን ተሻግሮ ድፍን ዓለምን ተቆጣጥሮ እኛም ጋር ደርሷል።እንደ ብራዚላውያን እግር ኳስ በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የሚወደድበት ስፖርት ማግኝት ይከብዳል። የሳንቶስ ከተማም ለዚህ ምስክር ነች።
ለሳንቶሳውያን የእግር ኳስ ስፖርት ጨዋታ፣ መዝናኛ ብቻ አይደለም የህይወታቸው አንድ አካል ጭምር እንጂ ።ይህም በእግር ኳስ ስፖርት ለዓለም ህዝብ ደስታን የፈጠሩ ገጸ በረከቶችን አበርክተዋል።ታላቁ ፔሌ እና ኔይማር ጁኒየር ደግሞ ዓለም የማይዘነጋቸው ከሳንቶስ ጉያ የወጡ ምልክት የእግር ኳስ ተጫዋቾች ናቸው። እግር ኳስ ከሚዝወተርባቸው እና ባህል ከሆነባቸው የብራዚል ከተሞች መካክል ሳንቶስ አንዷ ናት።
የሳንቶስ ከተማ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ለብራዚል ዕድገት የጀርባ አጥንት እንደነበረች ያታሪክ መዝገብ ያስረዳል።ትንሿ ከተማ ሳንቶስ ፣ የወደብ ከተማ በመሆኗ ከፍተኛ የቡና እና የአሳ ምርት ለውጪ ገበያ በማቅረብ ትታወቃለች። የከተማዋ ሕዝብ ኑሮ ሲሻሻል ፣ በሀብት እና በኢኮኖሚ ሲበለጽግ ፣ ማህብረሰቡ ለስፖርት ያለው ፍላጎት እና ፍቅር እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች አመልክተዋል። የእግር ኳስ ስፖርት በከተማዋ ቀድም ብሎ ቢታወቅም ይህ ነው የሚባል የተቋቋመ ክለብ ግን አልነበረም።
ስፖርቱን ወዳድ የሆኑ ሦስት ግለሰቦችም 14 ስዓታት የፈጀ ውይይት እና ምክክር ካደረጉ በኋላ ሳንቶስ የሚባልን ክለብ ሊወልዱ ችለዋል። ይህ ክለብም አሁን ላይ የሚሊዮኖች ሆኗል። የሀገሪቱ አራት በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ይህንን ታሪካዊውን ክለብ ይደግፈዋል፡በሀገሪቱ 10 ሚሊዮን ደጋፊ ያለው ሲሆን በአራቱም የዓለም ማዕዘን ደግሞ ከ20 ሚሊዮን በላይ ደጋፊዎች እንዳሉት የክለቡ ድረ ገጽ መረጃ ያመለክታል። ነገር ግን ይህ ክለብ በ2022/23 የውድድር ዘመን በብራዚል ሴሪ ኤ ሊግ አስቸጋሪ የውድድር ዓመት አሳልፏል። በመጨረሻም ከ111 ዓመታት በኋላ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ወርዷል።
የታሪክ ተቀናቃኙ ፓልሜራስ 12ኛ ዋንጫውን ባነሳበት በመጨረሻው ዙር የሴሪ ኤ መርሐ ግብር ሳንቶስ በሜዳው በፎርታሌዛ ሁለት ለአንድ መሸነፉን ተከትሎ ወደ ሴሪ ቢ ወርዷል። በተለይ የመጨረሻዎቹን አምስት የሊግ ጨዋታዎች አለማሸነፉ ውድቀቱን አፋጥኖታል። 43 ነጥቦችን በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የውድድር ዓመቱን አጠናቋል።
ይህን መጥፎ ዜና መቀበል የተሳናቸው ሳንቶሳውያን ሜዳ ውስጥ ነውጥ ሲፈጥሩ ታይተዋል። ታላቁ ክለባቸው ወደ ታችኛው የሊግ እርከን መውረዱ ያበሳጫቸው ደጋፊዎች በክለቡ ተጫዋቾች ላይ ጥቃት ለማድረስ አዋክበዋቸዋል። በዚህ ምክንያት በስቴዲየሙ ውስጥ ትልቅ ነውጥ ተፈጥሮ እንደነበረ የብራዚል ጋዜጣ መረጃ ያመለክታል።
ጨዋታው እንዳለቀ ደጋፊዎች ሜዳውን በመውረር በተጫዋቾች ላይ ጉዳት ለማድረስ ሞክረዋል። ነገር ግን የከፋ ጉዳት ሳይደርስ የከተማዋ ፖሊስ ተጫዋቾችን እና የቡድን አባላቱን በሄሊኮፍተር ከሜዳ ይዘዋቸው ወጥተዋል። ክስተቱም የፊልም ትዕይንት ይመስል እንደነበር የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ጋዜጣው አስነብቧል። ይህ ሁሉ ግርግር ግን ክለባቸውን ከመውረድ አላተረፈውም።
ሳንቶስ በሁሉም መድረኮች ኃያልነቱ፣ አስፈሪ ሞገሱ ከተገፈፈ ሰባት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በ2016 እ.አ.አ በብራዚል የላይኛው የሊግ እርከን የሚፎካከሩበትን የኮምፒዮናቶ ፓውሊስታን ዋንጫ ካሳካ በኋላ ስኬት ርቆት እንደቆየ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ክለቡ የሴሪ ኤውን ዋንጫ ካነሳም 12 ዓመታት አልፈዋል፡፡
አሁን ላይ በብራዚል እግር ኳስ ታሪክ ኃያሎቹ ሳኦ ፖሎ እና ፍላሚንጎ ብቻ ናቸው ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ወርደው የማያውቁ። የዚህ ታሪክ ተጋሪ የነበረው ሳንቶስ ክለብ ግን ዘንድሮ ይህንን ታሪኩን ሰርዞታል፡፡ ሳንቶስ በተለይ እ.አ.አ በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ኃያል እና ስሙ የናኘ እንደነበር የታሪክ ማህደሩ ያሳያል። ስድስት የሴሪ ኤ ዋንጫን ጨምሮ 20 የተለያዩ የሀገር ውስጥ ዋንጫዎችን አሳክቷል።
ሁለት የኮፓሌበርታዶሬስ እና ሌሎችንም አህጉራዊ፣ ዓለማቀፋዊ ዋንጫዎችን አንስቷል። ይህ ሁሉ ታሪክ የማይዘነጋው ገድል የተፃፈው፣ ወርቃማ ትውልድ ብለው በሚጠሩት በትልቁ የእግር ኳሱ መሲህ ፔሌ ዘመን ነው። ክለቡ በአጠቃላይ ከ24 ዋንጫዎች በላይ ሲሰበስብ የብራዚል ሴሪ ኤ ን አምስት ጊዜ በተከታታይ በማሸነፍም ባለክብረ ወሰን ጭምር ነው። ጥር 20/ 1998 እ.አ.አ አስር ሺህ ግቦችን ከመረብ ያሳረፈ የመጀመሪያው ክለብ በመሆን በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ (ፊፋ) እውቅና ተሰጥቶታል። የ20ኛው ክፍለ ዘመን ስኬታማ ክለብ ነው በማለት ፊፋ ሽልማትም አበርክቶለታል።
ክለቡ በቅርብ የሚገኝ የከተማ ተቀናቃኝ የለውም። ከኮሪንቲያንስ ፣ ከፓልሜራስ እና ሳኦ ፖሎ ጋር የታሪክ ሽሚያ ውስጥም ይገኛል። ከእነዚህ ሦስቱ ክለቦች መካከል ግን ሳኦ ፖሎ ለሳንቶስ ከተማ ቅርብ መሆኗ ይነገራል። ከሳኦ ፖሎ ጋር ያለው ፉክክርም ጠንካራ እንደሆነ ይገለፃል። የሳንቶስ እና የሳኦ ፖሎ ፉክክር “ሳን ሳኦ” ደርቢ ተብሎ ይጠራል።
በብራዚል ውስጥ ከታላላቅ የደርቢ ፍጥጫዎች መካከልም አንዱ ነው።ሳንቶስ መልካም እግር ኳስ አቀንቃኝ ሲሆን በሀገሪቱ በማራኪ የእግር ኳስ አጨዋወቱ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ይታወቃል። ምስጋና ለወርቃማው ትውልድ ለነ ፔሌ ይግባና ከእነርሱ ዘመን የተወረሰ ስለመሆኑም ይነገራል። ምርጥ ከሚባሉ ጥቂት ክለቦች መካከልም አንዱ ለመሆን በቅቷል። ሳንቶስ ለዓለም እግር ኳስ ስፖርት ትልቅ ገጸ በረከት ናቸው የሚባሉትን ባለ ተሰጥኦ ተጫዋቾችንም አበርክቷል።
በብራዚል ምድር የላቀ ተሰጥኦ ያላቸውን ተጫዋቾችን በማምረትም ይታወቃል። የ20ኛው ክፍለ ዘመን ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋቹ ፔሌ በሳንቶስ ክለብ ተጫውቶ አሳልፏል። በወቅቱ በዚህ ሰኬታማ የእግር ኳስ ኮከብ ዘመን፣ ክለቡ ቀዳሚው የአህጉሩ ኃያል ክለብ መሆን ችሎ እንደነበር ታሪክ ያስታውሳል። በትውልዱ ካሉት የላቀ ተሰጥኦ ካላቸው ተጫዋቾች መካከል ኔይማር ጁኒየርም ከሳንቶስ የተገኘ ተጫዋች ነው። ያለውን እምቅ ችሎታ ሳይጠቀምበት በእግር ኳሱ ዓለም ድንገት ታይቶ የጠፋው ሮቢንሆ ፣ የአሁኑ የሪያል ማድሪዱ ተጫዋች ሮድሪጎ ፣ የቀድሞዎቹ ጆቫኒ ሲልቫ፣ ካርሎስ አልቤርቶን የመሳሰሉት ከብዙዎቹ በጥቂቱ ከሳንቶስ የተገኙ የእግር ኳስ ጠበብቶች ናቸው። ይህ ክለብ አሁን ጊዜ ከድቶት ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ወርዷል። ይህንን መጥፎ ዜና የሰሙት የቀድሞ ተጫዋቾቹ ከክለቡ ጎን መሆናቸውን በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው አስነብበዋል።
ይህን መጥፎ ዜና የሰማው በሳውዲ አረቢያ አል ሂላል የሚጫወተው ኔይማር ጁኒየር “ሳንቶስ ሁሌም ሳንቶስ ነው” በቅርቡ ወደ ላይኛው የሊግ እርከን ይመለሳል ሲል በቲውተር ገጹ አስፍሯል። የሪያል ማድሪዱ ኮከብ ሮድሪጎ ደግሞ የሳንቶስ መንፈስ የሚለቅ አይደለም። ምንም ይሁን ምን ሳንቶስ ከልቤ አይጠፋም ፣ ነፍሴ ሁሌም ከሳንቶስ ጋር ነች ሲል በቲውተር ገጹ የማጽናኛ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ዋን ፉትቦል፣ቢቢሲ ሰፖርት እና የሳንቶስ እግረ ኳስ ክለብ ድረ ገጽን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ታኀሣሥ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here