የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝነት ተስፋ እና ስጋቶች

0
190

ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ብቁ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኅይል ለማፍራት ትኩረት ሰጥታ እየሠራች  ስለመሆኑ መንግሥት ሲናገር ይደመጣል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ያሉ የጸጥታ መደፍረሶች ወቅታዊ ፈተና ሆነው ቢቀጥሉም ግን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል፣ የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ማድረግ እና የመምህራንን አቅም ማሳደግ እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች ተጠቃሾች ናቸው:: ከእነዚህ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል::

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ የሚያስችለው አዋጅም በ2015 ዓ.ም ግንቦት ወር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል:: አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ወደ ትግበራው የተሸጋገረ የመጀመሪያው ተቋም ለመሆን በቅቷል::

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት እና ሥነ ባህሪ ኮሌጅ የትምህርት ዕቅድ እና ሥራ አመራር ትምህርት መምህር እና ተመራማሪ እንዲሁም የጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አበባው ይርጋ ከዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆታ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባሰቡት ልክ  ውጤታማ ሆነው እንዳይቀጥሉ ካደረጓቸው ምክንያቶች መካከል ራስ ገዝ አለመሆናቸውን በቀዳሚነት ያነሳሉ። ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሲሆኑ ከመንግሥት ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ እንዲወጡ በማድረግ ተቋማቱ ሳይንሳዊ በሆነ እና ውጤታማ በሚያደርጋቸው መንገድ እንዲሠሩ ነጻነትን እንደሚሰጣቸው ፕሮፌሰሩ ይጠቅሳሉ።

ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ራስ ገዝ እንዲሸጋገሩ የሚደረገው በዋናነት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ነው:: ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሲሆኑ ተማሪዎችን በመግቢያ ፈተና ብቻ ይቀበላሉ:: ይህም የተሻለ አቅም ያላቸው እና ተወዳዳሪ  ተማሪዎች ብቻ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ የሚያስችል ነው:: ይህ ሲሆን ደግሞ  ተማሪዎች እና ወላጆች ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ለትምህርት ጥራት ትኩረት እንዲሰጡ ያደርጋቸዋል::

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በድረ ገጹ ያሰፈረው ጽሑፍ እንደሚያስረዳው ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆናቸው ጥራት ያለው ትምህር እና ሥልጠና ለመስጠት፣ ያለን ሀብት ያለብክነት በጥንቃቄ ለመጠቀም፣ ተመራጭ እና ተወዳዳሪ የትምህርት ፕሮግራሞችን ለመቅረጽ እና ለመተግበር ሰፊ ዕድልን ይሰጣል:: በእርግጥ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ለመሆን ጠንካራ የሰው ኀይል፣ የፋይናንስ አቅም እና የተሟላ መሰረተ ልማት ሊያሟሉ ይገባል::

ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ በሚሆኑበት ወቅት አሁን ያላቸውን መዋቅር በራሳቸው መከለስ፣ መቀየር እና ለማማሻሻልም ዕድል ያገኛሉ:: ዩኒቨርሲቲውን የሚመሩ አካላትን እስከ መሰየም የሚደርስ ሥልጣንም ያገኛሉ::

ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎችን ያለ መንግሥት ምደባ በራሳቸው የመግቢያ ፈተና የመቀበል፣ የራሳቸውን ሠራተኞች የመቅጠር እና የማሰናበት፣ ግዢን ጨምሮ የራሳቸውን የገንዘብ /ፋይናንስ/ እንቅስቃሴ መምራት እንዲችሉም ያደርጋቸዋል::

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የራሳቸውን የአስተዳደር መዋቅር፣ የሰው ኀይል ምደባ፣ ቅጥር እና ደመወዝ የሲቪል ሰርቪስ ሕግን መከተል ሳይጠበቅባቸው ለራሳቸው በሚመች መልኩ እንዲያዘጋጁ አስተዳደራዊ ነጻነት እና ሥልጣን ይሰጣቸዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ተፈላጊነታቸውን እና ተመራጭነታቸውን በመመዘን በየትምህርት ክፍሎች የሚኖሩ  ተማሪዎችን ቁጥር የመወሰን፣ የትምህርት ፕሮግራሞችን ያለማንም ይሁንታ እና ጣልቃገብነት የመቅረጽ መብት እና ሥልጣን እንዲኖራቸው በማድረግ ለትምህርት እና ሥልጠና ጥራት መረጋገጥ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱም ያደርጋቸዋል::

አዋጁ ዩኒቨርሲቲዎች በሚኖራቸው የፋይናንስ ነጻነትም የራስን ገቢ ማመንጨት እና መጠቀም እንዲችሉ ያበረታታል:: በዚህም ተቋሙ  ዓላማውን ለማሳካት በተለያዩ የገቢ ማመንጫ ዘርፎች ላይ በመሰማራት እና ገቢን በማመንጨት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመንግሥት ጥገኝነት እንዲላቀቁ ያደርጋቸዋል::

ይሁን እንጂ የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝነት ከመንግሥት በጀት የሚያስወጣቸው መሆኑን፣ ይህንንም በጀት ለማግኘት መክፈል የሚችሉ ተማሪዎችን ብቻ መመልመል እና መቀበል ላይ እንዲያተኩሩ የሚያበረታታ በመሆኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ትምህርት ውጪ እንዲሆኑ ሊያደርጋቸው ይችላል የሚሉ ወገኖች ስጋታቸውን ሲናገሩ እየተደመጡ ነው::

ፕሮፌሰር አበባው “እነዚህ ሐሳቦች እየተሰነዘሩ ያሉት የራስ ገዝነት ባህሪን በአግባቡ ካለመረዳት እንደሆነ አብራርተዋል:: “ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ማለት የመክፈል አቅም ያላቸው ብቻ የሚማሩበት ማለት አይደለም:: መክፈል ለማይችሉ ተማሪዎች የወጪ መጋራትን ጨምሮ ነጻ የትምህርት ዕድል እና ሌሎች የመፍትሄ አማራጮች በዩኒቨርሲቲዎች እና በመንግሥት በኩል ይተገበራሉ::  ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ  ስለሆኑ ብቻ ራሳቸውን ከመንግሥት ነጥለው ሊያዩ እንደማይገባ እና መንግሥት ለዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጣቸው ድጎማም ሙሉ ለሙሉ አይቀርም” ሲሉ አስገንዝበዋል::

ፕሮፌሰሩ የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን ሌላው ስጋት ኢትዮጵያዊ ብዝኃነትን እንዳያመነምነው ነው:: ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተጠሪነታቸው ለፌደራል መንግሥቱ (ትምህርት ሚኒስቴር) ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ከባለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ሀገሪቱ እያጋጠማት ያለውን የሰላም መደፍረስ ተከትሎ ተቋማቱ ተጠሪነታቸውን በክልሎች የተነጠቁ ያህል እንደተሰማቸው ያምናሉ:: ለዚህ ማሳያቸው ተቋማቱ ከተሰጣቸው ኃላፊነት በማፈንገጥ እና ተጠሪነታቸውን በመዘንጋት የክልላቸውን ፖለቲካ ለማስፈጸም ሲሯሯጡ መታየታቸው ነው።

እንደ ፕሮፌሰር አበባ? ዩኒቨርሲቲዎች ኤምባሲ መሆን አለባቸው:: ኤምባሲዎች በየትኛውም ሀገር ቢቀመጡም የሚያገለግሉት የወከሉትን ሀገር እንጂ የተቀመጡበትን ሀገር አይደለም። የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችም ከየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ ቢገኙም ከክልል መንግሥታት ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው ሀገር የመገንባት ተልዕኳቸውን ሊወጡ ይገባል” ባይ ናቸው::

ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆናቸው ከሚሰጣቸው ዕድሎች መካከል አንዱ የራሳቸውን ተማሪዎች በራሳቸው መመልመል እና መቀበል ነው። በሀገሪቱ ውስጥ የብሄር ልዩነት እየሰፋ በመጣበት በዚህ ወቅት የትኛው ተማሪ ወዶ እና ፈቅዶ ሌላ ክልል ካለ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ትምህርቱን ይከታተላል? የሚለው የፕሮፌሰሩ ዋነኛ ስጋት ነው::  “ዩኒቨርሲቲዎች የኢትዮጵያ ብዝኃነት ማዕከል ናቸው” የሚሉት ፕሮፌሰር አበባው፣ ሀገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ  ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንዲሆኑ ማድረግ እየሳሳ የመጣውን ብዝኃነት እንዳይበጥሰው ስጋት ፈጥሮባቸዋል::

ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎቿን ራስ ገዝ እንዲሆኑ የሚያደርግ አዋጅ ስታጸድቅ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለው ልምድ እና አንጋፋነት  ቀዳሚው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ወደ ትግበራ ገብቷል። በሂደት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ በሀገሪቱ የመጀመሪያ ትውልድ ተብለው የሚጠሩ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ራስ ገዝነት ይሸጋገራሉ:: ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በትግበራ ውስጥ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጠበቀው እና በታመነው ልክ ሳይሆን ቢቀር ውድቀቱ ሀገርን እና ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጭምር ሊሆን ስለሚችል  ስጋት አድርገው አንስተዋል::

ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ራስ ገዝነት መሸጋገራቸው ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የሚያበረክቱት ፋይዳ ከፍተኛ ነው:: በመሆኑም በሀገሪቱ የቀጠሉ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የዩኒቨርሲቲዎችን  የብዝኃነት ማዕከል ማስቀጠል ይገባል:: ዩኒቨርሲቲዎችም ከየትኛውም የፖለቲካ አቋም ነጻ ሆነው ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ እና ብቁ ትውልድ ማፍራት ላይ ሊያተኩሩ ይገባል:: ተማሪዎችም ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ሲሄዱ ኢትዮጵያዊ መንፈስን ተላብሰው ሊሆን ይገባል::  ቀድመው ወደ ትግበራ የገቡትን ዩኒቨርሲቲዎች መደገፍም ተገቢ ነው:: ይህም በቀጣይ ራስ ገዝ የሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ከቀደሙት ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ልምድ እና ትምህርት ወስደው ውጤታማ ሆነው እንዲጓዙ ያደርጋቸዋል::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here