የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ (ፖስትፒል)

0
519

በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 05 ሰፈነ ሰላም ክፍለ ከተማ በፋርማሲ ሥራ የሚተዳደሩት እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ባለሙያ እንደሚናገሩት በሥራቸው ሦስት ዓመታትን እንዳስቆጠሩ በማንሳት ያልታሰበ የእርግዝና መከላከያ ወይም ፖስትፒል የሚገዙ ደንበኞች በየቀኑ ቁጥራቸው እንደጨመረ ይገልፃሉ::

እንደባለሙያዋ ማብራሪያ በተደጋጋሚ የሚመጡ ሴቶችን የጎንዮሽ ጉዳት ስለሚኖረው ቋሚ የእርግዝና መከላከያ እንዲወስዱ ምክር ይለግሳሉ፤ ይሁን እንጂ ደንበኞቻቸው ምክራቸውን እንደማይቀበሉ እና ወደሌላ ፋርማሲ ሄደው ይገዛሉ፤ ሌሎችም እንደ እሳቸው ፋርማሲ ሙያ ላይ ያሉ ሰዎችም እንደዚህ ዓይነት ድርጊት መመልከታቸውን እንደተወያዩ ነግረውናል::

ይህን መነሻ በማድረግ ፖስትፒል ምንድን ነው? ጥቅም እና ጉዳቱስ? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ባለሙያ አነጋግረናል፤ ለጥያቄዎቹ መረጃ የሰጡን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የቤተሰብ አገልግሎት አስተባባሪ ሲስተር ንብረት እያሱ ናቸው::

ሲስተር ንብረት እንደሚናገሩት ፖስትፒል በአፍ የሚወሰድ ባለሆርሞን የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ እንክብል ነው::                      ይህ የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ ዘዴ በአስገድዶ መደፈር ወቅት ወይም ባልተጠበቀ ሁኔታ በተከናወነ ጥንቃቄ በጎደለው የግብረስጋ ግንኙነት ሳቢያ ሊከሰት የሚችለውን ያልተፈለገ እርግዝና የግብረ ስጋ ግንኙነት በተፈጠረ በ72 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ለመከላከል የሚጠቅም ነው::

ፖስትፒል ባለነጠላ አካላዊ ቅመም የያዘ ሲሆን የተሠራውም በሴቶች አካል ውስጥ በተፈጥሮ ከሚመረተው ፕሮጀስትሮን ከተባለው አካላዊ ቅመም (ሆርሞን) ጋር ከሚመሳሰል ፕሮጀስቲን ከሚባል ንጥረ ነገር ነው:: እያንዳንዱ የፖስትፒል እሽግ በውስጡ ሁለት ባለ 0.75 ሚሊግራም ሌቮኖርጀስትሪል የተባሉ እንክብሎችን ይዟል::

ሲስተር ንብረት እንደሚናገሩት እርግዝናን የመከላከል አስተማማኝነቱ እንደ ተጠቃሚዎች አጠቃቀም ይወሰናል:: እንክብሉ ጥንቃቄ የጎደለዉ የግብረ ስጋ ግንኙነት በተፈጸመ በ72 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ መወሰድ አለበት::

አሁን ተሻሽሎ በወጣው መመርያ መሠረት ደግሞ እስከ አምስት ቀናት ይሠራል፤ ሆኖም ጊዜዉ እየጨመረ ሲሄድ የመከላከል አቅሙ እየቀነሰ ስለሚሄድ ተመራጩ ጊዜ በ72 ሰዓታት ውስጥ ቢወሰድ ነው::

የቤተሰብ አገልግሎት አስተባባሪዋ እንደሚገልጹት  ፖስትፒል በማስገደድ ወይም ባልተጠበቀ ሁኔታ በተከናወነ ጥንቃቄ በጎደለው የግብረ ስጋ ግንኙነት ሳቢያ ሊከሰት የሚችለውን እርግዝና ለመከላከል የሚወሰድ እንክብል እንጂ በዘላቂነት የሚወሰድ መደበኛ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ አይደለም::

ፖስትፒል ኤች አይ ቪን ጨምሮ ከማንኛውም ተላላፊ የአባላዘር በሽታዎች ስለማይከላከል ጥንቃቄ ያስፈልገዋል:: ፖስትፒልን ከመደበኛው የእርግዝና መከላከያ ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር፤ የግብረ-ሥጋ ግንኙንት ካደረጉ በኋላ መወሰዱ ነው።

በዘርፉ እስካሁን ብዙም ጥናት ባይደረግም እስካሁን ባለው ሂደት ግን እንክብሉን በመውሰድ  የሚከሰቱ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዳሉት ይታወቃል::

እነዚህም እንክብሉ በተወሰደ ከአንድ እስከ ሁለት ቀናት ውስጥ መጠነኛ የሆነ የደም መፍሰስ ሊከሰት ይችላል፣ የወር አበባ ከሚጠበቅበት ጊዜ ቀድሞ ወይም ዘግይቶ ሊመጣ ይችላል (የወር አበባ ጊዜ መዛባት)፣ ማቅለሽለሽ (ማስመለስ)፣ ከእምብርት በታች የሆድ ቁርጠት፣ የድካም ስሜት /የሠውነት መዛል/፣ የራስ ምታት፣ የጡት መደደር በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው::

ሲስትር ንብረት እንደሚናገሩት፤ መደበኛ የእርግዝና መከላከያን ከሚወስዱት መቶ ሴቶች ስምንቱ ላይ እርግዝና ሊፈጠር ይችላል፤ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያን ከሚወስዱት  መካከል ግን ከመቶው ሁለቱ ብቻ ናቸው ሊያረግዙ የሚችሉት። ፖስት ፒል በውስጡ ሲንተቲክ የተባለ ሆርሞን የያዘ ሲሆን እርግዝናን የሚከላከለው ደግሞ ውፃት (እንቁላል ከማህፀን የሚወጣበት) ወቅትን በማዘግየት ነው:: በመሆኑም ሴቶቹ እንክብሉን ሲወስዱ ውፃት ተከናውኖ ከሆነ በኋላ ጥንቃቄ የጎደለው ግንኙነት ከፈፀሙ እርግዝናን ላይከላከል ይችላል::

ይህ በእንዲህ እዳለ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ እንክብል ላይሠራበት የሚችልበት ዕድል መኖሩን ባለሙያዋ ይናገራሉ፤ ሰዓት አለመጠበቅ ወይም የሴቷ የሰውነት ክብደት በጣም ከፍተኛ ከሆነ ሴቶች ድንገተኛ እርግዝና መከላከያ ቢወስዱም ሊያረግዙ እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ እንክብል ከተረገዘ በኋላ ቢወሰድ ደግሞ ጽንሱን የማስወረድ ተጽዕኖን ሊያስከትል ወይም  የሚያመጣው ለውጥ ላይኖር እንደሚችል ሲስተር ንብረት አብራርተዋል::

ከድንገተኛ አስገድዶ መድፈር እና ግንኙነት ጋር ተያይዞ ሴቶች ፖስትፒል እንዲወስዱ ሲፈልጉ ደግሞ ድንገተኛ እርግዝና መከላከያ ሊያመጣ የሚችለውን ችግር በፋርማሲስቶች ወይም በሕክምና ባለሙያዎች መረዳት አንዳለባቸው ይገልፃሉ።

አንዲት ሴት ብትደፈር አልያም ድንገተኛ ግንኙነት ፈፅማ እርግዝና ቢፈጠር ወደ ውርጃ ልትሄድ ትችላለች፤ በተደጋጋሚ ውርጃ ሲፈፀም ደግሞ ለመሃንነት፣ ለፌስቱላ፣ ለማሕፀን መበሳት ዓይነት ዘላቂ ጠባሳ ያለው ችግር ልትጋለጥ ትችላለች:: በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለማስቀረት ነው ድንገተኛ እርግዝና መከላከያ እንክብሉ የሚሰጠው::

ፖስትፒል ተመራጭ ድንገተኛ አማራጭ ቢደረግም እንክብሉ በውስጡ ብዙ ሆርሞን ስላለው በተደጋጋሚ ከተወሰደ የሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ ችግር ያስከትላል:: ባለሙያዎችም በተደጋጋሚ ለሚመጡ ተጠቃሚዎች ዘላቂ የእርግዝና መከላከያ አማራጮችን እንዲጠቀሙ ማስገንዘብ ይገባቸዋል ብለዋል ባለሙያዋ::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ጥቅምት 4  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here