የድርቁ አስከፊ ገጽታ

0
339

በአማራ ክልል በ2015/2016 የምርት ዘመን በተለያዩ አካባቢዎች ድርቅ ተከስቷል:: የተከሰተው ድርቅ በሰው እና በእንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው::

በክልሉ በሰሜን ጎንደር፣ በማዕከላዊ ጎንደር፣ በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ጎንደር ዞኖች እንዲሁም በዋግ ኸምራ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደሮች በተለያዩ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ድርቅ እንደተከሰተ ከአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በተከሰተው ድርቅ ዜጎች ለማሕበራዊ እና ለምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ እየተዳረጉ ነው:: ሰዎች እየተራቡ፤ እንስሳትም እየሞቱ ነው:: ለአብነትም በሰሜን ጎንደር ዞን በተከሰተው ድርቅ ከሠላሳ በላይ ሰዎች በረሃብ እና ከ72 ሺህ በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸውን የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በጥናት ማረጋገጡ አይዘነጋም።

በተመሳሳይ ከድርቁ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ በሽታዎች ችግሩን አባብሰውታል:: በድርቁ ከተጋለጡ አካባቢዎች መካከል ሌላዉ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን አንዱ ነው። ዝናብ ያላገኙ አካባቢዎች መኖራቸውን ከአካባቢው በስልክ ያነጋገርናቸው አርሶ አደር እና የወረዳው የሥራ ኃላፊ ተናግረዋል:: የዝናብ እጥረቱ ባስከተለው ድርቅ ለረሃብና መፈናቀል እንደዳረጋቸው ነው አርሶ አደሩ በስልክ  ለበኩር የተናገሩት::

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኪንፋዝ በገላ ወረዳ ቀንወጣ ቀበሌ ኗሪው አርሶ አደር አለነ ወርቅነህ በዚህ ዓመት ያጋጠመውን ድርቅ “በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አስከፊ” ሲሉ ነው የገለጹት:: ነዋሪዎች እየተሰደዱ እንስሳትም እየሞቱ መሆኑን ይናገራሉ:: ከሞት የተረፉ እንስሳትም መኖ እና  ውኃ ፍለጋ ወደ አጎራባች ወረዳዎች እየሄዱ ነው ብለዋል።

እንደ አርሶ አደሩ ገለጻ ሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ያካፋው ዝናብ ድጋሚ ነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም መጠነኛ ዝናብ ዘንቦ ከዚያ በኋላ ዘንቦ አያውቅም:: በዚህም ምክንያት መሬታቸዉን አርሰዉ በተለያዩ ሰብሎች የሸፈኑት ስምንት ሄክታር መሬት ከጥቅም ውጭ እንደሆነባቸው አብራርተዋል።

ይህ አስከፊ ድርቅ በሰው እና በእንስሳት ላይ የከፋ ጉዳት  እያደረሰ በመሆኑ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠው አርሶ አደሩ ጠይቀዋል:: እስካሁን ድጋፍ እንዳላገኙ የሚናገሩት አቶ አለነ “ዛሬ፣ ነገ ድጋፍ ይመጣልን ይሆን!  በሚል ተስፋ እንገኛለን” ብለዋል:: ስድስት የቤተሰብ አባላትን እንደሚያስተዳድሩ የተናገሩት አርሶ አደር “ፈጣሪን ይታረቀን። ለዕለት ጉርሳችን መንግሥት ሊደርስልን ይገባል” ሲሉ ተማጽነዋል።

በተመሳሳይ በቀበሌው የውኃ ችግር በመኖሩ ውኃ ለማምጣት ብዙ ርቀት መጓዝ ግድ ይላል። በዚህም ምክንያት ሁለት ልጆቻቸው ከትምህርት ገበታ ውጭ እንደሆኑ አስረድተዋል።

አርሶ አደር አለነ በመጨረሻም “በዝናብ እጥረቱ ምክንያት የተዘራውን ሰብል ከመሬት አስቀርቶታል። ማጭድ አልሰደድንበትም። በተከሰተው ድርቅም ለረሃብ እና ለበሽታ ተጋልጠናል” ብለዋል። በመሆኑም አስቸኳይ ድጋፍ እንዲሰጣቸው የድረሱልን ጥሪ አቅርበዋል።

“በድርቁ ምክንያት ወንዞች ደርቀው ውኃ በመጥፋቱ የ6 እና የ7 ሰዓት መንገድ ውኃ ፍለጋ ለመጓዝ ተገደናል” ያሉት ደግሞ በዚሁ ወረዳ የስላሬ ቀበሌ ኗሪ አርሶ አደር ዓለምነው ገነት ናቸው:: አርሶ አደሩ በዘር የሸፈኑት ዘጠኝ ሄክታር መሬት ከጥቅም ውጪ እንደሆነባቸው እና ሁለት እንስሳት እንደሞቱባቸው በስልክ ነግረውናል።

ተማሪዎች ለእንስሳት መኖ እና ውኃ ፍለጋ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ እንደተገደዱም አክለዋል። እስካሁን ድረስ ምንም ድጋፍ እንዳላገኙ የሚናገሩት አርሶ አደሩ መንግሥት እንዲደርስላቸው ጥሪ አቅርበዋል:: ነዋሪዎች መታከሚያ  ገንዘብ አጥተው ሕክምና ማግኘት እንዳልቻሉም አክለዋል።

ችግሩ እየከፋ መሆኑን በማንሳትም አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። “ይህ ካልሆነ ግን ችግሩ መናገር ከምንችለው በላይ እጅግ ይከፋል” ብለዋል።

አቶ ወረዳው ሹሜ በማዕከላዊ ጎንደር  ዞን የኪንፋዝ በገላ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ ናቸው። እርሳቸውም የአርሶ አደሩን ሐሳብ ይጋራሉ። በአካባቢው የተከሰተው ድርቅ ነዋሪዎችን ለከፋ ችግር እየዳረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ወረዳው ለድርቅ ተጋላጭ ከሆኑ ወረዳዎች መካከል አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል አስተዳዳሪው በበጀት ዓመቱ ክረምቱ ዘግይቶ ገብቶ ቀድሞ በመውጣቱ የዝናብ እጥረት ተከስቷል ብለዋል። ይህም አርሶ አደሩ የዘራውን ከጥቅም ውጪ እንዳደረገው ተናግረዋል።

ድርቁ ባስከተለው ረሃብ እንስሳት እየሞቱ  ቀሪዎች ደግሞ ወደ አጎራባች ወረዳዎች  እና ቀበሌዎች እየተሰደዱ መሆኑን  አስረድተዋል:: እንደ ምክትል አስተዳዳሪው ማብራሪያ በወረዳው ከፍተኛ የውኃ ችግር አለ። ችግሩም  ማሕበረሰቡን ለከፋ ችግር አጋልጦታል። ስለሆነም “አስቸኳይ መፍትሔ ይፈልጋል” ይላሉ።

ችግሩን ለዞኑ እና ለክልሉ በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም በቂ ድጋፍ እንዳልተገኘ ያስረዳሉ:: ይህ በእንዲህ እንዳለ በእንስሳት ላይ እየተከሰተ ያለውን በሽታ ለመከላከል ወረዳው ባለው አቅም ሕክምና እየሰጠ መሆኑን አስረድተዋል። የጋማ፣ የዳልጋ ከብቶች እና መሰል እንስሳት በድርቁ ምክንያት እንደሞቱ ለበኩር በስልክ ተናግረዋል።

በኪንፋዝ በገላ ወረዳ 18 ቀበሌዎች በድርቅ የተጎዱ መሆናቸውን ምክትል አስተዳዳሪው ተናግረዋል:: ችግሩም ከወረዳው አቅም በላይ መሆኑን አስታውቀዋል:: እንደ አቶ ወረዳው ማብራሪያ ማሕበረሰቡ የዕለት ጉርስ እያጣ፣ በውኃ ጥም እየተሰቃየ፣ እንስሳቱ እየሞቱ እና መኖ ፍለጋ እየተሰደዱ ነው። በመሆኑም አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት  መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በወረዳው በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በሽታዎች ተከስተው እንስሳት እየሞቱ መሆኑን አቶ ወረዳው ተናግረዋል:: አስቸኳይ ድጋፍ ካልተደረገም ችግሩ እንደሚከፋ አስጠንቅቀዋል። በመሆኑም ሁሉን አቀፍ ርብርብ ማድረግ እና በቅንጅት መሠራት እንዳለበት ጠይቀዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ  አቶ ኑረዲን ሰይድ    በዞኑ  በአምስት ወረዳዎች ድርቅ መከሰቱን ገልጸዋል:: በኪንፋዝ በገላ፣ ምሥራቅ በለሳ፣  ምዕራብ በለሳ፣ ጎንድር ዙሪያ እና ወገራ ወረዳዎች ድርቅ መከሰቱን ተናግረዋል:: በተለይ በኪንፋዝ በገላ፣ ምሥራቅ በለሳ እና ምዕራብ በለሳ ወረዳዎች ድርቁ ከባድ መሆኑን ለበኩር በስልክ ተናግረዋል::

ምሥራቅ በለሳ እና ኪንፋዝ በገላ ወረዳዎች በመኸር ወቅቱ ሁለት ቀን ብቻ ዝናብ እንዳገኙ አስረድተዋል:: በዚህ ምክንያት የተከሰተው ድርቅ በሰው እና በእንስሳት ላይ አደጋ አስከትሏል ነው ያሉት።

በአጠቃላይ በአምስቱ ወረዳዎች ከ253 ሺህ በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል:: እስካሁን የክልሉ መንግሥት ለምሥራቅ በለሳ ወረዳ አራት ሺህ ኩንታል እና የፊደራል መንግሥት ደግሞ ለኪንፋዝ በገላ ወረዳ 120 ኩንታል ዱቄት ድጋፍ እንዳደረጉ ተናግረዋል።

የጎንደር ሕብረት 400 ኩንታል በቆሎ እንዲሁም የተለያዩ በጎ አድራጎት ድረጅቶች 500 ኩንታል ዱቄት የከፋ ችግር ላለባቸው በዞኑ ለሚገኙ ዜጎች ድጋፋቸውን መለገሳቸውን ተናግረዋል።

ለክልሉም ሆነ ለፌደራል መንግሥት ችግሩን ቢያሳውቁም በቂ መፍትሄ እየተሰጠ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ድርቁ እየከፋ የመጣበት ወቅት በመሆኑ የእንስሳት መኖ እና የውኃ እጥረት ከወትሮው በተለየ መልኩ ተከስቷል። እንስሳትም  እየሞቱ እና እየተሰደዱ ነው። ነዋሪዎች ውኃ ለማግኘት ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ እንደሚጓዙ ነግረውናል። ግጭቱ እና የነዳጅ ቅርቦት እጥረት ደግሞ ለችግሩ አባባሽ ምክንያት ሆነዋል።

በመሆኑም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች አካላት እጃቸውን እንዲዘረጉ፣ ለወገናቸውም እንዲደርሱላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

በተመሳሳይ የዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ድርቁ ከባድ ጉዳት ካደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው። የብሔረሰብ አስተዳደሩ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ ለበኩር በስልክ እንደገለጹት በብሔረሰብ አስተዳደሩ ሰሀላ ሰየምት፣ ዝቋላ እና አበርገሌ ወረዳዎች ድርቁ የከፋባቸው ወረዳዎች ናቸው። በሌሎች ወረዳዎችም በከፊል የተጎዱ እንዳሉ አስረድተዋል።

ለድርቁ ተጋላጭ ዜጎች ምላሽ ለመስጠት የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል። ድጋፍ የሚሹ ከ425 ሺህ በላይ ዜጎች እንደተለዩም ተናግረዋል:: እስካሁን የሁለት ዙር ድጋፍ መደረጉን የሚናገሩት ኃላፊዉ ዜጎች ተረጋግተው በቀያቸው እንዲቀመጡ ሥራዎች እየተሠሩ ቢሆንም የእንስሳት መኖ እጥረት ፈተና መሆኑን አስረድተዋል።

በጉዳቱ ልክ ድጋፍ ባይደረግም ረጅ ድርጅቶች እና መንግሥት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በተመሳሳይ ከ171ሺህ በላይ እንስሳትን ወደ አጎራባች ወረዳዎች ሄደው እንዲቆዩ ተደርጓል ብለዋል። ነገር ግን የእስሳት መድኃኒት እጥረት ችግሩን ፈታኝ አድርጎታል ነው ያሉት።

ድርቁ በሰው እና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አቶ ምህረት አስረድተዋል፤ ችግሩ ከአስተዳደሩ አቅም በላይ በመሆኑም ርብርብ እንደሚጠይቅ አክለዋል::

የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ከረጅ ድርጅቶች እና ለጋሽ ባለሃብቶች የሚገኘውን ድጋፍ ለተጎጅዎች እያቀረበ መሆኑን ቢገልጽም ድርቁ ካለው ስፋት እና መጠነ ሰፊ ችግር አኳያ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here