የጋራ ጥረት ለጋራ ተጠቃሚነት!

0
202

የአማራ ክልል በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ የመስህብ ሀብቶች የታደለ ነው፡፡ ከታህሣሥ

መጨረሻ ጀምሮ በየዓመቱ የሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት እና ባሕላዊ ክዋኔዎችም ክልሉን የበርካታ

ጎብኝዎች መናኸሪያ እንዲሆን ያደርጉታል፡፡ የልደት እንዲሁም የጥምቀት በዓል፣ የአገው ፈረሰኞች

ዓመታዊ በዓል እና ሌሎችም የአማራ ክልል የወርሀ ጥር በረከቶች ናቸው፡፡

ክልሉ እነዚህን የመስህብ ሀብቶች፣ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክዋኔዎች በተለይም ከ2012 በፊት

በየዓመቱ ከታህሣሥ መጨረሻ ጀምሮ ለገጽታ ግንባታ እና ለዘርፉ መነቃቃት ሲጠቀምባቸው ኖሯል፡፡

ይሁን እንጂ፣ በ2012 የተከሰተው ዓለም አቀፉ የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ከ2013 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት

የዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት፣ ከሐምሌ 2015 ጀምሮ በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት ክልሉ የመስህብ

ሐብቶችን በሚፈለገው ልክ እንዳይጠቀምባቸው እንቅፋት ሆነውበታል፡፡

ከኮቪድ ወረርሽኝ መከሰት በፊት በአመት ክልሉን እስከ 207 ሺህ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች

ይጎበኙት እንደነበር የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ያሳያል፡፡ እንዲሁም በ2016 ዓ.ም 20 ሺህ

የውጭ ሀገር እና ስምንት ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ሐብቶችን

ጎብኝተዋል፡፡

ሆኖም ኮቪድ እንዲሁም የሰላም እጦት ከተከሰተ ወዲህ ጎብኝዎች ክልሉን እንደልብ

ተንቀሳቅሰው እንዳይጎበኙት በማድረጉ ቱሪዝሙ የሚፈጥረው የሥራ ዕድል ተቀዛቅዟል፡፡ ይህን

ተከትሎ መተዳደሪያቸውን ጎብኝዎችን በማጓጓዝ፣ የሆቴል አገልግሎት በመስጠት፣ የስጦታ

እቃዎችን በመሸጥ፣ ጓዛቸውን በበቅሎ በማድረስ፣ መንገድ በመምራት… ያደርጉ የነበሩ ወገኖች

እንቅስቃሴያቸው በእጅጉ ተገድቦባቸው ይገኛል፡፡

እናም እንደቀደሙት ዓመታት ተንቀሳቅሰው ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ይችሉ ዘንድ የክልሉን

ሰላም መሆን አብዝተው እየሻቱ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥትም የክልሉን ሰላም ወደ ተሟላ ሁኔታ

ለመቀየር እየሠራ ይገኛል፡፡ የልማት ሥራዎች እና ሌሎች የክልሉን ገቢ የሚያሳድጉ ተግባራት እየተሠሩ

ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ከታህሣሥ መጨረሻ ጀምሮ የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላትን በድምቀት

ለማክበርም ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ፣ ለጎብኝዎችም ጥሪ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በርካታ ጎብኝዎችም ጥሪውን ተቀብለው ባሕር ዳርን ዋና መዳረሻቸው ያደርጋሉ ተብሎ

ይጠበቃል፡፡ እናም ወሩን ባሕር ዳርን ማስተዋወቂያ፣ ለገጽታ ግንባታ እና የሕዝቡን እንግዳ ተቀባይነት

ማስመስከሪያ አድርጎ ለማለፍ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ የጽዳት ዘመቻም ከዝግጅቶቹ አንዱ ነው፡፡

የንግድ እና ባዛር ትርኢት እንደሚከፈትም ተመላክቷል፡፡

የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ ባሕላዊ የገና ጨዋታ ክዋኔ የ”ጥርን በባሕር ዳር” መክፈቻ

ሁነት እንደሚሆን ታውቋል፡፡ የባህል እና ኪነ ጥበባት ዝግጅትም በከፍተኛ ድምቀት እንደሚከናወን

ተጠቁሟል፡፡ የከተማዋ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ለጎብኝዎች ምቹ ሆነው ተዘጋጅተዋል። የባሕረ ዳር

መታወቂያ የሆነው የብስክሌት ሽርሽርም ይካሄዳል፡፡

የከተራ በዓልን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ታውቋል። የቃና ዘገሊላ፣

የአቡነ ዘራብሩክ፣ ሰባሩ ጊዮርጊስ እና አስተርዮ ማርያም በዓላትን በልዩ ድምቀት በማክበር የቱሪዝም

ዘርፉን ለማነቃቃት ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው፡፡ የታንኳ ቀዘፋ ትርኢት የ”ጥርን በባሕር ዳር” ልዩ

ድምቀት ሆኖ ይካሄዳል፡፡ የፈጠራ ምርቶች ለዐውደ ርዕይ ይቀርባሉ፡፡

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በርካታ ታዳሚዎች ወደ ክልሉ እንዲገቡ የሚቀሰቅሱ የማስታወቂያ

ሥራዎችን እያከናወነ ነው፡፡

የ”ጥርን በባሕር ዳር” መርሀ ግብር ለሕዝቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከፍ ያለ ጠቀሜታ ያለው

በመሆኑ በበዓሉ ከመሳተፍ ጀምሮ ለጉብኝት የሚመጡትን እንግዶች በሚገባ ተቀብሎ ማስተናገድ

ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን የእንግዶችን የቆይታ ጊዜ ማራዘም እንዲሁም ገጽታን መገንባት ይቻላል፡፡

ስለሆነም እነዚህ ቁም ነገሮች ታሳቢ ተደርገው የተጀማመሩት እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል

ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሕዝቡ ከፍተኛ ተሳትፎ ይጠበቃል፡፡ ሕዝቡ ከዚህ ቀደም ይታወቅበት

የነበረውን መልካም የእንግዳ አቀባበል እና አያያዝ እሴት በማሳየት ለጋራ ተጠቃሚነቱ መረጋገጥ

ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ ሁሉን አቀፍ የጋራ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡

በኲር የታኅሳስ  14  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here