እኝህ ሰው የአፍሪካ እግር ኳስን ለማሳደግ ብዙ ለፍተዋል፤ ደክመዋል:: የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን እና የአፍሪካ እግር ኳስ ማህበርን የመሰረቱ፣ በፕሬዝዳንትነትም ለ15 ዓመታት ያገለገሉ ናቸው:: ወደ ታላላቅ የሥራ ኃላፊነቶች ከመምጣታቸው በፊት ለአንድ ክለብ ብቻ ታምነው ተጫውተው አሳልፈዋል:: በአሰልጣኝነታቸው ዘመን ደግሞ ብቸኛውን የመድረኩን ዋንጫ አሳክተዋል፡፡ ታላቁ የስፖርት ሰው በሀገራችን የእግር ኳስ ጫማ ተጫምተው የተጫወቱ የመጀመሪያው የእግር ኳስ ተጫዋችም ናቸው- ይድነቃቸው ተሰማ::
የታላቁ የስፖርት ሰው ታሪክ ከዚህ ይጀምራል:: ይድነቃቸው ተሰማ መስከረም 1 ቀን 1914 ዓ.ም በጅማ ከተማ ነው የተወለዱት:: ዕድሜያቸው ስምንት ሲሞላቸውም ከስፖርት ጋር መተዋወቃቸውን የታሪክ ማህደራቸው ያሳያል:: በትምህርታቸው ጎበዝ የነበሩት ይድነቃቸው በ1928 ዓ.ም ወደ ፈረንሳይ ሀገር ለመሄድ ከተመረጡት ሁለት ጎበዝ ተማሪዎች መካከል አንደኛው ነበሩ:: ይሁን እንጂ በጊዜው ጣሊያን ኢትዮጵያን በመውረሩ የፈረንሳይ ጉዟቸው ሳይሳካ ቀርቷል:: በዚህ ምክንያትም በ14 ዓመታቸው የያኔውን የአራዳ ልጆች በመባል የሚታወቀውን የሰፈር ቡድን የአሁኑን ቅዱስ ጊዮርጊስን መቀላቀላቸውን ታሪክ ያስረዳል:: ሁለገብ ስፖርተኛ የነበሩት ይድነቃቸው ተሰማ በአጭር ርቀት ሩጫ፣ በቡጢ እና በብስክሌት ስፖርትም ይወዳደሩ እና ይታወቁ እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል:: ነገር ግን ለእግር ኳስ ስፖርት ጥልቅ ፍቅር ስለነበራቸው ወደ እግር ኳሱ በማድላት በዘርፉ ዘመናቸውን አሳልፈዋል:: በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ለ23 ዓመታት ያህል በታማኝነት ተጫውተው አልፈዋል:: በፈረሰኞቹ ቤትም በአንድ የውድድር ዓመት በ47 ጨዋታዎች 43 ግቦችን በማስቆጠር እስካሁንም የክብረ ወሰኑ ባለቤት ናቸው::
ይድነቃቸው በወቅቱ በቀድሞው ሀንጋሪያዊው የእግር ኳስ ኮከብ ስም የኢትዮጵያው “ፕሽካሽ” ነበር የሚባሉት:: ምንም እንኳ በቁመታቸው አጭር ቢሆኑም በቴክኒክ ችሎታቸው ላቅ ያሉ እንደነበሩ ይመሰከርላቸዋል:: ምርጥ ኳስ የመግፋት ክህሎት ያላቸው፣ ጥሩ ቅብብሎችን የሚያደርጉ ተጫዋች ናቸውም ይባልላቸዋል:: ከ1940 እስከ 1944 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በተጫዋችነት አገልግለዋል:: በእነዚህ ስድስት ዓመታት ውስጥም 15 ጨዋታዎችን በማከናወን ሦስት ግቦችን ከመረብ አገናኝተዋል::
ከተጫዋችነት ከተገለሉ በኋላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን አሰልጥነዋል:: የብራዚል እግር ኳስ አድናቂ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ይድነቃቸው ተሰማ በአሰልጣኝነት ዘመናቸው በአፍሪካ አህጉር ታይቶ በማይታወቅ መልኩ አዲስ የአጨዋወት ዘይቤ ማስተዋወቃቸውም ይነገራል:: ታላቁ የስፖርት ሰው በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ በዘመናት የማይደበዝዝ የጎላ ሥራ የሰሩት ግን በተጫዋችነት እና በአሰልጣኝነት ዘመናቸው ብቻ አልነበረም:: ከተጫዋችነት እና ከአሰልጣኝነት ከተገለሉ በኋላ ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም እግር ኳስ እድገት ባበረከቱት አስተዋጽኦ ስማቸው ተደጋግሞ ይነሳል::
በ1936 ዓ.ም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንን በመመስረት በሀገራችን የክለቦች ውድድር እንዲጀመር አድርገዋል:: ከአራት ዓመታት በኋላም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፀሀፊ በመሆን ተመርጠዋል:: በዚህ ወቅትም የጨዋታ ሕጎችን እና ደንቦችን በመተርጎም፣ ሰራተኞችን በማሰልጠን እግር ኳሱን ለማሳደግ ብዙ ደክመዋል:: በ1953 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ስፖርት ኮንፌደሬሽን ፀሀፊ በመሆን ተመርጠዋል:: በተመሳሳይ በዚህ ዓመት ከእግር ኳሱም ባለፈ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴን መስርተዋል:: ሀገራችን ለውጪ የስፖርት ግንኝኑነቶች እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በሯን የከፈተችው በእርሳቸው የኃላፊነት ዘመን እንደነበረ ታሪክ ያስነብባል:: በሮም፣ በቶኪዮ እና በሞስኮ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድንን በመምራትም በታሪክ መዝግብ ስማቸው ሰፍሯል::
ከሀገራችን ባለፈም በአፍሪካ እግር ኳስ ማህበር በፕሬዝዳንትነት፣ በምክትል ፕሬዝዳንትነት እና በሌሎቹም በርካታ የሥራ ኃላፊነት ከ30 ዓመታት በላይ በብቃት እና በትጋት ሠርተዋል:: በዓለም አቀፍ ደረጃም በፊፋ የካፍ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ የዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል በመሆን ጭምር አቶ ይድነቃቸው አገልግለዋል:: በእነዚህ የኃላፊነት ዘመናቸውም በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የአፓርታይድ ሥርዓት በመዋጋት ረገድ ትልቅ ሚና ነበራቸው::
ደቡብ አፍሪካ ከ1962 እስከ 1991 እ.አ.አ በአፓርታይድ አገዛዝ ምክንያት በአፍሪካ ዋንጫ ላይ እንዳትሳተፍ እገዳ የተጣለባትም በእርሳቸው ግፊት እንደነበረ ታሪክ ይነግረናል:: በአሥራ ዘጠኝ ዘጠናዎቹ መጀመሪያ ላይ ሀገሪቱ የአፓርታይድ አገዛዝን ከገረሰሰች በኋላ የአፍሪካ እግረ ኳስ ማህበር አባል መሆን ችላለች፡፡ በተጨማሪም ይደነቃቸው በዓለም ዋንጫው ላይ የሚሳተፉትን የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድን ቁጥር በማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል::
እ.አ.አ በ1982 ስፔን በአስተናገደችው የዓለም ዋንጫ የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ከአንድ ወደ ሁለት ከፍ እንዳለ የሚታወስ ነው፡፡ በተጨማሪም አፍሪካውያን ዳኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ጨዋታወችን መምራት አይችሉም እያሉ አውሮፓውያን ሲሳለቁ መልስ ከሚሰጡት ግንባር ቀደሙ ሰው ነበሩ:: በካፍ እና በፊፋ በርካታ ኃላፊነቶችን በመሸከም ለእግር ኳሱ እድገት ትልቅ አሻራቸውን አስቀምጠው ያለፉት ይድነቃቸው ተሰማ የአፍሪካ እግር ኳስ አባት እና የጅብራልታሩ አለት የሚል ስያሜም ተሰጥቷቸዋል:: እንኳንስ ኢትዮጵያውያን እና አፍሪካውያን ይቅሩና በስራቸው የሚያውቋቸው ስለሳቸው ከመዘመር ወደ ኋላ አይሉም ነበር::
ፊፋን ለረጅም ዓመታት በፕሬዘደንትነት የመሩት ሴፍ ብላተር ምስጋና ከማቅረብም በላይ አሞካሽተዋቸዋል፡፡ “ስለ ኢትዮጵያ ካነሳሁ አይቀር እ.አ.አ በ1976 ለፊፋ መሪነት ስወዳደር እገዛ ያደረጉልኝ ይድነቃቸው ተሰማ ነበሩ፡፡ሁልጊዜም ላወድሳቸው እፈልጋለሁ:: የአፍሪካ ስፖርት አባት ሊባሉ የሚገባቸው ናቸው’’:: በወቅቱ የነበሩት የውጪ ጋዜጦች እና መጽሔቶች ለአፍሪካ እግር ኳስ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ እና ቁርጠኝነታቸው ብዙ መጣጥፎችን አስነብበዋል::
ከአማርኛ በተጨማሪ እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያንኛ፣ ሰዋሂሊኛ እና አረብኛን አቀላጥፈው የሚናገሩት ይድነቃቸው የእግር ኳስ ተጫዋች፣ አሰልጣኝ፣ የእግር ኳስ አስተማሪ እና የስፖርቱ መሪ ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል፡፡ ታላቁ የስፖርት ሰው በሀገራችን በስፖርቱ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ተገቢውን ክብር እና እውቅና ባይሰጣቸውም በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ ግን በስማቸው ስቴዲየም ተሰይሟል፡፡ የሞሮኮ እግር ኳስ ፌደሬሽን በካዛብላንካ የሚገኘውን ስቴዲየም በእርሳቸው ስም ስያሜ ሰጥቶታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በካፍ (CAF) በየ ዓመቱ በሚዘጋጁ የኮከቦች ሽልማት ዘርፍ ላይ በይድነቃቸው ተሰማ ስም ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች ሽልማት መስጠት ተጀምሯል፡፡
ይህ ሽልማት ዘንድሮ ስድስተኛ ዓመቱን ይዟል:: ታላቁ የእግር ኳስ ሰው ይድነቃቸው ተሰማ አሁን ህይወታቸው ካለፈ 38 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በሀገራችን እና በአፍሪካ የስፖርት ዘርፍ ለፈጠሩት ትልቅ መነቃቃት አስመልክቶ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በሚዘከሩበት በዚህ ወር የእግር ኳስን አርበኛ እኛም እንዲህ ዘክረናችዋል፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም