የዳርቻዎች ስጋት

0
177

በአትላንቲክ እና በፓስፊክ ውቅያኖስ እንዲሁም በባሕረሰላጤው ዳርቻዎች በሚገኙ 32 ከተሞች በቀጣዮቹ ሰላሳ ዓመታት የጐርፍ መጥለቅለቅ እና የመሬት መስመጥ እንደሚከሰት፤ በአደጋውም አምስት መቶ ሺህ ነዋሪዎች ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ መተንበዩን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

በአሜሪካ የቨርጂኒያ ቴክኖሎጂ የምድር መቃኛ እና የአዳዲስ ግኝቶች መፈልፈያ የምርምር ጣቢያው አሁን ላይ ያለውንና በቀጣዮቹ 26 ዓመታት በ32 የባሕር ተጐራባች ከተሞች የሚኖሩ አምስት መቶ ሺህ ነዋሪዎች ተጐጂ እንደሚሆኑ በትንበያ ማረጋገጡን አመላክቷል፡፡

የቅድመ ትንበያና የምርምር ሥራው መሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ማንቺር ሺርዜ በህዋ ላይ ባሉ የራዳር ሳተላይቶች የተሰበሰበ መረጃን በመቀመር በባህር ዳርቻዎች ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ጥራት ባለው ምስል ማደራጀታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ተመራማሪዎቹ አሁን ያለውን ጉዳት እና በመጪዎቹ ዓመታት ሊከሰት የሚችለውን በንጽጽር ቀምረው አመላክተዋል፡፡ በሁነቱ ከ500 እስከ 700 ማይል መሬት በጐርፍ እንደሚጥለቀለቅ እና ከ176 ሺህ እስከ 518 ሺህ ሰዎች በቀጥታ ተጐጂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተንብየዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከ94 ሺህ  እስከ 288 ሺህ የሚደርስ ንብረት፣ በገንዘብ ከ32 ቢሊዮን እስከ ከ109 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሊወድም ይችላል- እንደትንበያው፡፡

በቅድመ ትንበያ ምርምሩ ተባባሪዎች መካከል በህንድ የሳይንስ ትምህርትና ምርምር ተቋም እንዲሁም በእንግሊዝ የኢስት አንጀሊያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እንደሚገኙበት ድረ ገፁ አስነብቧል፡፡

ጥናትና ምርምሩ አሁን ላይ በባህር ዳርቻ ከሚገኙ 32 ከተሞች በ24ቱ በዓመት እስከ ሁለት ሚሊ ሜትር የመሬት መስመጥ የተስተዋለባቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የታየው የመስመጥ ልኬታ ወይም መጠን አነስተኛ ቢመስልም በመጪዎቹ ዓመታት እየጨመረ እንደሚሄድ ነው ያሳሰቡት፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here