የገበያ ማእከሉ መስህብ

0
65

በኢስቶኒያ ሃብኔሚ ከተማ ቪሚሲ የገበያ ማእከል በወለሉ መሀል የሚገኘው ግዙፍ ቋጥኝ ለግብይት ጐራ የሚሉ በርካታ ሰዎችን በመሳብ ታዋቂ ሊሆን መቻሉን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ  አስነብቧል፡፡

 

የገበያ ማእከል  በርካታ ነገሮች የሚገኙበት ቦታ ነው- ግዙፍ ቋጥኝ ግን  አይታሰብም፡፡ በሃብኔሚ ከተማ ቪሚስ የገበያ ማእከል ግን የዙሪያው ስፋት 22 ሜትር፣ ቁመቱ 6 ሜትር የተለካ ቅርፀ አልባ ግዙፍ ቋጥኝን በወለሉ መሀል ይዟል። ጐብኚዎችን በመሳብም ታዋቂነትን አግኝቷል፡፡ ግዙፉ ቋጥኝ የገበያ ማእከሉ ባለቤት ግንባታ ከመጀመራቸው አስቀድሞ ለዘመናት እዛው የነበረ ነው፡፡ ምናልባትም ከ10,000 ዓመታት በፊት፡፡

 

በ2014 እ.አ.አ የገበያ ማእከሉ ግንባታ ሲጀመር የግንባታ ሰራተኞች ዓለቱን በ “ደማሚት” ፈረካክሰው ሊያስወግዱት ይወስናሉ፤ የአካባቢው ኗሪዎች ግን መፈረካከስ የእንደሌለበት ሞገቱ።  ውሎ አድሮ የዓለቱ ሁኔታ በባለሙያዎች ሲጠና በበረዶው ዘመን ከቦታ ቦታ ተገፍቶ በረዶው ሲቀልጥ አሁን ባለበት መገኛዉ ተተክሎ የቆየ ሳይሆን እንደማይቀር ግምታቸውን አስረድተዋል፡፡

 

የስነምድር  ሳይንስ ባለሙያዎች በበኩላቸው ዓለቱ ስለቀደምቱ የበረዶ ዘመን ፍንጭ የሚሰጡ ማስረጃዎች ሊገኙበት እንደሚችል ነው ድምዳሜ ላይ የደረሱት፡፡ ቋጥኙ ባለበት ቦታ ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባ ቅርስ መሆኑን በማስረዳትም ባለሀብቱ የግንባታ አማራጭ ሊወስዱ እንደሚገባ፣ የከተማዋ ባለስልጣናትም እንደሚደግፏዋቸው ቃል ይገባሉ፡፡

 

ከዚያም የማእከሉ ባለቤት ባለሙያዋችን አማክሮ፣ ያወጣውን ወጪ አስልቶ ዘመናትን ያስቆጠረው ግዙፍ ዓለት ለስነምድር ጥናት እና ምርምር የሚኖረውን አበርክቶ  በማጤን ቋጥኙ   ሳይነካ የገበያ ማእከሉን ገንብቶ አጠናቋል፡፡

ግዙፉ ቋጥኝ በጥንቃቄ ባለበት ወደ ማእከሉ ጐራ በሚሉ ደንበኞች የሚፈለጉ ምርቶች ማሳያ  ዳራም ሆኗል፡፡ ከሁሉም በላይ ስእል እና ቅርፃቅርጽ የመሳሰሉ የጥበብ ውጤቶችን በላዩ ላይ በጥንቃቄ በማስቀመጥ የማሳያ ቦታ ሊሆን መቻሉም ነው የተገለጸው።

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሐምሌ 21  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here