የገሞራዎች ምድር

0
191

ከሰላማዊ ውቅያኖስ ዳርቻ የመካከለኛው አሜሪካ አካል የሆነች አንድ በ21ሺህ ስኩዌር ኪሎሜትር መሬት ላይ የተመሰረተች አነስተኛ ሀገር አለች። በየዘመኑ የፈነዱ የብዙ እሳተገሞራዎች ውጤት ስትሆን እስከዛሬም ንቁ የእሳተጎመራ ክስተቶች የሚስተዋሉባት፣ የደጋግ፣ ሰው አክባሪ፣ ታታሪ እና ጀግና ብርቱ ሕዝብ መኖሪያ ይባልላታል፣ ኤል ሳልቫዶር።

ኤልሳልቫዶርን የቆረቆሯት የመጀመሪያ ሰፋሪዎች ፒፒል የተባሉ ቀይ ሕንዳውያን እንደነበሩ እና ሀገራቸውንም ኩዝካትላን  ብለው ይጠሯት እንደነበር ይነገራል። ይሁን እንጂ ከፒፒሎች ቀደም ብለው ለዓለማችን የጥንት ስልጣኔ አሻራቸውን ያሳረፉት ማያውያን ይኖሩ  ነበር የሚሉ እና የለም አዜቲካውያን ናቸው የሚሉ ሁለት የታሪክ ተመራማሪዎች ሙግት አለ። ይሁን እና በአርኪዮሎጂ ምርምር እንደታወቀው በ2000 ዓ.ዓ አካባቢ ከማያ የሆኑ ኦልሜኮች በምራባዊው ክፍል ባሉት ከተሞች ይኖሩ እና ይናገዱ ነበር። በዚያም የማያውያን በርካታ የስልጣኔ አሻራዎች በኤልሳልቫዶር ትተው ማለፋቸውን የሚመሰክሩ ቅርሶች አሁን ድረስ ይታያሉ። ኦልሜኮችን ተከትለው ፒፒሎች ወደ ኤልሳልቫዶር ማቅናታቸው በሀገሪቱ አዲስ የታሪክ ምእራፍ ሆኖ ይነገራል።

በአስራ አንደኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ፒፒሎች ከሜክሲኮ ተሰድደው አልሳልቫዶር ገቡ እና  እንደ ማያውያን አይነት የእርሻ ሕይወትን ጀመሩ። አዲሷን መኖሪያቸውን የጌጣጌጦች ምድር እንደማለት “ኩዝካትላን” ብለው በመሰየም በተለያዩ አውራጃዎች ከፋፍለው አስፋፏት።  የማያውያኑን የስልጣኔ መስመር በማስቀጠል የላቀ ስራ እንደከወኑ የሚነገርላቸው ስልጡኖቹ ፒፒሎች በግብርና ስራዎቻቸው እና በስርዓተ አምልኮዎቻቸው የማያውያኑን እና የአዜቲኮቹን የዘመን ስሌት ይጠቀሙ ነበር። ፒፒሎች ውስብስብ የሒሳብ ስርአቶችን ይፈፅሙ የነበሩ፣ በተለየ መልኩ የሸክላ፣ የሽመና፣ የድንጋይ ቅርፃቅርፅ፣ እንዲሁም በወርቅ እና በብር ስራዎች የተካኑ ነበሩ። ከአስራ አምስት በላይ የሆኑ ሰብሎችን የሚያመርቱ ብርቱ ገበሬዎችም ነበሩ።

የስፔን ወረራ

ለአራት መቶ ያህል ዓመታትን ሀገራቸውን እየገነቡ መሰረቷን እያጠነከሩ ከኖሩ በኋላ ፒፒሎች በ16ኛው ክፍለ ዘመን ላይ አንድ ታሪክ ቀያሪ ክስተት ገጠማቸው። በዘመኑ አዲስ ዓለማትን እያሰሱ በመውረር ተግባር ላይ የተጠመዱት ስፔናውያን በ1516 ዓ.ም ፔድሮ ዲ አልቫራዶ እና ወንድሙ ዲያጎ በሚመሩት ወራሪ ኃይል የጥንቷን ኩዝካትላንን ወረሯት። የስፔናውያኑ ወረራ በፒፒል ሕዝብ ሕይወት ላይ መሰረታዊ ለውጦችን ማስከተሉ አልቀረም። ስፔናውያኑ ወራሪዎች እግራቸው በዚህች ምድር ከረገጠ ጊዜ ጀምሮ የሕዘቡን መሬት ቀምተው መያዝ ጀመሩ። ይህ ብቻ አይደለም በፒፒሎች ላይ የጅምላ ግድያ፣ ቤተ አምልኮታቸውን እና አማልክቶቻቸውን የማውደም ወንጀል ፈፀሙ፤ ሕዝቡን በግዳጅ ወደ ባርነት አስገቡት። አልበቃ ብሎ ሴቶቹን በመድፈር የስሜት መደሰቻ እና የወራሪዎቹን ዲቃላ እንዲወልዱ አደረጓቸው።

ኩሩው የኤልሳልቫዶር መስራች የፒፒል ሕዝብ ግን ይህን የስፔናውያኑን እኩይ ድርጊት እያየ ዝም ይል ዘንድ ባህላቸው ማንነታቸው አልፈቀደም። ምንም እንኳ ወራሪው የስፔን ሰራዊት ጥቂት ግን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀ ቢሆንም በስልት እና በብቃት አሸንፈው ከምድራቸው ለመጠራረግ መራር ትግል ጀመሩ። ለአስራ አምስት ዓመታት ያህል በጀግንነት ወራሪውን ጠላት ተፋለሙ። ስፔን ኤልሳልቫዶርን በወረሩበት በመጀመሪያው ሀምሳ ዓመታት ውስጥ የፒፒል ሕዝብ ከ500ሺህ ወደ 75ሺህ እስኪመናመን ድረስ በወራሪው ጭካኔ እንደተጨፈጨፉ የታሪክ አዋቂዎች ይስማማሉ። ከጅምላ ጭፍጨፋው በተጨማሪም በሰፋፊ የእርሻ ማሳዎች ላይ በአስከፊ ሁኔታ እንዲሰሩ በመገደዳቸው ምክንያት በርካታ ሕዝብ በሕመም ያልቅ ነበር።

በዚህ አካባቢ ሕይወት ውስጥ የተከናወነው አንድ ወሳኝ ታሪካዊ እውነታ አሁን ድረስ በሀገሪቱ እየተከወነ ይገኛል። በስፔን ወረራ ወቅት ሰፊ የሆነው የሀገሪቱ መሬት ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በታጠቁ አናሳዎች እጅ ውስጥ መግባት፣ እና መሬታቸውን የተቀሙ ሕዝቦች ቀጣይነት ያለው የትግል እንቅስቃሴ በአካባቢው ሕይወት ውስጥ የተከሰተ አሁን ድረስ እየሰራ ያለ ዋነኛ ታሪካዊ እውነታ ነው።

የ14ቱ ቤተሰቦች መሬት

በ1800ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ግማሹ የኤል ሳልቫዶር መሬት በ14 ቤተሰቦች እጅ ቁጥጥር ውስጥ ገብቷል። በዚህ የተነሳ መላው የኤል ሳልቫዶር ሕዝብ መሬቱ ተነጥቆ ለከበርቴዎች ሲሰጥ የተረፈለት እድል በገዛ መሬቱ ለግፈኞቹ የከበርቴው ቤተሰቦች በጉልበት ማገልገግ ወይም ባሪያ ለመሆን ተገደዱ። ከራሳቸው ጥቅም ውጭ ለመላው ሳልቫዶራውያን ወገኖቻቸው ደንታ የሌላቸው ከበርቴዎች ከሕዝቡ በተቀማው መሬት ላይ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆኑ እንደ ሸንኮራ፣ ቡና፣ እና ጥጥ በማምረት ላይ ተጠመዱ። ሕዝቡ ያመርታቸው የነበሩ ሕይወቱን የሚደጉሙ ከአስራ አምስት በላይ የምግብ ሰብሎችን መመረት እንዲቆም ተደረገ። የኤል ሳልቫዶር መሬት ለሀገሩ ሳይሆን ለሌሎች  የሚላኩ ምርቶችን እና ለከበርቴው ጥቅም ያመርት ነበር።

ነፃነት

በ1813 ዓ.ም ኤል ሳልቫዶር ነፃነቷን ከስፔን ብትረከብም በሰፊ የእርሻ ማሳ ላይ የተመሰረተው ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ቀጠሎ ነበር። ዐብዛኛውን የሀገሪቱን መሬት እና የመንግስት ስልጣን የተቆጣጠሩት ያለፈው የስፔን መንግሥት ርዝራዦች ነበሩ።

ከ1872-1882 ዓ.ም ድረስ ባሉት ዓመታት የነበረው የኤልሳልቫዶር መንግሥት የወል መሬትን ከገበሬው ወሰደ እና ለቱጃሮቹ ሰጠ።  በርካታ አልሳልቫዶራውያን መሬታቸውን ለመተው እና በየፋብሪካው ምንደኛ ሆነው ሕይወታቸውን ለመግፋት ተገደዱ።

በ1920ዎቹ ታላቅ የኢኮኖሚ ቀውስ ኤልሳልቫዶርን መትቷል።

ይቀጥላል…..

(መሠት ቸኮል)

በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here