ባለፈው ሳምንት ክፍል አንድ ዝግጅት ስለገሞራዎች ሀገር ኤል ሳልቫዶር የተመለከተ አመሰራረቷን እና ከቅኝ ግዛት እስከ ነፃነት ድረስ ያለውን ታሪክ ለማሳየት ሞክረናል። በሁለተኛው ክፍል ደግሞ ተከታዩን ይዘን ቀርበናል።
ላ ማታንዛ
ላ ማታንዛ የተባለው ጅምላ ግድያ ከተፈፀመ በኋላ በነበሩት ከ30 ዓመታት በላይ ጊዜያት ሀገሬው የኤል ሳልቫዶር ገበሬ መከራ አልተሻሻለም፤ ይባስ ነበር እየከፋ የሄደው። የሀብት እና የመሬት ስርጭት ልዩነቱም በጣም የጨመረበት ጊዜ ነበር። በ1950ዎቹ ግብርናው የተስፋፋበት እና ኢንዱስትሪውም ያደገበት ነበር። ይሁን እንጂ የሕዝቡ ገቢ ከድህነት ወለል በታች እንደነበረ እና ሰፊው ሕዝብ በቂ የመጠጥ ውሃ፣ የጤና አገልግሎት፣ እና የተሟላ የስራ ቅጥር አያገኙም ነበር።
የሕዝብ ንቅናቄ
በ1960ዎቹ ተማሪዎች፣ የሰራተኞች ቡድኖች፣ የማህበረሰብ አባላት እና የሀይማኖት መሪዎች ፍትሃዊ ሕብረተሰብ ለውጥ እንዲኖር ለመጠየቅ ተደራጁ። ለሁለት ያህል ጊዜ ተራማጅ እጩዎች ለፕሬዝደንት ተመርጠው ቢመረጡም በተበላሸ የምርጫ አሰራር ምክንያት ወደ መንግሥት ያስጠጋቸው አልነበረም።
በርካታ ሰላማዊ ሰልፎች ቢካሄዱም በኤልሳልቫዶር የመንግሥት ኃይሎች በቀጥታ እየተኮሱ በርካቶችን ገደሉ። በዚያ አላልቅ ብሎ ገዳይ ቡድን ተደራጅቶ ዜጎችን እያሳደዱ መግደሉን ቀጠሉበት እናም መላው ሕዝብ ተሳደደ፣ ተሸበረ።
የርስ በርስ ጦርነት
ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የቀድሞ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ እና የፋብሪካ እና የእርሻ ሰራተኞች የገጠሩን ማህበረሰብ ማደራጀት እና የትጥቅ ትግል ውስጥ ማስገባት የጀመሩበት ሁኔታ ተፈጠረ። ድርጅቱን በ1910ሮቹ የሳልቫዶርን ሰራተኞችን እና ገበሬዎችን ባደረጀው በ ላ ማታንዛ ወቅት በተገደለው ታጋይ ነገረ ፈጅ ስም ፋራቡንዶ ማርቲ ግንባር ለብሔራዊ ነፃነት የሚል ስያሜ ሰጥተውት ነበር ትግላቸውን ያጦፉት።
ግንባሩ ሁሉን የሕብረተሰብ ክፍል ያካተተ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት እንዲመሰረት ይሹ ነበር። ከዚህ በፊት ግን በፖሊስ እና በወታደሩ የሚደረገው አፈና የግድ መቆም መቻል ነበረበት። ስለሆነም ለአፈናዎች እና ለግድያዎች ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ እና እንዲቀጡ ማድረግ የግንባሩ መሀከለኛ ጥያቄ ነበር። እነዚህ እስኪከናወኑ ድረስ በፍጹም ትጥቃቸውን እንደማያወርዱ ወስነው ትግላቸውን አፋፍመው አልበገሬነታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
ይህ በሀገሪቱ ከአስር ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ ሀገሪቱ በከፋ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንድትገባ አድርጓል። አሜሪካ ለመንግሥት ገንዘብ፣ ወታደራዊ ቁሳቁስ እና ወታደራዊ ልምምድ በመስጠት ድጋፍ አድርጎ ነበር። አንድ ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝብ ማለትም አንድ አምስተኛው ሕዝብ ሀገሩን ለቆ ለመሰደድ ተገድዷል። እስከ 75,000 ሳልቫዶራዊያን ተገድለዋል። በሺዎቹ የሚቆጠሩት ደግሞ ቶርቸር ተደርገዋል። በጦርነቱ መጨረሻ በሀገሪቱ የሚኖረው ሕዝብ በግጭቱ ወታደራዊ ቃጠና እንዲሆን እና እንዲሸበር ሆኗል።
አሜሪካስ ዎች የተሰኘ ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ቡድን በ1977 ዓ.ም ላይ እንዳወጣው ሪፖርት አብዛኛው በተለይ በገጠር የሚኖረው ሕዝብ የታጣቂዎች መሸሸጊያ ተደርጎ ይቆጠር ስለነበር ለተለያዩ ወታደራዊ ጥቃት ሰለባ ሆኗል። በመሆኑም ሆን ተብሎ ቀየውን እየለቀቀ እንዲሰደድ ባለመ መልኩ በሕዝቡ ላይ የሚፈፀመው ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃንን ለሞት ዳርጓል። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኤል ሳልቫዶሪያውያን ወደ አሜሪካ፣ ወደ ጎረቤት ሀገር ሁንድራስ እና ሜክሲኮ በስደት እንዲጎርፉ አስገድዷል፤ እስከ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝብ ደግሞ እዚያው በሀገሪቱ ውስጥ ለስደት ተዳርጓል። በጥቅሉ ሩብ የሚሆነው የኤል ሳልቫዶር ዜጋ ለደህንነቱ ሲል አካባቢ ቀየውን እንዲለቅ ተገድዶ አሳር መከራውን ያየበት የርስ በርስ ግጭት ነበር አስተናግደው ያለፉት።
የተደራጁ ወንበዴዎች
በእንቅርት ላይ… እንዲሉ አበው አንዴ በቅኝ ገዠው ዱላ ከዚያም ለጥቂት ከበርቴዎች ጥቅም በቆመው ወታደራዊው ስርዓት ለዓመታት በገዛ ቀየው እንደባሪያ የማቀቀው፣ በርስ በርስ ጦርነቶች የደቀቀው መከረኛው የኤልሳልቫዶር ሕዝብ እንደገና ወደ ሌላ ሰቆቃ ገብቷል። የጋንጎች ዘመን በመባል ይታወቃል። ለብዙ አስርት ዓመት የመካከለኛው አሜሪካ ትንንሽ ሀገራት የወንጀለኝነት ውሃ ልክ የሆኑ ማራ ሳለቫትሩቻ (MS13) እና የ18ኛው ጎዳና (Barrio 18) የተባሉ ሁለት ቡድኖች ተደራጅተው ነበር። በመላ በድሃው ማህበረሰብ ውስጥ ተተክለው የከተማ ነዋሪውን አስገድዶ ገንዘብ በማስከፈል እና በመግደል ያሸብሩት ነበር። የሀገሪቱ ጎዳናዎች በጋንጎች የተሞሉ እና በሕዝቡ ላይ ያሻቸውን ሲያደርጉ ሀይ የማይባሉበት አስከፊው ዘመን ነበር። በየቀኑ ከ200 በላይ ንፁሃን ዜጎች ተገድለው መገኘት አዲስ አልነበረም። ህዝቡ በፍርሃት እና በሰቀቀን ለመኖር ተገደደ፤ ዝርፊያው፣ እገታው ከአቅም በላይ ተስፋፋ። ሰውነታቸው አስፈሪ በሆኑ ንቅሳቶች በተዝጎረጎረ አደገኛ ወንበዴዎች የተማረረው ሕዝብ አንገቱን ደፍቶ መኖር ካልሆነም እግሩ ወዳደረሰው ጎረቤት ሀገራት መሰደድ እጣፋንታው ሆኖ በመከራ ውስጥ አለፈ።
የተለያዩ የሀገሪቱ መንግሥታት የጋንጎቹን ሰንሰለት በመበጣጠስ እፎይታ ለማምጣት መጠነ ሰፊ ጥብቅ ፖሊሲዎችን ቀርፀው ለመተግበር ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። የጋንግ ችግሩ በሀገሪቱ ተንሰራፍቶ በቀጠለው እኩልነት አለመኖር፣ ብጥብጥ እና ሙስና የጋንግ ችግሩን ወደ ከፋ ደረጃ አደረሰው።
በ2000ዎቹ ዘመን የኤልሳልቫዶር ኢኮኖሚ ማሽቆልቆሉን ቀጠለ። የሀገሪቱ ወጣቶች አማራጭ ስላልነበራቸው የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጥቅሞችን ለማግኘት ሲሉ የወንበዴዎቹን ቡድን ተቀላቀሉ፡፡
የቡክሊ ዘመን
አዲሱ ፕሬዚደንት ናይብ ቡኩሊ ችግር ውስጥ የገባች ሀገሩን ከገባችበት አዘቅት ለማውጣት ስልጣን ከያዘበት ማግስት ጀምሮ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፀድቆ እንቅስቃሴ ጀምረ። ይህም በተለይ በየጎዳናው በነፃነት የሚንቀሳቀሱት የጋንግ ቡድኖች የ87 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ጥቃት መፈፀማቸውን አስታኮ በወንበዴ ቡድኖቹ ላይ ሙሉ ጦርነት አወጀ።በዚህ ስልጣን ተጠቅመው ወዲያውኑ በሺዎቹ የሚቆጠሩ ጋንግስተሮችን በስፋት በማደን ማሰር ጀምረዋል። ወዲያውኑ በወራት ውስጥ በመለቃቀም ሰንሰለቱን መስበር ችሏል። ሀገሪቱም ከነበረችበት ችግር ወጥታ አሁን በዓለማችን በሰላሟ ተመራጭ መኆን የቻለች ሀገር ሆናለች።።
ይቀጥላል…..
(መሠት ቸኮል)
በኲር የሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም