የደርግ ቱርፋቶች

0
19

በዐፄ ዳግማዊ ቴዎድሮስ የጀመረው የዘመናዊት ኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታን ተከትለው ሀገሪቱን በመሩት መንግሥታት የተለያዩ አሻራዎች አርፎበታል። ሁሉም የሚኮነንበት ጎን እንዳላቸው ሁሉ ዘመን ተሻጋሪ ተወዳሽ ስራዎችንም ትተው አልፈዋል። ታሪክ የትናንቱን ለዛሬው መማሪያ እንዲሆን፣ እና  የበለጠ እንዲበረታ የደርግ ዘመነ መንግሥትን ስኬታማ ስራዎች ለማሳየት ወደድን።

“አብዮት ፈነዳ በስልሳ ስድስት

ጭቁኖች ተባብረው የታገሉለት…!”

እየተባለ በየትምህርት ቤቱ የተዘመረለት አብዮት በ1966 ዓ.ም  ተቀስቅሶ በዓመቱ የትግሉ ውጤት  እውን ሆነ፤ ወታደራዊው ደርግ  መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም የዐፄ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት  ገርስሶ ስልጣን ያዘ። የዘውዳዊውን ስርዓት ምክር ቤት አፈረሰ፣ ሕገ-መንግሥቱንም አገደ።

ከ1966 ዓ.ም እስከ 1969 ዓ.ም ያሉት ዓመታት ደርግ ፋታ በማይሰጥ ስልጣን የማደላደል ትግል ውስጥ የነበረበት ነው። መጀመሪያ ላይ ደርግ ራሱን እንደ የሽግግር መንግሥት  አድርጎ በማቅረብ ለውጦችን እና ሀገሪቱን ወደ መረጋጋት እንደሚመልስ ቃል ይገባ ነበር። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ስልጣኑን ወደ ማደላደል ገባ። ደርግ  ስልጣኑን ለማደላደል የወሰዳቸው እርምጃዎች ለጊዜውም ቢሆን የተሳኩ መሰለ። ነገር ግን አያሌ ኢትዮጵያውያን ከባድ ዋጋ ከፈሉ። እናም ደርግ ዋነኛ የስልጣኑ ተቀናቃኝ የነበሩትን ኃይሎች በኃይል ካስወገደ በኋላ የደርግ ሊቀመንበሩ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ያለተገዳዳሪ የሀገሪቱ መሪ ሆነው ተሰየሙ፣ ፓርቲያቸው ደርግ ብቸኛ አራጊ ፈጣሪ የመንግሥት ገዢ ፓርቲ ሆነ። በማርክሲስት ሌኒኒስት ርእዮት “ሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ” መመስረቷ ታወጀ።  ከዚህ በኋላም ነበር ደርግ ኢትዮጵያ ለዓመታት ስትሰቃይባቸው በነበሩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ስር ነቀል ለውጥ መተግበር እንደጀመረ ሜክሲኮ ሂስቶሪኮ ዶት ኮም ያስረዳል።

ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች

የኢትዮጵያ አብዮት በሀገሪቱ ለአስርት አመታት ሲታወሱ የነበሩትን ስር የሰደዱ ኢ-ፍትሃዊ ልዩነቶችን እና ጉዳዮችን ለመፍታት ተከታታይ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን አድርጓል። በደርግ የተዘረጋው የመሬት ማሻሻያ ፖሊሲ የፊውዳል የመሬት ባለቤትነትን አስወግዶ መሬትን ለገበሬዎች መልሶ ማከፋፈል ከለውጦቹ አንዱና ዋነኛው ነው። ከአብዮቱ በፊት መሬት በብዛት የተያዘው በጥቃቅን ከበርቴዎች በመሆኑ በገጠሩ ህዝብ ዘንድ ሰፊ ድህነት እና የመብት እጦት አስከትሎ ነበር።

በተጨማሪም ደርግ የልማት ስትራቴጂው ወሳኝ አካል አድርጎ በትምህርትና በጤና አጠባበቅ ላይ አተኩሯል። ህዝቡን ለማስተማር እና አብዮታዊ ሀሳቦችን ለማራመድ ያለመ የማንበብ ዘመቻዎችንም ጀምሮ ነበር። ከማርክሲዝም-ሌኒኒዝም መርሆዎች ጋር የተጣጣመ አዲስ የሶሻሊስት ዜጋ ለመፍጠር ይፈልግም ነበር።

መሬት ለአራሹ

የደርግ ትልቅ ትርጉም ያለው ፖሊሲ መጋቢት 1967 ዓ.ም የወጣው የመሬት ማሻሻያ አዋጅ ነው።ይህ ማሻሻያ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ስር የሰደዱ የፊውዳል የመሬት ባለቤትነት ስርዓቶችን ለማፍረስ ያለመ ነበር። ደርግ በሀገሪቱ ለዘመናት ሲታመስ የነበረውን ጥልቅ ማህበራዊ ኢ-ፍትሃዊነትን ለመፍታት የመሬት ማሻሻያ ማድረግ ወሳኝ እርምጃ አድርጎ ይመለከተው ነበር። አዋጁ የግል የመሬት ባለቤትነትን በመሰረዝ ሁሉንም መሬቶች ወደ መንግሥት በማዛወር ለገበሬው ለማከፋፈል የታቀደ ነበር።

የሀገሪቱ የመሬት ስሬት የተዛባ እና በጥቂት የመሬት ከበርቴዎች እጅ የወደቀ ስለነበር አራሹን ገበሬ መሬት አልባ አድርጎ ያስቀረ ብቻ ሳይሆን ጉልበቱንም የበዘበዘ ነበር። ጭቁኑ ገበሬ መሬት ከመሬት ከበርቴው ተከራይቶ ካመረተ በኋላ ያመረተውን ምርት 70 በመቶውን ለመሬቱ ባለቤት ሰጥቶ የተቀረውን 30 በመቶ ምርት ብቻ ነበር ወደ ጎተራው የሚያስገባው። ይህን በመቃወም በንጉሡ ዘመን ተቀስቅሶ የነበረው የተማሪዎች ንቅናቄ አንዱ የትግል ጉዳይ በመሆን “መሬት ለአራሹ” መፈክር መስተጋባት ጀመረ። መጋቢት 4 ቀን 1957 ዓ.ም ላይ አደባባይ ወጥቶ በተማሪዎች ተስተጋባ። ነገር ግን ሰሚ ሳያገኝ ለአስር ዓመታት ያህል ዘልቋል። ምላሽ ያገኘው በደርግ ዘመን ነበር። ደርግ መሬት ለአራሹን በማወጅ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ስር ነቀል ለውጥ ጀመረ።

ለዚህ ሥር ነቀል ለውጥ መንግሥት የሰጠው ምክንያት በማርክሲስት ርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሠረተ ሲሆን ይህም የፊውዳል መሬት አወቃቀር ለድህነት እና ለማህበራዊ ኢፍትሃዊነት ቀዳሚ መንስኤ መሆኑን በማሳየት ነው። መሬት መከፋፈል የነበረበት መሬት የሌላቸውን ገበሬዎች ፣ የጋራ እርሻን እና የኅብረት ሥራ ማህበራትን በማስተዋወቅ ላይ ባለው ሥርዓት መሠረት ነው። በሌላ በኩል  የግብርና ተሃድሶው ብዙ ፈጣን ውጤቶች ነበሩት። መጀመሪያ ላይ ብዙ ገበሬዎች ለመጀመሪያ ጊዜ መሬት ስለተቀበሉ በገጠሩ ህዝብ መካከል የጋለ ስሜት ጨምሮ ነበር።

በ1967 ዓ.ም የወጣው የደርግ የመሬት ማሻሻያ ፖሊሲ መሬትን ከትላልቅ ባለቤቶች መንጠቅ እና ለገበሬዎች መከፋፈልን ያካተተ ነበር። ይህ ፖሊሲ የገጠሩን ህዝብ ለማብቃት፣ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እና የፊውዳል ስርአትን ለማስወገድ ያለመ ነው። የመሬት ማሻሻያው በአንዳንድ አካባቢዎች የግብርና ምርትን ቢያሳድግም በኢንቨስትመንት እጥረት፣ በመሠረተ ልማት ደካማነት እና ለአርሶ አደሩ በቂ ድጋፍ ባለመኖሩ አጠቃላይ ምርታማነት እንዲቀንስ ሆኗል።

ትምህርት ለሁሉም

ደርግ የትምህርትና የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል ያለመ መርሃ ግብሮችንም ጀምሮ ነበር። የማንበብ ዘመቻዎች መመስረት እና የትምህርት ቤቶች መስፋፋት በተለይም በገጠር ያለውን የተንሰራፋ መሃይምነት ለመፍታት ያለመ ነው።

አብዮቱን ተከትሎ የተፈጠረው የርእዮተ ዓለማዊ እና ፖለቲካዊ አዲስ አሰላለፍ በሀገሪቱ የትምህርት ስርአት ላይ ሶሺያሊስታዊ ቃና የያዘ ስር ነቀል ለውጥ አምጥቷል። ዋነኛ የትምህርት ፖሊሲው አላማ የአገዛዙን የማርክሲስት ሌኒኒታዊ አስተሳሰብ ማስረፅ እና አዲስ ሕብረተሰባዊ ዜጋ መፍጠር ነው። ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ ያሉ ተማሪዎች የማርክሲስት ሌኒኒስታዊ አስተሳሰብን በሁሉም ደረጃ እንዲማሩት ይደረግ ነበር። ትምህርትን የልማት ዋነኛ መሳሪያ አድርጎ ትልቅ ትኩረት የሰጠው የደርግ መንግሥት፣ ማርክሲስት ሌኒኒስታዊ አስተሳሰብን እና የምርታማነትን እሴትን የትምህርት ዋነኛ ምሰሶዎች አድርጎ ነበር። በመሆኑም በ1968 ዓ.ም በወጣው የብሄራዊ አዋጅ ላይ ነፃ ትምህርት ለሰፊው ሕዝብ የማቅረብ አዋጅ አወጀ። ይህም በፊውዳሊዝም፣ በኢምፔሪያሊዝም እና በቢሮክራቲክ ካፒታሊዝም ላይ የተጀመረውን ትግል ያቀጣጥለዋል የሚል አላማ ነበረው። ይህ አዋጅ መሀይምነትን ለማስወገድ ሁሉንም አይነት እርምጃዎች ለመውሰድ፣ የሳይንስን፣  የቴክኖሎጂ፣ የኪነ ጥበብ እና የስነ ፅሁፍ እድገትን ለማበረታታት፣ እንዲሁም ዘርፈ ብዙውን የኢትዮጵያ ባህል ከኢምፔሪያሊስቱ የባህል ወረራ ነፃ ለማውጣት ሁሉም አይነት አስፈላጊ እርምጃዎች እንደሚወስድ ቃል ገብቷል።

ደርግ ትምህርትን የአብዮቱ አንዱ እና ዋነኛ የልማት ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ መሳሪያ አድርጎ ወሰደ።  በመሆኑም ሁሉንም ማህበረሰብ በየደረጃው የማስተማር ልዩ የመሰረታዊ ትምህርት ፕሮግራምን በመተግበር የመሀይምነትን ደረጃ ለመቀነስ ልዩ ዘመቻ አውጆ ነበር። የተማሩ ተማሪዎች ሳይማር ያስተማራቸውን ወገናቸውን እንዲያስተምሩ ግድ የሚል ዘመቻ ላሉት ዓመታት የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ተዘግቶ እንዲከናወን መደረጉ ደርግ ከሚወደስባቸው ስኬቶቹ አንዱ ነበር።

ሁሉም አስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ የወሰዱ ተማሪዎች ቢያንስ ለሶስት ወራት የዚህኑ ዘመቻ ተሳታፊ መሆንን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ አንዱ መስፈርት አድርጎ ወስዶት ነበር። እናም ሁሉም ተማሪዎች ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ተሰማርተው ወገናቸውን እንዲያግዙ ሆነዋል። በእግረ  መንገዳቸውም ማህበራዊ አንድነታቸውን  አጠንክረውበታል። ደርግ ለወሰደው እንዲህ አይነቱ ስር ነቀል ዜጎችን የማስተማር እንቅስቃሴ በ1972 ዓ.ም የዩኔስኮ የትምህርት ተሸላሚ ለመሆን አብቅቶታል። ፡፡

 

ሳምንቱ በታሪክ

ጃንሆይ በለንደን

ጥቅምት 4 ቀን 1947 ዓ.ም – የብሪታኒያዋ ንግሥት ዳግማዊት ኤልሳቤጥ ለሁለት ሣምንት ጉብኝት ወደ እንግሊዝ  የቀኑትን  ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን በለንደን ቪክቶርያ የባቡር ጣቢያ ተቀበሉ።

ሙዋሊሚ

ጥቅምት 4 ቀን 1992 ዓ.ም. – በምሥራቅ አፍሪቃ የታንዛኒያ መሪ የነበሩት፤ በወገኖቻቸው አቆላማጭ ጥሪ ሙዋሊሙ (አስተማሪ) በመባል የሚታወቁት ጁልየስ ካምባራጌ ኔሬሬ በለንደን ሆስፒታል በሉኪሚያ በሽታ ምክንያት አረፉ። እኒህ ታላቅ አፍሪቃዊ መሪ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትን ከመሠረቱት አንዱ ሲሆኑ፤ በአህጉሩ የመጀመሪያው በፈቃዳቸው የፕሬዚዳንትነት ስልጣናቸውን የለቀቁ ናቸው።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here