የገፀ ምድር መሀንዲሶቹ

0
93

እንስሳት ገፀምድር ወይም መልካዓምድርን በመቅረፅ ረገድ የላቀ ሚና ያላቸው ተፈጥሯዊ መሀንዲሶች መሆናቸውን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አበቅቶታል፡፡

በለንደን የኩዊን ሜሪ ዩኒቨርሲቲ ኘሮፌሰር ጀማ ሀርቪ የተመራው የተመራማሪዎች ቡድን ባካሄደው ጥናት በምስጥ የአፈር ቁልል ወይም ጉብታዎች፣ በጉማሬ በሚከፈት ማፋሰሻ – ሸለቆዎች፣ እንዲሁም በፍልፈል ዓፈር ውስጥ ለውስጥ አፈር እየተቦረቦረ- ረግረጋማ ቀጣናዎች ወ.ዘ.ተ እንደሚፈጠሩ አመላክቷል፡፡

በብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚ የመጀመሪያ በሆነው የሳይንስ ግኝቶች ህትመት በምድራችን 603 ዝርያዎች በገፀምድር ቀረፃ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ ነው የሰፈረው፡፡

ይህም በአካላዊ መጠን አነስተኛ ከሆኑት ጉንዳኖች ጀምሮ ፍልፈል፣ ዓሳ፣ ዓዕዋፍት ወዘተ በሂደቱ የላቀ ተሳትፎ ከሚያደርጉት መካከል ጥቂቶቹ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

እንስሳት ገፀምድር በመቅረጹ ሂደት በዓመት 76000 ጊጋ ጁል ሃይል ወይም በመቶ ሺህ ከሚቆጠር ከባድ ጐርፍ ከሚፈጥረው ኃይል መጠን ጋር ሊወዳደር የሚችል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ለአብነት ምስጦች በብራዚል በስፋት በኪሎሜትር የሚለካ የግንኙነት መረብ ፈጥረው ኮረብታዎችን እንደሚገነቡ ተመላክቷል፡፡

በወንዞች እና ሀይቆች የቀረሶ ዓሳ እንቁላላ መጣል እና መራባት ከደለል እና ጐርፍ ጋር የሚመጣጠን ለውጥ እንዲከሰት መንስኤ ይሆናሉ – ተፈጥሯዊ ገፀምድርን በመቅረፅ፡፡

በጥናቱ የተገኙ ቁልፍ ግንዛቤዎችን መሰረት አድርገው የጥናቱ መሪ ኘሮፌሰር ሀርቪ የእንስሳት ሚና መልክዓምድርን በመቅረፅ ረገድ ቀደም ባሉት ዓመታት ከታወቀው የበለጠ የጐላ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

በተለይም በአሁኑ ወቅት የብዝሃ ህይወት ወይም እንስሳት እና እፅዋት መመናመን ለገፀምድር ግንባታ ቁልፍ የሆኑትን እንስሳት ሊያሳጣ መቻሉ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ስጋትነቱን አፅንኦት ሰጥተው አስረድተዋል፡፡

ለዚህም በገፀምድር ግንባታ የአንበሳውን ድርሻ የሚጫወቱ እንስሳትን የመጠበቅ እና በአዳዲስ ቀጣናዎች ማስተዋወቅ፣ ማራባት ተግዳሮቶቹን ለመቋቋም ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን አስምረውበታል- ተመራማሪዎቹ፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here