የጉዳት ካሳ

0
10

የጉዳት ካሳን ምንነት እና በኢትዮጵያ ሕግ እንዴት ይገለፃል? የዚህ ሳምንት የፍትሕ እና አስተዳደር አምዳችን ትኩረት ነው፤ ጉደዳዩን በተመለከተም በፍትሕ ቢሮ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ ከሆኑት ከአቶ ስሜነህ ታደሰ ጋር ቆይታ አድርገናል::

ባለሙያው እንዳስገነዘቡት ጉዳት የሚለው ቃል በፍትሐ ብሔር ሕጉ ትርጉም ያልተሰጠው ቢሆንም ከድንጋጌዎቹ አጠቃላይ ይዘት በመነሳት በሰው ጥቅም፣ አካል ወይም ሕይወት ላይ የሚደርስ ጉድለት ስለመሆኑ ግንዛቤ ይወሰዳል:: በአጭር አገላለጽ ጉዳት በሰዉ ጥቅም ወይም ሀብት ላይ የሚደርስ ጉድለት ወይም ኪሳራ (የአካል ጉዳትን ጨምሮ) ነው::

ከፍተኛ የሕግ ባለሙያው ጉዳትን በተመለከተ በምሳሌ አስደግፈው እንደሚከተለው ያብራሩታል፤ በአካል ላይ የሚደርስ ጉዳትን ስንመለከት የወደፊት የመሥራት አቅምን ሊጎዳ የሚችል ዘላቂ ወይም ዛሬ ላይ ያለ /አሁን/ የሚታይ፣ ጊዜአዊ የአካል ጉዳት ነው:: ለምሳሌ በጽሑፍ ሥራ የምትተዳደር ሰው እጇ ቢቆረጥ ጉዳቱ ሠርቶ የመኖር ህይወቷን የሚጎዳ ቋሚ ጉዳት ነው::

ስለዚህ ጉዳትን ጉዳት በደረሰባቸው ሰዎች ከሥራቸው ጠባይ አንፃር መተንተንም ያስፈልጋል::

የጉዳት ካሳ የሚባለው ደግሞ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ጉዳት ሲደርስ በጉዳቱ የታጣውን ነገር የመመለስ (የማግኘት) መብትን የሚመለከት ነው::

ካሳው ከጉዳቱ መነሻ ወይም ምንጮች እንዲሁም ከውል ሊመነጭ ይችላል፤ አስቀድሞ ሰዎች ወደው እና ፈቅደው በሚያደርጉት ውል መሠረት ውል ገብተው ውሉን ባለመፈፀም /በመፍረሱ/ የሚደርስ ጉዳት በፍትሐ ብሔር ሕጉ 1790 ንኡስ አንቀፅ 2 ላይ ውል ባለመፈፀም መጠየቅ ይችላል::

የጉዳት ካሳ ምንጮች በራስ ጥፋት፣ ጥፋት ሳይኖር /የንብረት ባለቤት በመሆን/፣ በሌላ ሰው ጥፋት፣ በአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ ማስጠንቀቂያ ሳይሠጡ ሠራተኛ ማባረር ይጠቀሳሉ::

በሀብትና ንብረት ጉዳት ከደረሰ በገንዘብ ተተምኖ ካሳው ይከፈላል:: በአካል ለደረሠ ጉዳት ደግሞ ጉዳቱ ሰውን በአሽከርካሪ መግጨት ከሆነ ማሳከም፣ ያወጣውን ወጪ መተካት ብቻ ሳይሆን አልሚ ምግብ መሥጠት፣ ለወደፊት ሊደርስ የሚችለውን የአካል ጉዳት ታሳቢ አድርጎ ካሳ መስጠትን ያካትታል::

የንብረት ጉዳት ከሆነ ደግሞ በንብረቱ የደረሰው ጉዳት ታውቆ ጉዳቱ ተሰልቶ ይከፈላል::

እንደ አቶ ስሜነህ ማብራሪያ ለተጎጂው የሚገባውን ካሳ ለማስላት የተጎጂውን የሥራ ሁኔታ ማወቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል:: ጉዳት የደረሰበት ሰው ተቀጥሮ የሚሠራ፣ የራሱን ሥራ እየሠራ የሚኖር ወይም ሥራ በመሥራት ላይ ያልነበረ ሰው ሊሆን ይችላል::

ተቀጥሮ የሚሠራ ሰው ላይ ጉዳት ቢደርስ በቅድሚያ ጉዳቱ የደረሰው ከሥራው ጋር በተገናኘ መሆን አለመሆኑን መለየት ግድ ይላል:: ጉዳቱ የደረሰው ከሥራው ጋር የተገናኘ ከሆነ የክርክር ሂደቱም ሆነ የካሳ አሰላል ሥርዓቱ የሚመራው በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1064/2010 እና አዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሠረት ይሆናል::

ከሥራው ጋር የማይገናኝ ከሆነ ግን ከውል ውጪ ኃላፊነት በሚሉ የሕግ ድንጋጌዎች መሠረት የሚመራ ይሆናል:: የደረሰው ጉዳት ጊዜያዊ ከሆነ ሥራ እስከሚጀምር ድረስ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ያክል መጠን ካሳ ሊያገኝ ይገባዋል:: ጉዳቱ በከፊል ቋሚ ከሆነ ደግሞ መሥራት ባላስቻለው መጠን ልክ ይሰላለታል:: ጉዳቱ ቋሚ ሆኖ መሥራት የማያስችለው ከሆነ ደግሞ መሥራት እስከሚችልበት ጊዜ ድረስ (እስከ ጡረታ ጊዜው) ተሰልቶ ካሳው ይሰጠዋል::

የአካል ጉዳት በደረሰ ጊዜ የወደፊት ጉዳት ካሳ አሰላል ላይ የሚከተሉት ጉዳዮች ግምት ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ባሙያው ያብራራሉ::

የራሱን ሥራ እየሠራ ሲተዳደር የነበረ ሰው ጉዳት ቢደርስበት ካሳውን ለማስላት የሚያስችለውን ገቢ ለማወቅ ሊከብድ ይችላል:: ቢሆንም የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ወርሐዊ ወይም የዓመት አማካይ ገቢውን በማየት ያጣውን ወይም ሊያጣ የሚችለውን ጥቅም በማስላት ካሳውን መተመን ይቻላል::

በሌላ በኩል በሕመም፣ ለመሥራት ባለመፈለግ፣ የሚመጥነውን ሥራ በማጣት ወይም በጠቅላላው ሥራ አጥ በመሆን ሥራ እየሠሩ ያልነበሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል:: በዚህ ሁኔታ ያለ ሰው ጉዳት በሚያጋጥምበት ጊዜ የገቢውን መጠን ለማወቅም ሆነ ካሳውን ለማስላት ያስቸግራል::

ሌላው የህሊና (አዕምሯዊ) ጉዳት ነው፤ ይህም የተጎጂውን ኢኮኖሚ ነክ ጥቅሞችን የሚጎዳ ሳይሆን በተጎጂው ላይ የስሜት መጎዳት፣ ሀዘን፣ ሀፍረትን እና የመሳሰሉ ሞራላዊ ጉዳቶችን የሚፈጥር ነው::  ይህም በፍትሐ ብሔር ሕጉ 1952 ዓ.ም በወጣው ሕግ የሚዳኝ ቢሆንም የሚሰጠው የካሳ ብር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀፅ 2116 ላይ እደተደነገገው የሞራል ካሳው አንድ ሺህ ብር ነው::

ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅጅና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ ቁጥር 410/1996 ንኡስ ቁጥር 134 ላይ የተለያዩ ዘፈኖች እና ፊልሞች በሌላ ሰው ከተሠረቁ፣ ከተሠሩ ወይም ከተቀረጹ በደራሲያን ላይ የደረሰውን ጉዳት በማመዛዘን የሞራል ጉዳት ካሳ ከ100 ሺህ ብር የማያንስ መሆኑን ደንግጓል::

ባለሙያው አቶ ስሜነህ እንደሚገልጹት የአካል ጉዳት ከህሊና እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የበለጠ ነው:: ባለሙያው አክለውም የጉዳት አይነቶችን በማንሳት እንደሚከተለው ያብራረዋቿል::

መጀመሪሪያው ጊዚያዊ የአካል ጉዳት ነው፤ ጉዳቱ  ጊዚያዊ ሕመምና ስቃይ ቢያስከትልም ቁስሉ የሚድንና ስብራቱም ከትንሽ ጊዜ በኋላ የሚጠገን ነው፤ ሥራውንም እንደወትሮው ለማከናወን የሚስችል ነው::

በጥገና ወደነበሩበት የሚመለሱ የእጅና የእግር ስብራት፣ በራስ አካባቢ መፈንከት እና የመሳሰሉት ጉዳቶች ጊዜያዊ የአካል ጉዳቶች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ነበሩበት የሚመለሱ ናቸው:: በአጠቃላይ ጊዜያዊ የአካል ጉዳት ማለት ሠራተኛው ሥራውን በተወሰነ ጊዜ በሙሉ ወይም በከፊል ለማከናወን እንዳይችል የሚያደርገው የአካል ጉዳት ነው::

ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት የሚባለው ደግሞ ሌላው የጉዳት አይነት ነው፤ ሥራን አንደ ድሮዉ አቀላጥፎ ለመሥራትና እንደልብ ለመንቀሳቀስ የማያስችል ነው:: በመጠኑም ቢሆን ቀለል ያሉ ሥራዎችን ግን ከመሥራት አይከለክልም:: የመስማት ችግር፣ የአንድ እጅ ወይም እግር መቆረጥ እና የአንድ ዓይን መጥፋት ከዚህ ክፍል የሚመደቡ ጉዳቶች  ናቸው:: እነዚህ ጉዳቶች ዘላቂ ቢሆኑም ሙሉ ለሙሉ ሥራን ለመሥራት ከልካዮች አይደሉም::

ሌላው የጉዳት አይነት ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ነው፤ ዘላቂ የአካል ጉዳት ጉዳቱ የደረሰበትን ሠራተኛ የመሥራት ቻሎታ የሚቀንስ፣ የማይድን ጉዳት ነው:: ይህ ከሁለም የጉዳት ዓይነቶች ከባዱ ነው:: በመሆኑም ማንኛውንም ዓይነት ሥራ ለመሥራት አያስችልም:: ይህ ዓይነት ጉዳት የደረሰበት ሰው ዕድሜ ልኩን የግል ህይወቱን ለመምራት ስለማይችል የሌሎች ሰዎች እርዳታ ያስፈልገዋል::

በአጠቃላይ አንድ ሰው ሙሉ የአካል ጉዳት ከደረሰበት በጊዜያዊነትም ሆነ በዘላቂነት ለዕለት ኑሮው ማድረግ የሚገባዉን እንደወትሮዉ ለማከናወን  ይቸገራል::

ለጉዳቶቹ የሚሰጠው ታዲያ ካሳ መሆኑን ያብራራሉ፤ ተጎጂው ላይ ለደረሰው የአካል ጉዳት ካሳ ለማግኘት ተጎጂው በጉዳቱ ያጣውን ጥቅም የማስረዳት ኃላፊነት አለበት:: የደረሰበት የጉዳት መጠንም በሕክምና ባለሙያ ተጠንቶ  ይቀርባል:: ጉዳቱ ሥራ ያሠራዋል አያሠራውም የሚለውን የሚገልጽ መሆንም አለበት፤ ለምሳሌ 20 ከመቶ ተጎድቶ ከሥራው ባህርይ አንፃር ግን ምንም የማያሠራው ከሆነ 100 ከመቶ የጉዳት  መጠን /ከሥራ ውጭ/ መሆኑ ተሰልቶ ነው ካሳ የሚሠጠው::

በአደጋ ምክንያት ሞት ባጋጠመ ጊዜ ደግሞ ካሳ የመጠየቅ መብት ያለው ማነው የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ነው::  በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር  2095 መሠረት ካሳ የመጠየቅ መብት ያላቸው የሟች ባል ወይም ሚስት፣ የሟች ወላጆችና የሟች ተወላጆች ናቸው፤ እነዚህ ሰዎች ለደረሰባቸው ጉዳት (በሟች የሚደገፉ መሆናቸውም ታሳቢ ይደረጋል) ካሳ መጠየቅ ይችላሉ:: ለእነዚህ ሰዎች የሚከፈለው ካሳ የቀለብ /የመተዳደሪያ/ ስለሆነ በቤተሰብ ሕጉ መሠረት ቀለብ ጠያቂ ሊያሟላቸው የሚገቡ መስፈርቶችን ማሟላትና ማስረዳት ይጠበቃል:: መስፈርቶቹም ሠርቶ ገቢ ማግኘት የማይችል መሆኑን እና የጉዳት አድራሹን የመክፈል አቅም ያገናዘቡ ናቸው::

የሕግ አንቀጽ

 

በፍትሐ ብሔር ሕጉ የህሊና ጉዳት ካሳ የሚያስከፍሉ ጥፋቶች

  • በተበዳዩ ሰውነት ላይ ስለሚደርስ ጉዳት – የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2107።
  • ያለአግባብ ሰውን በመያዝና በማገድ የሚደርስ ጥፋት – የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2108::
  • በሥም ማጥፋት ስለሚደርስ ጉዳት – የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2109
  • የባልና ሚስትን መብት በመድፈር የሚደርስ ጥፋት የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2110

ምንጭ፡- ፍትሕ ሚኒስቴር

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here