የዲሞክራቲክ ኮንጎ አሳዛኝ የዓለም ዋንጫ ታሪክ

0
10

ባለፉት ጥቂት ዐስርት ዓመታት የአፍሪካ እግር ኳስ ረጅም መንገድ ተጉዟል። ዛሬ የአፍሪካ ኮከቦች በዓለም ታላላቅ ሊጎች ላይ በጉልህ ሲያንጸባርቁ ማየት የተለመደ ነው። በየአራት ዓመቱም በዓለም ዋንጫ መድረክ እንደ ካሜሩን፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ግብጽ እና ጋና ያሉ ሀገራት የሚያስመዘግቧቸው  ውጤቶች የአፍሪካ አህጉር የእግር ኳስ እድገት አብነቶች ናቸው።

ነገር ግን ይህ ታሪክ ከመጻፉ በፊት አፍሪካ በዓለም መድረክ ላይ ያላት ስም የተለየ ነበር። ለረጅም ጊዜ የአውሮፓ እና የደቡብ አሜሪካ የእግር ኳስ ኃያላን ሀገራት ለአፍሪካ ምንም አይነት ክብርም ሆነ ትኩረት አይሰጡም ነበር። ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራትን ያገለለ በሚመስለው የፊፋ የማጣሪያ ሕጎች ምክንያት አንድ ጥቁር አፍሪካዊ ሀገር ወደ ታላቁ መድረክ ለመግባት እስከ 1974 እ.አ.አ ድረስ መጠበቅ ነበረባት። ያቺ ሀገር የቀድሞዋ ዛየር (የአሁኗ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ) ነበረች። የቀድሞዋ ዛየር በወቅቱ በእግር ኳስ ደካማ ሀገር አልነበረችም። እንዲያውም የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት በመሆኗ ከአፍሪካ ጠንካራ ቡድኖች ውስጥ አንዷ ነበረች።

የዚህ ቡድን ስኬት ደግሞ ከአንድ ሰው ህልም ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነበር፤ የሀገሪቱ ፈላጭ ቆራጭ ከነበረው መሪ ፕሬዝዳንት ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ ጋር። ሞቡቱ ስልጣናቸውን ለማጽናት እና የሀገራቸውን ገናናነት ለዓለም ለማሳየት እግር ኳስን እንደ ዋና መሳሪያ ይጠቀሙበት ነበር። የሀገሪቱን ብሄራዊ ቡድን “ነብሮቹ” (The Leopards) በሚል ስያሜ በማደራጀት ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እና የሞራል ድጋፍ ያደርጉለት ጀመር።

የሞቡቱ አላማ ግልጽ ነበር፤ ዛየርን በእግር ኳስ መድረክ የአፍሪካ ሃያል በማድረግ የመንግሥታቸውን ጥንካሬ ማሳየት። ይህንን ህልማቸውን እውን ለማድረግ የሀገር ውስጥ ሊግን አጠናከሩ፤ ዘመናዊ ስታዲየሞችንም አስገነቡ፤ እንዲሁም በወቅቱ ከነበሩት ምርጥ አሰልጣኞች አንዱ የነበረውን ዩጎዝላቪያዊውን ብላጎዬ ቪዲኒችን ቀጠሩ። ይህ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይም ውጤት አልባ አልነበረም። “ነብሮቹ” እ.ኤ.አ በ1974 የአፍሪካ ዋንጫን  በማሸነፍ ለዓለም ዋንጫው በማለፍ አዲስ ታሪክ አስመዘገቡ።

ይህም  በመላው ዛየር ከዳር እስከ ዳር የደስታ ማዕበልን አስነሳ። ፕሬዝዳንት ሞቡቱ ለእያንዳንዱ ተጫዋች ዘመናዊ መኖሪያ ቤት እና የግል መኪና በመሸለም ለቡድኑ ያላቸውን ድጋፍ ገለጹ። ተጫዋቾቹ ብሄራዊ ጀግና ተደርገው ሲወደሱ የዛየር ሕዝብም ቡድናቸው በዓለም መድረክ ላይ የአፍሪካን ክብር እንደሚያስጠብቅ ትልቅ ተስፋ ሰንቆ ነበር። ነገር ግን ይህ የደስታ እና የተስፋ ጉዞ ብዙም ሳይቆይ ወደ አስከፊ ቅዠት እንደሚቀየር ማንም አላሰበም ነበር።

ነብሮቹ ወደ ምዕራብ ጀርመን ሲያቀኑ የተሸከሙት የሀገራቸውን ተስፋ ብቻ አልነበረም፤ የመላው ጥቁር አፍሪካ ኩራት እና ውክልናን ጭምር እንጂ። በምድባቸውም ከጠንካራዎቹ ስኮትላንድ፣ ዩጎዝላቪያ እና በወቅቱ የዓለም ሻምፒዮን ከነበሩት ብራዚል ጋር ተደልድለው ነበር። የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ከስኮትላንድ ጋር ሲሆን ጨዋታውንም ሁለት ለባዶ ተሸንፈዋል:: ባሳዩት አስደናቂ እና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ግን ዓለም አቀፍ አድናቆትን አትርፈው ነበር። ይህ ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ግን ብዙም አልቆየም። ከጨዋታው በኋላ የተፈጠረው ክስተት የቡድኑን የሞራል አንኮታኮተው።

ተጫዋቾቹ ከፕሬዝዳንቱ ቃል ከተገባላቸው ክፍያ በተጨማሪ ከፊፋ የሚያገኙት ገንዘብ እንዳለ ያውቁ ነበር። ከቡድኑ ጋር የተጓዙ የመንግሥት እና የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለስልጣናት ለተጫዋቾች የተዘጋጀውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ለግል ጥቅማቸው አዋሉት። ተጫዋቾቹም ለደመወዝ እና ለቦነስ ይመደባል ብለው የጠበቁት ገንዘብ እንደተዘረፈ አወቁ:: እናም ምንም ክፍያ እንደማያገኙ ሲረዱ በቁጣ እና በክህደት ስሜት ተዋጡ።  ለሁለተኛው የዩጎዝላቪያ ጨዋታ ወደ ሜዳ እንደማይገቡ በማመፅ አድማ መቱ። ይህ የአድማው ዜና በፍጥነት ኪንሻሳ ከሞቡቱ ጆሮ ደረሰ።

አምባገነኑ መሪም ተዋረድኩ በሚል ስሜት  በቁጣ ተሞሉ። የተጫዋቾቹን እምቢተኝነትም እንደ ትልቅ ክህደት ቆጠሩት። ፊፋ የውድድሩን ስም ለማዳን ጣልቃ ገብቶ ለእያንዳንዱ ተጫዋች ሦስት ሺህ የጀርመን ማርክ (ማርክ የቀድሞ ስሙ ነው) እንደከፈላቸው ቢነገርም ሞቡቱ ግን ለተጫዋቾች መራራት አልቻለም::

ወዲያውኑ የቤተመንግሥት ጠባቂዎቻቸውን ወደ አውሮፓ በመላክ “ጨዋታውን ካልተጫወታችሁ ከባድ መዘዝ ይጠብቃችኋል” የሚል የማያዳግም ማስፈራሪያ አስተላለፉ። ምንም እንኳን ሳይወዱ በግዳቸው ወደ ሜዳ ለመግባት ቢስማሙም ስሜታቸው እና የጨዋታ ፍላጎታቸው ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ ነበር።

ተጫዋቾቹ ሞራላቸው የተሰበረ እና ምንም አይነት የጨዋታ ስሜት በሌለበት ሁኔታ ከዩጎዝላቪያ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ ወደ ሜዳ ገቡ። ዛየር በታሪኳ ከተሸነፈችባችው የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ሁሉ የከፋው ይህ ዘጠኝ ለባዶ በሆነ ውጤት የተሸነፉበት ነው። ይህ ሽንፈት የዛየርን ገፅታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያዋረደ እና ሞቡቱን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳፈረ ነበር።

ዩጎዝላቪያ በሃያ ደቂቃ ውስጥ ሦስት ግቦችን ስታስቆጥር አሰልጣኝ ቪዲኒች ግብ ጠባቂውን ካዛዲ ሙዋምባን አስወጥቶ በምትኩ ቁመቱ አጭር (163 ሳ.ሜ) የሆነውን ዲምቢ ቱቢላንዱን አስገባ። ቱቢላንዱ በገባ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ግብ ተቆጠረበት፤ በዚያ ምሽትም ስድስት ተጨማሪ ግቦች ተቆጠሩበት። ይህ ሽንፈት በፕሬዝዳንት ሞቡቱ ላይ ከፍተኛ ቁጣን ቀሰቀሰ። በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሱበት ቡድን እንዲህ አይነት ውርደት መቀበሉን ማመን እና መቀበል  አልቻሉም።

የፕሬዝዳንት ሞብቱ ጠባቂዎች በድጋሚ ወደ ተጫዋቾቹ ሆቴል በመሄድ ከሁሉም ጋዜጠኞች እንዲርቁ አደረጉ። ከዚያም ለተጫዋቾቹ ቀጥተኛ እና የማያዳግም ማስጠንቂያ ተሰጣቸው:: “ከብራዚል ጋር በምታደርጉት ቀጣይ ጨዋታ ከአራት ግብ በላይ ከተቆጠረባችሁ አንዳችሁም ወደ ሀገራችሁ በህይወት አትመለሱም” የሚል ነበር። ይህ ማስፈራሪያ የተጫዋቾቹን ስጋት ወደ ፍርሃት ለወጠው። አሁን ጉዳዩ የእግር ኳስ ጨዋታ መሆኑ ቀርቶ የህይወት እና የሞት ጉዳይ ሆኗል።

እ.ኤ.አ ሰኔ 22 ቀን 1974 ዛየር ከዓለም ሻምፒዮኗ ብራዚል ጋር የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ለማድረግ ወደ ሜዳ ገባች። የዛየር ተጫዋቾች ዋነኛ አላማቸው ጨዋታውን ማሸነፍ ሳይሆን ከአራት ግብ በላይ እንዳይቆጠርባቸው በመከላከል ህይወታቸውን ማትረፍ ነበር። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ብራዚል ሁለት ለባዶ  እየመራች ነበር። በዚህን ጊዜ ብራዚል ከዛየር የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ የቅጣት ምት አገኘች። የብራዚል ተጫዋቾች ኳሱን ሊመቱ ሲዘጋጁ ያልተጠበቀ እና በዓለም ዋንጫ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ ክስተት ተፈጠረ። የዛየሩ ተከላካይ ምዌፑ ኢሉንጋ በብራዚል ተጫዋች ላይ ያልተጠበቀ ጥፋት ሠራ።

ይህንን ድርጊት የተመለከቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ግራ ተጋብተው ነበር። የቢቢሲው ተንታኝ ጆን ሞትሰን ድርጊቱን “የአፍሪካውያን የእግር ኳስ ህግ አለማወቅ አስገራሚ ማሳያ” ሲል ተችቶታል። ነገር ግን እውነታው ከዚህ የተለየ ነበር። ኢሉንጋ ድርጊቱን የፈጸመው ከአለማወቅ ሳይሆን ከከፍተኛ ፍርሃት እና ተስፋ መቁረጥ ነበር። በኋላ ላይ በሰጠው ቃለ መጠይቅ  እንዳስረዳው አላማው ጊዜ በማባከን የብራዚል ተጫዋቾችን ትኩረት መስበር እና ምናልባትም በቀይ ካርድ ከሜዳ በመውጣት የቡድኑን ስቃይ ማቆም ነበር። ነገር ግን ዳኛው በቢጫ ካርድ ብቻ አለፉት።

ብራዚል በኋላ ላይ አንድ ተጨማሪ ግብ ብታስቆጥርም ጨዋታው ሦስት ለባዶ በሆነ ውጤት ተጠናቀቀ። የዛየር ተጫዋቾች ጨዋታውን ቢሸነፉም በህይወት የመቆየት እድላቸውን አስጠብቀዋል። የመጨረሻው የፍፃሜ ፊሽካ ሲነፋ ተጫዋቾች ትልቅ እፎይታ ተሰምቷቸው ነበር። ከፕሬዝዳንት ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ የተላለፈላቸውን የሞት ፍርድ አስቀርተዋልና ነው። ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የጠበቃቸው መከራ እና ስቃይ ግን በጀርመን ሜዳዎች ላይ ከደረሰባቸው ሽንፈት እጅግ የከፋ ነበር። የዓለም ዋንጫው ለእነሱ የውርደት መጨረሻ ሳይሆን ረጅም እና አሰቃቂ የመከራ ህይወት መጀመሪያ ሆኖ ተመዘገበ።

ወደ ኪንሻሳ ሲመለሱ የአፍሪካ ዋንጫን ይዘው ሲመጡ እንደተደረገላቸው አይነት የጀግንነት አቀባበል አልጠበቃቸውም። ከአውሮፕላን ሲወርዱ የጠበቃቸው ባዶ እና ቀዝቃዛ የሆነ የወታደራዊ  መኪና ነበር። ከአውሮፕላን ማረፊያው በቀጥታ የተወሰዱት ወደ ፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት ነበር። ሞቡቱ በዓለም መድረክ  ሀገራችንን አዋርዳችኋል በሚል ከባድ ወቀሳ አወረደባቸው። ሁሉም የቡድኑ አባላት ከዛየር እንዳይወጡ የዕድሜ ልክ እገዳ ተጣለባቸው። ይህ እገዳ በአውሮፓ የመጫወት ህልማቸው እውን የሚሆንበትን ወርቃማ እድል በአንድ ጀንበር አጨለመው።

ከዓለም ዋንጫው በኋላ ሞቡቱ በእግር ኳሱ ላይ ያላቸውን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ስላጡ ለብሄራዊ ቡድኑም ሆነ በአጠቃላይ ለሀገር ውስጥ እግር ኳስ የሚደረገው ድጋፍ ቆመ። እነዚያ የሀገር ጀግኖች የነበሩ ተጫዋቾች ወደ አስከፊ የድህነት አዘቅት ውስጥ ገቡ። የዚህ ሰለባ ከሆኑት መካከል የቡድኑ ኮከብ ተጫዋች የነበረው ንዳዬ ሙላምባ አንዱ ነው። ሙላምባ በ1974ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ዘጠኝ ግቦችን በማስቆጠር የውድድሩ ጀግና የነበረ ሲሆን ከዓመታት በኋላ ግን በደቡብ አፍሪካ በልመና ሲኖር በአሳዛኝ ሁኔታ ተገኝቷል።

በአሜሪካ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጥምረት ለሚዘጋጀው ለ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሀገራት የመጨረሻውን የማጣሪያ ውድድር አድርገዋል:: ታዲያ በምድብ ሁለት ተደልድላ ማጣሪዋን ስታከናውን የነበረችው ምዕራብ አፍሪካዊት ሀገር ዲሞክራቲክ ኮንጎ ከምድቡ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች:: ነብሮቹ በዓለም ዋንጫው የሚሳትፋትን ትኬት ለመቁረጥም ወደፊት የጥሎ ማለፍ መረሀግብር የሚጠብቃት ይሆናል:: ምናልባት በዓለም ዋንጫው ባትሳተፍ እንኳ ቡድኑ ከ51 ዓመታት በፊት የነበረው ችግር አይገጥመውም:: ስፖርት ጋዜጣ እና ዴይሊ ኔሽን አፍሪካ የመረጃ ምንጭ ናቸው::

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here