የደበዘዘዉ መድረክ

0
49

የሁለት ሺህ አስራ ሰባት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ መድን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሻምፒዮን የሆነበት፣ የቀጥታ ስርጭት አስተላላፊው ዲ ኤስ ቲቪ የውል ስምምነቱ የተጠናቀቀበት፣ የአምናው ሻምፒዮኑ ክለብ የተንገዳገደበት ሆኖ ተደምድሟል። ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ መልኩ ከተዋቀረበት 1992 ዓ.ም በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ክለቦች ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ቢወርዱም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዘግይቶ በወሰነው ውሳኔ መሰረት በሊጉ እንዲቆዩ ተደርገዋል።

ኢትዮጵያ መድን ቀሪ ሦስት መርሀግብር እያለው ነው ዋንጫ ማንሳቱን ያረጋገጠው። በአሰልጣኝ ገብረ መድህን ኃይሌ የሚመራው ቡድን ዓመቱን ሙሉ የደረጃ ሰንጠረዡን ሲመራ ከርሞ በዋንጫ ታጅቦ የውድድር ዓመቱን አጠናቋል። ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በተመለሰ በሦስተኛው የውድድር ዓመቱ ነው ዋንጫውን ያነሳው።

አሰልጣኝ ገብረ መድህን ኃይሌ ከሦስት ክለቦች ጋር ሻምፒዮን በመሆን ታሪክ ሠርቷል። ከዚህ በፊት ከጅማ አባጅፋር እና  መቀለ ሰባእንደርታ ጋርም ዋንጫ ማንሳቱ አይዘነጋም። ኢትዮጵያ መድን ከ23 ዓመታት በኋላ ከዋንጫ ጋር ተገናኝቷል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ያነሳ አስረኛው ክለብም በመሆን በታሪክ መዝገብ ሰፍሯል። በዘንድሮው የውድድር ዓመት 306 ጨዋታዎች ተደርገው 584 ግቦች ተቆጥረዋል። በየጨዋታው በአማካይ ከአንድ ግብ በላይ ከመረብ ጋር ተገናኝቷል።

ኢትዮጵያ መድን ብዙ ጨዋታዎችን ያሸነፈ ክለብ ሲሆን በአጠቃላይ 22 መርሀግብሮችን በድል ተወጥቷል። በአንጻሩ ወልዋሎ ዩንቨርሲቲ ክለብ ብዙ ጨዋታዎችን በመሸነፍ ቀዳሚው ክለብ ነው፤ 19 ጨዋታዎችንም ተሸንፏል። ክለቡ ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ያሸነፈ ብቸኛ ክለብ ነው። ፋሲል ከነማ ደግሞ 16 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል። ሻምፒዮኑ ኢትዮጵያ መድን 49 ግቦችን በተጋጣሚዎች ላይ አስቆጥሯል። ይህም ከፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ብዙ ግቦችን ያስቆጠረ ያደርገዋል።

የአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ቡድን በአማካይ ከአንድ ግብ በላይ አስቆጥሯል። ኢትዮጵያ መድን በ1975 ዓ.ም መመስረቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። የ42 ዓመታት ታሪክ ያለው ኢትዮጵያ መድን በ1987 እና 1994 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊም እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል። ብዙ ግብ የተቆጠረባቸው ሁለቱ የትግራይ ክልል ክለቦች ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ እና ስሁል ሽረ ሲሆኑ እኩል 46 ግቦች ተቆጥሮባቸዋል።

የሀዋሳ ከነማው አጥቂ ኤርትራዊው አሊ ሱሌማን በ21 ግቦች ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ አጠናቋል። የመድኑ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑራ ደግሞ ምርጥ ግብ ጠባቂ ሆኖ ጨርሷል።ምርጥ የውድድር ጊዜ ያሳለፈው አቡበከር ኑራ በ22 ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርበት ዓመቱን በስኬት አጠናቋል። አቡበከር አንድ ግብ የሆነ ኳስ ለቡድን ጓደኞቹ አመቻችቶ ማቀበሉ አይዘነጋም።

ሌላኛው የመድኑ ተጫዋች የመሀል ሚዳው ኮከብ ሀይደር ሸረፋ በምርጥ ብቃት ያጠናቀቀበት ዓመት ነበር- የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ። ሀይደር ሸረፋ ከመድን ቁልፍ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። ጋቶች ፓኖም ቡድኑን ከለቀቀ በኋላ የእርሱን ቦታ በመተካት ምርጥ አቋሙን አሳይቷል። በውድድር ዓመቱ አጠቃላይ በ33 ጨዋታዎች ተሰልፎ ተጫውቷል። አምበሉ ሀይደር ሸረፋ ቡድኑን በመምራት ለዋንጫ አብቅቶታል። በግሉም እንደ ቡድንም ድንቅ የውድድር ጊዜ ያሳለፈው ተጫዋቹ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ በአወዳዳሪው አካል መመረጡ የሚታወስ ነው።

በሁለት ሺህ አስራ ሰባት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 49 የውጪ ተጫዋቾች ተጫውተዋል። 565 ተጫዋቾች በሊጉ የተጫወቱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 147ቱ ወጣት ተጫዋቾች መሆናቸውን የሊግ አክሲዮኑ መረጃ ያመለክታል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሊጉ ዋነኛ ተፎካካሪ የነበረው ባሕር ዳር ከነማ ዘንድሮ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ነው የጨረሰው። የጣና ሞገዶቹ በዚህ ዓመት ወጥ ብቃት ማሳየት ተስኗቸው ዓመቱን አጠናቀዋል። ቡድኑ ካለፈው ዓመት አንጻር ሲገመገም ሜዳ ውስጥ ደክሞ የታየበት እንደነበር ብዙዎች ይመሰክራሉ።

ቡድኑ በየጨዋታው በአማካይ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠሩን ቁጥራዊ መረጃዎች ያስረዳሉ። ባሕር ዳር ከነማ ካደረጋቸው 34 ጨዋታዎች 15ቱን አሸንፏል፤ ዐስሩን ሲሸነፍ በዘጠኙ መርሀግብር ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። አርባ ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ከኢትዮጵያ መድን ቀጥሎ አስፈሪ የፊት መስመር ካለው ሀዋሳ ከተማ ጋር በእኩል ደረጃ ተቀምጧል። የኋላ ክፍሉም ሦስተኛው የፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ክለብ መሆኑን ቁጥራዊ መረጃዎች ያሳያሉ። ነገር ግን ካለፉት ዓመታት አንጻር ግን ትንሽ ተዳክሞ መታየቱን ሜዳ ላይ ተመልክተናል።

ሌላኛው የአማራ ክልል ክለብ ፋሲል ከነማ ዘንድሮ የቀድሞ ኃያልነቱ እና ጉልበቱ ከድቶት ታይቷል። ፋሲል ከነማ ዓመቱን ሙሉ ላለመውረድ ሲታገል እንደነበር የሚታወስ ነው። አጼዎቹ እስከመጨረሻው ሳምንት ድረስ በሊጉ መቆየታቸውን አላረጋገጡም ነበር። ምንም እንኳ ዘንድሮ ወደታችኛው የሊግ እርከን የሚወርድ ክለብ እንደማይኖር የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ዘግይቶ ቢያሳውቅም በመጨረሻው የ36ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ መቀለ ሰባእንደርታ በኢትዮ ኤሌክትሪክ አንድ ለባዶ መሸነፉን ተከትሎ ነው አጼዎቹ በሊጉ መቆየታቸውን ያረጋገጡት።

ቀደም ሲል የፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ጉልበታቸው ዝሎ አቅማቸው ተዳክሟል። ክለቡ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደገ በኋላ አስከፊውን የውድድር ዓመት ያሳለፈው ዘንድሮ ነው። ፋሲል ከነማ ካደረጋቸው 34 ጨዋታዎች ዘጠኙን ብቻ ነው ያሸነፈው። በተመሳሳይ ዘጠኝ ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፏል ። ቀሪ 16 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ነው ያጠናቀቀው። በጌታነህ ከበደ የሚመራው የፊት መስመር ያን ያህል ደካማ ነው ባይባልም የኋላ ክፍሉ ግን በቀላሉ ግቦች የሚቆጠሩበት እና የሚረበሽ እንደነበር አይዘነጋም።

አጼዎቹ በተጋጣሚ መረብ ላይ ካስቆጠሯቸው ግቦች የበለጠ በእነርሱ መረብ ላይ ተቆጥሮባቸዋል። 33 ግቦችን ሲያስቆጥሩ 35 ግቦች ደግሞ በእነርሱ የግብ መረብ ላይ አርፏል። ፋሲል ከነማ ጠንካራ እና ደካማ ጎኑን በመገምገም ከወዲሁ ለቀጣይ የውድድር ዓመት መዘጋጀት አለበት- የብዙዎች ሀሳብ ነው። በሂሳባዊ ስሌት ወደታችኛው የሊግ እርከን የወረዱት ሦስት የትግራይ ክለቦችን ጨምሮ መቀለ ሰባእንደርታ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ ክለብ፣ ስሁል ሽረ እና አዳማ ከተማ በቀጣይም በፕሪሚየር ሊጉ እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዘግይቶ ውሳኔውን አስተላልፏል። የዘንድሮው የከፍተኛ ሊግ የውድድር ዓመት ሸገር ሲቲ እና ነገሌ አርሲን ወደ ፕሪምየር ሊጉ አሳድጎ መጠናቀቁ አይዘነጋም። ታዲያ የ2018 የውድድር ዓመት በ20 ክለቦች የሚከናወን ይሆናል።

የዘንድሮው የፕሪሚየር ሊጉ የውድድር ዓመት ክለቦች ከክፍያ ጋር በተያያዘ እና ከአቅም በታች በመጫወት ተጠርጥረው ቅሬታ ቀርቦባቸው በውዝግብ የውድድር ዓመቱ ተጠናቋል።

ሱፐር ስፖርት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ  እድገት የበኩሉን አስተዋፆ  አድርጎ ቆይታውን አጠናቋል። ዲ ኤስ ቴቪ ሱፐር  ስፖርት ባለፉት አምስት ዓመታት  ስምንት መቶ ሁለት ጨዋታዎችን በሰባት ከተሞች  በቀጥታ ስርጭት አስተላልፏል። ዲ ኤስ ቴቪ የኢትዮጵያን  ባህል እና ቋንቋዎችን ለዓለም ሕዝቦች አስተዋውቋል፤ የኢትዮጵያን እግር ኳስንም ከነውስብስብ ችግሩም ቢሆን ለዓለም ሕዝብ በቀጥታ ስርጭት አስተላልፏል።

ኢትዮጵያ መድን የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን ተከትሎ በቀጣይ ዓመት በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ መድረክ የሚሳተፍ ይሆናል። ከወገብ በላይ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ወላይታ ዲቻ ደግሞ በአቋራጭ የአፍሪካ መድረክ ተሳታፊ ይሆናል። የዘንድሮው የኢትዮጵያ ዋንጫ ከሲዳማ ቡና ተነጥቆ በፎርፌ ለጦና ንቦች መሰጠቱን ተከትሎ ነው ወላይታ ዲቻ በቀጣይ ዓመት በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚሳተፈው።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here