የገጠር መሬት የካሳ አከፋፈል

0
216

አርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ ለኑሮው ዋስትና የሆነውን መሬት በነፃ የማግኘት መብት እንዳለው በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀፅ 40 ከንዑስ አንቀፅ 4 እስከ 8 ሰፍሯል፡፡ ይሁንና አርሶ አደሩ የመሬቱ ባለይዞታ የመሆን እና ያለበቂ ምክንያት ያለመነቀል መብት ቢኖረውም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህ ሲሆን ግን ከይዞታው የሚነሳው ሰው በቅድሚያ ተመጣጣኝ ካሳ የማግኘት ሕገ መንግስታዊ መብቱ ተከብሮለት ሊሆን እንደሚገባ  የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ያመላክታሉ፡፡

አርሶ አደሮች ከይዞታቸው የሚነሱበት በቂ ምክንያት ባለ ጊዜ መሬቱን በማልማት ላደረጉት ቋሚ መሻሻል፣ በመሬቱ ላይ ተክለው እና ኮትኩተው ላፀደቁት ቋሚ ተክል እና ማሳቸውን ለሸፈኑት ሰብል በቂ ካሣ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ እና ዋስትና አላቸው፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 (8) መርህ ተግባራዊ ለማድረግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 455/97 አንቀፅ 7 “የካሳ መሠረት እና መጠን”  እንዲሁም በአንቀፅ 8  “የማፈናቀያ ካሳ” በሚሉ ሁለት ዓይነት የካሳ ክፍያ አፈጻጸም ሥርዓቶች እንዳሉ ተደንግጓል፡፡ እነዚህን ሁለት ድንጋጌዎች  ኢትዮጵያ የምትከተለውን የካሳ አከፋፈል ሥርዓት በግልፅ ለመረዳት ያስችላሉ፡፡

በአንቀፅ 7 መሠረት የካሳ መነሻ ሆኖ የሚወሰደው እንዲለቅ በሚመለከተው አካል የተወሰነበት ባለይዞታ በመሬቱ ላይ ለሚገኘው ንብረት እና በመሬቱ ላይ ላደረገው ቋሚ ማሻሻል የሚከፈል ካሳ ነው፡፡ በመሬት ላይ ለተደረገ ቋሚ መሻሻል የሚከፈለው ካሳ መሠረቱ በመሬቱ ላይ ለዋለው ገንዘብ እና ለጉልበት ዋጋ የሚተካ የካሳ መጠን ነው፡፡

ባለይዞታው እንዲለቅ የተደረገውን መሬት መልሶ በማልማት አገልግሎት ለመስጠት የሚችል በሚሆንበት ጊዜ  ንብረቱን ባለበት ሁኔታ የሚተካ ካሳ እና በመሬቱ ለተደረገ ቋሚ መሻሻል ለወጣ ገንዘብ እና የጉልበት ዋጋ በካሳ መልክ ከሚከፈለው በተጨማሪ የንብረቱ ማንሻ፣ ማጓጓዣ እና መልሶ ለመትከል የሚጠይቀው ወጪ ይሸፈንለታል፡፡ ይህ ማለት ግን ለሁሉም ሰው ከይዞታው በመልቀቁ ምክንያት የሚከፈል ሳይሆን  እንደየ ሁኔታው እና የንብረቱ ዓይነት እየታየ የሚከፈል ካሳ ነው፡፡

የገጠር መሬት የካሳ አከፋፈል

በቋሚነት የሚለቅ የገጠር መሬት ባለይዞታ ባለፉት ዓምስት ዓመታት  ያገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ በዐሥር ተባዝቶ ከዚህ ላይ ደግሞ የቋሚ ማሻሻያ ገንዘብ እና የጉልበት ዋጋ ተደምሮ ወይም ባለፉት አምስት ዓመታት ያገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ በዐሥር ተባዝቶ ከዚህ ላይ  ንብረቱ ባለበት ሁኔታ መተኪያ፣ የቋሚ ማሻሻያ ገንዘብ እና የጉልበት ዋጋ፣ የንብረቱ ማንሻ፣ ማጓጓዣ እና መልሶ መተኪያ ወጪ ተደምሮ የሚሰጥበት የካሳ አከፋፈል ቀመርን የሚከተል ነው፡፡

በሌላ በኩል ለተወሰነ ጊዜ ከገጠር መሬት ይዞታው ለሚለቅ ተፈናቅሎ የሚቆይበት ዓመት፣ ንብረቱ ባለበት ሁኔታ መተኪያ፣ የቋሚ ማሻሻያ ገንዘብ እና የጉልበት ዋጋ ወይም ያገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ፣ ንብረቱ ባለበት ሁኔታ መተኪያ፣ የቋሚ ማሻሻያ ገንዘብ እና የጉልበት ዋጋ፣ የንብረቱ ማንሻ፣ ሟጓጓዣ እና መተኪያ ተደምሮ ይህም ባለይዞታ ወይም ለወል መሬት ባለይዞታዎች (Holders of Common land) እንዲለቅ ከመደረጉ በፊት በነበረበት አምስት ዓመታት ካገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ   ጋር ተባዝቶ ካሳው ይሰራለታል፡፡

ሕጉ ለተወሰነ ጊዜ የሚደረግ ከይዞታ መልቀቅን በተመለከተ ለቋሚ መልቀቅ ከተከተለው ስሌት ጋር ሲታይ ከተወሰነ የብዜት መሰረት (base) ለውጥ ውጨ ሌላ ልዩነት ባይኖረውም ለቋሚ መልቀቅ ከሚከፈለው ካሳ መብለጥ እንደሌለበት የካሳ ክፍያው ጣሪያ ገድቦታል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለውም ለተወሰነ ጊዜ የሚደረግ መልቀቅ በአንቀፅ 8(1) ባለይዞታው ከመሬቱ ለቆ የሚቆይበት ጊዜ ከ10 ዓመት በላይ ከሆነ ለተወሰነ ጊዜ ከገጠር መሬት ይዞታ መልቀቅ መሆኑ ቀርቶ እንደ ቋሚ ከገጠር መሬት ይዞታ መልቀቅ ይቆጠራል፤ የካሳ አከፋፈሉም በቋሚ መልቀቅ አከፋፈል ሥርዓት ይሆናል፡፡

ሕጉ ከእነዚህ የካሳ አከፋፈል ስሌቶች በተጨማሪ አንድ ሰው ካለው የገጠር መሬት ይዞታ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል እንዲለቅ በሚደረግበት ጊዜ ሌላ አማራጭ የካሳ አከፋፈል ሥርዓትን በአንቀፅ 8(3) ደንግጓል፡፡ ይህም ተመጣጣኝ ገቢ የሚያስገኝ፣  በቀላሉ ሊታረስ እና ምርት ሊያስገኝ የሚችል ተተኪ መሬት እና መሬቱን እንዲለቅ ከመደረጉ በፊት በነበሩት አምስት  ዓመታት የሚያገኘውን አማካይ ዓመታዊ ገቢ ያህል በካሳነት እንዲከፈለው በሕጉ ተጠቅሷል፡፡

ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ከይዞታቸው የሚፈናቀሉትን  የካሳ አከፋፈል በተመለከተ በቋሚነት ለሚለቅ በመሬት ላይ ለሚገኘው ንብረት የተደረገ ቋሚ መሻሻል ካለ ለዚህ የተደረገን ወጪ እና እንደየ ሁኔታው የንብረት ማንሻ፣ ማጓጓዣ እና መልሶ መተኪያ ወጪን የሚሸፍን ካሳ እና ከዚህ በተጨማሪ እንደየ ሁኔታው የሚከፈል የመፈናቀያ ካሳ የመክፈል ሥርዓትን (compensation schem) የያዘ ነው፡፡

የሰብል ካሳ አተማመን

ሕጉ ሰብሉ ለመሰብሰብ ካልደረሰ  ሰብሉ ሲደርስ ሊሰጥ የሚችለውን የምርት መጠን እና ምርቱ ሊያወጣ ይችል የነበረውን የአካባቢውን የወቅቱን የገበያ ዋጋ መሰረት በማድረግ እንደሆነ ደንግጓል፡፡ ሰብሉ ለመሰብሰብ የደረሰ ከሆነ ደግሞ ባለ ንብረቱ በካሳ ክፍያ ፋንታ በአዋጁ አንቀጽ 4   መሰረት በተሰጠው የጊዜ ገደብ /በ90 ቀን/ ውስጥ ሰብስቦ መውሰድ ይችላል፡፡

የቋሚ ተክል ካሳ አተማመን

ስሌቱ ተክሉ ፍሬ መስጠት ካልጀመረ በሚገኝበት ደረጃ ለማድረስ የሚያስፈልገውን ወጪ ግምት በማስላት ይሆናል፡፡ ቋሚ ተክሉ ፍሬ ለመስጠት የጀመረ ከሆነ ደግሞ ተክሉ በአንድ ዓመት የሚያስገኘውን ምርት በወቅቱ ካለው የአካባቢው የገበያ ዋጋ ጋር በማባዛት እንዲሁም የመሬት ቋሚ ማሻሻያ ወጪን በመደመር ይሆናል፡፡

የዛፍ ካሳ አተማመን

የሚሰላውም በዛፋ የዕድገት ደረጃ ላይ ተመስርቶ የወቅቱን የነጠላ ወይም የካሬ ሜትር ዋጋ በማውጣት ይሆናል፡፡ ባለንብረቱ በካሳ ክፍያ ፋንታ በአዋጁ አንቀጽ 4 መሠረት በተሰጠው የጊዜ ገደብ በ90 ቀናት ውስጥ ዛፉን ከመሬቱ አንስቶ መውሰድ ይችላል፡፡

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here