ከያኒ ደሳለኝ መኩሪያ
በአገውኛ ቋንቋ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠራው አንታጉ ፊልም ዳይሬክተር እና ተዋናይ ነው፡፡ ፊልሙ የአገውኛ ቋንቋን እና ባህልን ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ ፊልሙን ለመሥራትም ከአንድ ዓመት በላይ ወስዷል፡፡ በተለያዩ ቲያትሮች እና ፊልሞችም በዋና እና ደጋፊ ተዋናይነት ሠርቷል፡፡ ለአብነት የመጨረሻው መንገደኛ እና አራት ዐይና ይጠቀሳሉ፡፡ በሙሉ ዓለም የባሕል ማዕከል በቲያትረኛነት ለረጅም ዓመት ሠርቷል፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ፖሊስ ኪነት ተቀላቅሏል፤ ከያኒ ደሳለኝ መኩሪያ፡፡ ከከያኒ ደሳለኝ ጋር የቲያትር ጥበብን እንዲሁም ተዛማጅ ጉዳዮችን በተመለከተ ሀሳቡን አጋርቶናል፡፡
መልካም ንባብ!
ከቲያትር የሚያስቸግረው ምንድን ነው?
ቲያትር ላይ ብዙ ጊዜ የሚያስቸግረኝ የስም እና የቦታ መርሳት ነው፡፡ ዳይሬክተሬ አባይ በለጠ ብዙ ጊዜ “እረ ተው አንተ” ይለኛል፡፡ የራሴን ገጸ ባህሪ ስም ልጠራ ሁሉ እችላለሁ፡፡ ለምሳሌ “የመጨረሻው መንገደኛ” የሚባል ቲያትር ላይ የኔ ገጸ ባህሪ ስሙ ማርቆስ ነው፤ ዋናውን ገጸ ባህሪ ማርቆስ ብየ ጠራሁት፤ የእኛ ክፍል አልቆ ከመድረክ ጀርባ ስንገባ “ምን ሆነህ ነው? በራስህ ገጸ ባህሪ ስም ስትጠራኝ እኮ ነው የነበረው” አለኝ፡፡ ይሄ አልፎ አልፎ አሁንም ድረስ ያጋጥመኛል፡፡ መሰል ነገሮች ሲያጋጥሙህ በራስህ ፈጠራ መጠገን እና በስልት ወደ ዋናው ሁኔታ መመለስ ብቃትህን ይጠይቃል፡፡
አንድ ጊዜ እየተወንን አብሮኝ ሲሠራ የነበረው ተዋናይ ያለ ጊዜው መድረኩን ጥሎ ወጣ፡፡ የእሱ የትወና ክፍል ያለቀ ነው የመሰለው፤ “እረ ብላታ ና ተመለስ!” እያልኩ በስልት ብጠራው እንኳ ሊገባው አልቻለም፡፡ በኋላ ሌላኛው ተዋናይ ነገሩ ስለገባው ለሽፋን ወደ መድረክ መጣ፡፡ የተወሰነ ነገር በራሳችን ፈጥረን መለዋወጥ ጀመርን፡፡ መድረኩን ጥሎ የወጣው ተዋናይ ድረሻውን ጨርሶ አለመውጣቱ ሲገባው ደንግጦ ተመልሶ ወደ መድረክ ገባ፤ ሌላ ስህተት ሠራ፡፡
ቲያትርን ከሌሎች ትወናዎች የሚያከብደው ምንድን ነው?
ቲያትርን ከሌሎች ትወናዎች ከባድ የሚያደርገው የራስህን ድርሻ መወጣት ብቻ ሳይሆን አብረው የሚሠሩትን ሰዎች ሁሉ መከታተል፣ መጠበቅ፣ ማረም እና ጉድለት መሸፈን የሚጠብቁህ በመሆኑ ነው፡፡ በመድረኩ ራሱን ስቶ የሚወድቅ ሰው ሊኖር ሁሉ ይችላል፤ ሳትደናገጥ የሚገባውን ነገር ማድረግ አለብህ፡፡ እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ መከፈል ያለበትን ዋጋ ከፍለህ በስኬት ማጠናቀቅ አለብህ፡፡
ስለ አራት ዐይና ቲያትር ንገረን?
አራት ዐይና ቲያትር ግዙፍ ሀሳብ ይዞ የተነሳ እውነትም እንደ አራት ዐይናው አለቃ ገብረ ሀና የገዘፈ ሥራ ነው፡፡ የእሳቸው አራተኛ ትውልዶች ተገኝተው ምሁራን ሙያዊ አስተያየት ሰጥተውበት የተሠራ ቲያትር ነው፡፡ በብሔራዊ እና ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤቶች ጭምር የታየ ነው፡፡ ሊደበዝዝ የማይችል ትልቅ ታሪክ ይዞ የመጣ ቲያትር ነው፡፡ በቲያትሩ ላይ የአለቃ ገብረ ሀና ተጻራሪ የሆነውን ደብተራ ይሄይስን ሆኜ ነው የተጫወትኩት፡፡ የአለቃ ገብረ ሀናን ወንበር ለመንጠቅ የሚደረግን ትንቅንቅ የሚያሳይ ነው፤ ነገር ግን አለቃ ገብረ ሀና ደግሞ እጅግ ከፍ ያሉ እና የማይረቱ ብርቱ ሰው ናቸው፡፡ አራት ዐይና የተባሉት ምድር ላይ ያለውን እውቀት ተገንዝበው ስለጨረሱ ነው፡፡ አብዛኛው ሰው የሚያውቃቸው በቀልድ እና በቧልት ነው፡፡ ደብተራ ይሄይስ አላዋቂ ሆነው የአለቃ ገብረ ሀናን ቦታ ለመያዝ የሚጣጣሩ እጅግ የሚንጨረጨሩ ሰው ነበሩ፡፡ በመጨረሻም አንግዲህ እውነት ታሸንፋለች፡፡
ሥራው የሙሉ ዓለም የባህል ማዕከል ነው፤ ደራሲዎቹ ንብረት ያለው እና ደሳለኝ ድረስ ናቸው፡፡ ቦታው ድረስ በመሄድ በጥናት የተሠራ ቲያትር ነው፡፡ ለእኔ የደብተራ ይሄይስን ገጸ ባህሪ ደራሲዎቹ ሰጡኝ፡፡ ወደ መድረክ ከመውጣቱ በፊት የአለቃ ገብረ ሀና ገጸ ባህሪን ለማግኘት ፈተና ሆኖ ነበር፡፡ ገጸ ባህሪውን የሚወክል ሰው ማግኘት ከባድ ሆኖ ነበር፡፡ ሦስት ሰው ከተሞከረ በኋላ በአራተኛው መላኩ ተገኘ፡፡ እሱ ጥሩ አድርጎ ተጫወተው፡፡ ቲያትሩ የእውነት ነው የሚመስለኝ፤ ወደ ቤቴ ስሄድ ስሜቱ አብሮኝ ስለሚከተል ደክሞኝ ነበር የምገባው፡፡
በሙሉ ዓለም የባህል ማዕከል የሚሠሩ ቲያትሮችን እንዴት ታያቸዋለህ?
የሙሉ ዓለም የባህል ማዕከል የሚሠራቸው ቲያትሮች በአብዛኛው በጥናት ላይ የተደገፉ ናቸው፡፡ ጥናቱ ዓመት ወይም ሁለት ዓመት ሊፈጅ ይችላል፡፡ ወደ ጽሑፍ ለመቀየር ደግሞ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ሊፈጅ ይችላል፡፡ ከዛ በኋላ ነው ወደ መድረክ የሚመጣው፡፡ ወቅቱ የተመቸ አለመሆኑ ነው እንጂ የእውነት ሥራ የሚሠራበት ቤት ነው፡፡ ቤቱ ለባለሙያ ጥሩ ነው፤ በደንብ ትታሻለህ፤ የቁሳቁስ አቅርቦቱ እና ሌሎች ድጋፎችም ጥሩ ናቸው፡፡
የአንተ የትወና እና አዘጋጅነት ጉዞህ፣ አሁን ያለህበት ሁኔታስ ምን ይመስላል?
እድሜ ከትምህርት ቤት እኩል የሚያስተምርህ ነገር አለ፡፡ በጥበብ ጉዞዬ በጣም ብዙ አስተማሪ ሰዎችን አግኝቻለሁ፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ቢኒ ፊልም ፕሮዳክሽን የሚባል አለ፤ እሱ ያስተማረኝ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ከእነዚህ ያገኘሁትን እውቀት ወደዚህ አምጥቼ እየሠራሁ እገኛለሁ፡፡ ትልቅ ተዋናይ እና ዳይሬክተር ወይም ጸሐፊ ነኝ ብዬ አላስብም፡፡ በልምድ ያመጣሁት ነገር አለኝ፤ ራሴንም እያበቃሁ ወደ ጽሑፉ እና ዳይሬክቲንጉ እገባለሁ፡፡ በእጄ ላይ ያሉ ጽሑፎች አሉኝ፡፡ በፊልም እና በአጫጭር ተንቀሳቃስ ፊልሞች ታሪካችንን እና ትውፊታችንን የሚገልጹ ጉዳዮችን ለተመልካች ለማድረስ ውጥን አለኝ፡፡
የሰው ልጅ የእውነት ደስተኛ መሆን ካለበት የሚወደውን ሥራ መሥራት ነው ያለበት፡፡ እኔ ፈጣሪ ባርኮኛል፤ ረድቶኛል፡፡ የምወደውን ሥራ እየሠራሁ ነው፡፡ በሕይወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ የደስታን ምንጭ ከገንዘብ እና ከቁሳቁስ ጋር አላገናኘውም፡፡ በቀን የሆነ መድረክ ሠርቼ ወይም ልምምድ አድርጌ ስወጣ ትልቅ ደስታ ነው የሚሰማኝ፡፡
ቲያትረኛ ገቢው እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡ በተለይ ክፍለ ሀገር ላይ ስትሆን ደግሞ የከፋ ነው፡፡ አዲስ አበባ ብትሆን ከማስታወቂያ፣ ፊልሞችን በመሥራት እና በሌሎች መንገዶች የተሻለ ገቢ ሊኖርህ ይችላል፡፡ የክልል ከተማ ላይ ግን እድሉ በጣም የጠበበ ነው፡፡ ነጋዴ ብሆን ጥሩ ገቢ ይኖረኝ ነበር፡፡ የሙያዬን ፍቅር ግን ከገቢው ጋር አላገናኘውም፤ የእውነቴን ነው የምናገረው፡፡
በአገውኛ ቋንቋ የመጀመሪያው ስለሆነው አንታጉ ፊልም ንገረን?
አንታጉ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ለመጀመሪያ ጊዜ በአገውኛ ቋንቋ የተሠራ ፊልም ነው፡፡ የአገው ሕዝብ የታሪክ፣ የሥልጣኔ እና የቱባ ባህል ባለቤት መሆኑን የሚያሳይ እና የሕዝቡን እሴት እና መስተጋብር የሚያንጸባርቅ ፊልም ነው። ፊልሙ የብሔረሰብ አስተዳደሩን ባህል፣ ታሪክ እና ቋንቋ ለዓለም ለማስተዋወቅ የታለመ ነው።
ፊልሙን ለመሥራት ከአንድ ዓመት በላይ ወስዷል፤ በአገውኛ ቋንቋ የተለያዩ ጽሑፎች እና ዘፈኖች ቢዘፈኑም በቋንቋው ፊልም ያልተሠራ በመሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊልሙን ለመሥራት አስቤ እውን አድርጌዋለሁ። ይህ ለእኔም ለአገው ሕዝብም ትልቅ እድል ነው፡፡ የተሠራው ፊልም የገጠሩን ገፀ-ባህሪ የያዘ ነው፣ በቀጣይ ማኅበረሰቡ የሚደግፈን ከሆነ በርካታ ፊልሞችን ለመሥራት ፈቃደኛ ነን፡፡
በፊልሙ እኔ በዳይሬክተርነት እንዲሁም በተዋናይነት እና የዞኑ ባህል እና ቱሪዝም ሠራተኞች በተዋናይነት ተሳትፈዋል።
ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!
እኔም አመሰግናለሁ!
(ቢኒያም መስፍ)
በኲር የታኅሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም