የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ

0
252

የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ስር የሚተዳደር ሲሆን የተመሠረተውም በ2011 ዓ.ም ነው፡፡ ጊቤ ሸለቆ ስያሜውን ያገኘው በሸለቆው ከሚፈሰው የጊቤ ወንዝ  መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ፓርኩ ከአዲስ  አበባ በስተደቡብ ምዕራብ 174 ኪሎ ሜትር ወደ ጅማ የሚወስደውን ጐዳና ተዋስኖ በጉራጌ ዞን ሦስት ወረዳዎች ውስጥ የተከለለ ነው፡፡ ወረዳዎቹም ቸሀ፣ አበሽጊ እና እነሞርናጊነር ናቸው፡፡

የፓርኩ ጠቅላላ ስፋት 360 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ተለክቷል፡፡ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጡም ከመሬት ወለል በላይ ከዝቅተኛው 980 እስከ ከፍተኛው 1,835 ሜትር መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ የፓርኩ ክልል ዋና መስሪያ ቤት መገኛ ወልቂጤ ከተማ ነው፡፡ ጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ የ17 አጥቢ እንስሳት መኖሪያ መሆኑ ተረጋግጧል – ከነዚህም መካከል አንበሳ፣ ጉማሬ፣ አነር፣ ነብር፣ የዱር አሣማ፣ ዝንጅሮ… ይገኙበታል፡፡

በፓርኩ ክልል 200 የአእዋፍ ዝርያዎች እንደሚገኙም ተመዝግቧል፡፡ በፓርኩ ውስጥ በዋናነት ከሚፈሰው የጊቤ ወንዝ በተጨማሪ የአኖ፣ ዋቢ፣ ዋቄ፣ ደጐሳን የመሣሰሉ ፍል ውኃ ምንጮች መገኛ ነው፡፡

የፓርኩ ክልል በሆነው በአበሽጊ ወረዳ ስድስት ቀበሌዎች ህገወጥ ሰፈራ፣ ለዕርሻ መሬት መስፋፋት የፖርኩን ክልል መጣስ፣ ከሠል ለማምረት የዛፎች መጨፍጨፍ፣ ልቅ ግጦሽ፣ የእሳት ቃጠሎን ሆን ብሎ ለዕርሻ መሬት ማስፋፊያ ማስነሳት፣ አደን እና ህገወጥ ዓሣ አስጋሪዎች ስጋት ሆነው ተስተውለዋል፡፡

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ሳይንስ ዳይሬክት፣ ኘሬስ ዶት ኢቲ፣ ሪሰርች ዶት ኔት፣ ሎንሊ ኘላኔት ድረ ገጾችን ተጠቅመናል፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here