የደረሰኝ ጠቀሜታ

0
219

ደረሰኝ ሰዎች ግብይት ወይም አገልግሎት ሲፈጽሙ  ሻጩ /አቅራቢው/ ለገዥው የሚሰጠው እንዲሁም  ነጋዴው ግብይት ስለመፈጸሙ፣ ገንዘብ ስለመሰብሰቡ፣ ዋጋ ስለመከፈሉ እና ወደ ፊት ለመክፈል ኃላፊነት የተወሰደ ስለመሆኑ የሚያሳይ ማረጋገጫ  ሰነድ ነው:: በኵር ጋዜጣ በዚህ ሳምንት እትሟ  ስለ ደረሰኝ ምንነት እና ደረሰኝ መጠቀም ያለውን አስፈላጊነት በተመለከተ በገቢዎች ሚኒሥቴር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከታክስ ከፋዮች ትምህርት እና መረጃ አቅርቦት ቡድን አስተባባሪ ከአቶ ፀጋዬ ቢተው ጋር ቆይታ አድርጋለች::

እንደ አስተባባሪው ማብራሪያ ደረሰኝ በተለያዩ አካላት መካከል የሚፈጸመውን ግብይት ግልጽ እና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን በማድረግ በሂሳብ አያያዝ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ ነው::  በተለይ እንደ ሀገራችን ባሉ የዕቃ እና አገልግሎት ግብይት በስፋት በጥሬ ገንዘብ በሚያከናውን ኢኮኖሚ ውስጥ በተለያዩ የገንዘብ ተቋማት አማካይነት የሚተላለፉ ገንዘብ ነክ ሰነዶች በዋናነት የወረቀት ሕትመቶች ስለሆኑ በሻጭ እና ገዥ መካከል ስለሚፈጸመው ግብይት ተአማኒነት ዋነኛው ማረጋገጫ በመሆን ያገለግላል::

በደረሰኝ አጠቃቀም ላይ ዋና ተዋናዮች የሚባሉት  ዕቃ ሻጭ ወይም አገልግሎት አቅራቢ/የንግድ እንቅስቃሴ የሚያካሂድ ሰው፣ ዕቃ ገዥ ወይም አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኛ፣  መንግሥት/ ግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች መሆናቸውን አስተባባሪው ተናግረዋል::

አቶ ፀጋዬ እንደገለጹት ለእቃ ገዥ እና ለአገልግሎት የሚሠጡ የደረሰኝ አይነቶች  ሦስት ናቸው:: እነዚህም በእጅ የሚቆረጥ /ማንዋል/፣ የሽያጭ መሣሪያን በመጠቀም የሚወጣ ደረሰኝ እና በመንግሥት የተመዘገበ ኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ ናቸው::  ደረሰኞቹ የተጨማሪ እሴት ታክስ ወይም  ተርን ኦቨር ታክስ ያለባቸው እንዲሁም ከታክስ እና ተርን ኦቨር ታክስ ነፃ የሆኑ ደረሰኞች ሊሆኑ ይችላሉ::

ደረሰኞች ያላቸው ጠቀሜታ ሰፊ ነው ያሉት  አቶ ፀጋዬ፤  ደረሰኝ መጠቀም ያለባቸው የታክስ ሒሳብ ደብተር መጠቀም ያለባቸው ነጋዴዎች ናቸው:: በሕግ የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ የተጣለባቸው የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች በሙሉ ደረሰኝ አሳትመው የመጠቀም ግዴታ እንዳለባቸው የገቢ ግብር አዋጅ ይደነግጋል:: ከዚህ በተጨማሪ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ምንም እንኳን የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ሕጋዊ ግዴታ ባይጣልባቸውም በራሳቸው ተነሳሽነት የሂሳብ መዝገብ ለመያዝ ፍላጎት ካላቸው የሕጉን አግባብ ተከትለው ደረሰኝ ማሳተም እንዳለባቸው ተቀምጧል::

ግብር ከፋዮች በሕግ በተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ መሰረት ከንግድ ሥራቸው ጋር አግባብነት ያላቸው ደረሰኞች ከባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በሚሰጣቸው ፈቃድ አሳትመው መጠቀም እንደ ሚገባቸው አስተባባሪው አስረድተዋል:: ማንኛውንም ግብይትም ያለደረሰኝ ማከናወን አይፈቀድላቸውም::

የሚከናወኑት ግብይቶች እንደ ደረጃቸው የተጨማሪ እሴት ታክስ ወይም የተርን ኦቨር ታክስ የሚያካትት በሚሆንበት ጊዜ የሽያጭ ደረሰኞች መጠቀም እንደሚገባቸውም አስተባባሪው ሕጉን መሰረት አድርገው አስገንዝበዋል::

እቃ የገዛ  ወይም የአገልግሎት ተጠቃሚ የሆነ ግለሰብ  ደረሰኝ በመቀበሉ  ለገዛው እቃ ወይም አገልግሎት በማረጋገጫነት ያገለግለዋል:: በትክክል ግብይቱን በደረሰኝ በመፈፀሙ እና በፈፀመው ግብይት ታክስ በትክክል ለመንግሥት እየከፈለ ነው ለማለት ያስችላል:: /ታክስ ለመንግስት ገቢ መሆኑን የሚያረጋግጥበት መንገድ ነው/፣ በንግዱ ማህበረሰብ በገዥ እና በሻጭ መካከል ትልቅ መተማመንን ይፈጥራል:: ከነዚህ በተጨማሪ በነጋዴች መካከል ፍትሐዊ  የገበያ ውድድር ለመፍጠር ያስችላል::

ለግብር ከፋዩ ደግሞ ደረሰኝ መስጠት ዘመናዊ የሒሳብ አያያዝን ለማዘመን ይጠቅመዋል እንዲሁም  በድርጅቶች እና ሽያጭ ሠራተኞች መካከል መተማመን ይፈጥራል፤ ይህ ሲባል የሚገባው እና የሚሸጠው እቃ በደረሰኝ ስለሆነ በቀላሉ ለመቆጣጠር ያስችላል::

እንደ አስተባባሪው መረጃ ደረሰኝ በግብር ከፋይ እና በገቢ ሰብሳቢው ቢሮ መካከል ያለውን ትልቅ መተማመንንም ይፈጥራል:: አጠቃላይ በየዕለቱ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማወቅም ያስችላል:: በመንግሥት በኩል ደግሞ ፍትሐዊ እና በመረጃ የተደገፈ ግብር ለመወሰን፣ ሕገ ወጥነትን ለመከላከል፣ በግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቱ እና በነጋዴው መካከል ያለውን መተማመን ይጨምራል:: እንዲሁም በኢኮኖሚ የሚመነጨውን ገቢ ወደ ልማት ለመቀየር ያስችላል::

ከዚህ አንፃር ደረሰኝ ለመቀበል  የመጠየቅ ባሕልን  የንግዱ ማህበረሰብ፣ ሻጩ እና ገዢውም ሊያዳብሩ እንደሚገባ አስተባባሪው አስገንዝበዋል::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የመጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here